ትኩረት | ፕሪምየር ሊጉ እየተጀመረ ወይስ እየተጠናቀቀ ?

ትኩረት | ፕሪምየር ሊጉ እየተጀመረ ወይስ እየተጠናቀቀ ?

የ2018 የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ጅማሮውን አድርጓል ፤ አጀማመሩ ግን ብዙም ያልተለመደ ነበር…..

በሁለት ምድቦች ተከፍሎ አዲስ አበባ እና ሀዋሳ ከተሞች ላይ ጅማሮውን ባደረገው ውድድር ገና በመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት ባልተለመደ መልኩ በርከት ያሉ እጅግ አደገኛ የሆኑ የሃይል አጨዋወቶች እና ቀይ ካርዶች የተመለከትንበት ነበር።

በጨዋታ ሳምንቱ በተመለከትናቸው በርከት ያሉ የሃይል አጨዋወቶች መነሻነት ጥቂት የማይባሉ ተጫዋቾች ከባድ ከሚባል ጉዳት ለጥቂት ሲተርፉ ሀቢብ ከማል ፣ ወገኔ ገዛኸኝ፣ ዘላለም አበበ እና ክንዱ ባየልኝ ደግሞ ከበድ ያለ ጉዳት አስተናግደው ከሜዳ ለመውጣት ተገደዋል። በጨዋታ ሳምንቱም ብሩክ እንዳለ ፣ ዳንላድ ኢብራሂም ፣ ሀይደር ሸረፋ እና ኤልያስ አህመድ ደግሞ የቀይ ካርድ ሰለባ ሆነው የተመለከትንበት ነበር።

እግር ኳስ የንክኪ ስፖርት እንደመሆኑ በተጫዋቾች መካከል አካላዊ ንክኪዎች መኖራቸው የግድ ቢልም በመጀመሪያ ሳምንት የተመለከትናቸው አብዛኞቹ የሃይል አጨዋወቶች ግን ኳሶችን ለማሸነፍ የማይመስሉ ፍፁም ኃላፊነት የጎደላቸው እንደመሆኑ ማንሳት ይቻላል ፤ ለአብነትም የሀዲያ ሆሳዕናው ኤልያስ አህመድ የባህር ዳር ከተማው ላይ የሰራው ጥፋት በየትኛውም አመክንዮ ኳሷን ለማሸነፍ የታለመ ነው ለማለት የሚያዳግት ነው።
ሌላው የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ዳንላድ ኢብራሂም በሸገር ደርቢ በተሳሳተ የጊዜ አጠባበቅ ከግብ ክልሉ ወጥቶ በሰራው ጥፋት እንዲሁ ከሜዳ የወጣበት አጋጣሚ ሌላው ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ተብሎ መውሰድ የሚቻል ነው።


ሌላው ከቀይ ካርዶቹ ጋር ተያይዞ ማንሳት የሚገባን ጉዳይ ቀይ ከተመለከቱት ተጫዋቾች አብዛኞቹ ባለልምድ የመሆናቸው ጉዳይ ነው ፤ በፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ማለትም የጨዋታው ውጤት በቡድኖቹ መፃኢ ጉዞ ላይ እዚህ ግባ የሚባል ተፅዕኖ በሌለበት በዚህ ወቅት በእነሱ ደረጃ የካበተ ልምድ ያለው ተጫዋች መሰል ድርጊቶችን ሲፈፅሙ ማየት የሚያስተዛዝብ ነው። በመጨረሻም ሊጉ ገና እየተጀመረ ነው የሚለው ጉዳይ ሊሰመርበት ይገባል ፤ ገና በመጀመሪያ ሳምንት መሰል የኃይል አጨዋወቶች እና ካርዶች መብዛታቸው ከሊጉ የፉክክር ሚዛን ፣ ከስፓርታዊ ጨዋነት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚኖራቸውን ተፅዕኖ ታሳቢ በማድረግ ሁሉም አካል በአስተውሎት መንቀሳቀስ ይገባዋል።