የዋልያዎቹ ተጋጣሚ ስብስባቸውን ይፋ አደረጉ

የዋልያዎቹ ተጋጣሚ ስብስባቸውን ይፋ አደረጉ

በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ዋልያዎቹን  የምትገጥመው ቡርኩናፋሶ ስብስቧን ይፋ አደረገች።

ለ2026 የአለም ዋንጫ የማጣሪያ ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ የተደለደለችው ቡርኪናፋሶ ከሴራልዮን እና ኢትዮጵያ  ላሉባት ሁለት የዓለም ዋንጫ የማጣርያ ጨዋታዎች ስብስቧን ይፋ አደርጋለች።

የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ብራማ ትራኦሬ በሁለቱም የማጣርያ ጨዋታዎች የሚጠቀሟቸው 26 ተጫዋቾችን ዛሬ ይፋ ሲያደርጉ በስብስቡም በኢንግሊዙ ብሬንትፎርድ የሚጫወተው ዳንጎ ኦታራ፣ የባየር ሊቨርኩሰኑ ኤድመንድ ታብሶባ፣ የማንቸስተር ሲቲ አካዳሚ ውጤት የሆነው እና በአሁኑ ወቅት በፈረንሳዩ ማርሴይ በመጫወት የሚገኘው የመስመር ተከላካዩ ኢሳ ካቦሬ፣ በኔዘርላንዱ ፒ ኤስ ቪ አይንድሆቨን የሚጫወተው ተከላካዩ አዳሞ ባጋሎ እንዲሁም በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ አዲስ አዳጊው ሰንደርላንድ በመጫወት ላይ የሚገኘው በርትራንድ ትራኦሬ አካተዋል።

ምድቡን ግብፅ በ20 ነጥብ ስትመራ ቡርኪናፋሶ በአምስት ነጥብ ዝቅ ብላ 15 ነጥቦች በመሰብሰብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ሴራልዮን እና ጊኒ ቢሳው ደግሞ ተከታትለው ተቀምጠዋል።  ሀገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ በስድስት ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ጅቡቲ በአንድ ነጥብ ግርጌ ላይ ተቀምጣለች።

ቡርኪናፋሶ እና ኢትዮጵያ ከአስር ቀናት በኋላ ጥቅምት 2 በ ‘August 4 1983’ ስቴድየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።