የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ጥቅምት እንደሚጀምር ሲታወቅ የሊጉ ውድድር የሚጀመርበት አንድ ከተማ ላይ ለውጥ ሳይደረግ እንዳልቀረ ተሰምቷል።
20 ተሳታፊ ክለቦች በመያዝ በሁለት ምድብ ተከፍሎ ጥቅምት 8 ቀን እንደሚጀመር ቀን ቀጠሮ እንደተቆረጠለት እና ባሳለፍነው ሳምንት የእጣ ማውጣት መርሃ ግብር ተካሂዶ ቡድኖቹ ምድባቸውን ማወቅ መቻላቸው ይታወሳል።
በዚሁ ዕለትም ከተመረጡት አራት ከተሞች መካከል የመጀመርያውን ዙር አዲስ አበባ ከተማ እና አዳማ ከተማ ውድድሩን ለማስተናገድ መመረጣቸው ከመድረኩ ተጠቁሞ ነበር።
ሆኖም አሁን እየወጣ ባለው መረጃ መሠረት ደግሞ አንደኛው የተመረጠው ማለትም አዳማ ከተማ የመጫወቻ ሜዳ አመቺ አለመሆኑን ተከትሎ ወደ ሌላ ከተማ ለማዞር አወዳዳሪው አካል ስራዎችን ለመስራት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።
በአዳማ ከተማ ምትክ ሀዋሳ ከተማ ወይም ድሬደዋ ከተማ ለማድረግ የታሰበ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያ እንደ መረጃ ምንጮቿ ከሆነ ወደ ድሬደዋ የአንደኛው ምድብ ውድድር የመሄድ ዕድሉ ሰፊ እንደሆነ ሰምተናል። በቀጣዮቹ ቀናትም አወዳዳሪው አካል አጠቃላይ መርሐ-ግብሩን የተመለከተ መረጃ ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
አስቀድሞ በአዲስ አበባ ለማድረግ የታሰበው አንደኛው ምድብ ውድድር ግን በተባለበት ቀንና ጊዜ እንደሚከናወን አውቀናል።