የቀድሞ የዋልያዎቹ አለቃ ወደ ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ሊያቀኑ ነው

የቀድሞ የዋልያዎቹ አለቃ ወደ ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ሊያቀኑ ነው

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የምዕራብ አፍሪካ ሀገር ክለብ ለማሰልጠን በቀጣይ ሳምንት እንደሚያቀኑ አውቀናል።

የቀድሞ የዋልያዎቹ አለቃ እና የተለያዩ የሀገሪቱ ክለቦችን ያሰለጠኑት ስኬታማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ባሳለፍነው ዓመት ከፋሲል ከነማ ጋር ከነበራቸው ቆይታ በስምምነት ከተለያዮ በኋላ በአሁኑ ወቅት ክለብ አልባ ሆነው በዕረፍት ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።

ሶከር ኢትዮጵያ አሁን እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ላይቤሪያ የሚገኝ አንድ ለጊዜው ስሙን ያልታወቀ ክለብ የአሰልጥነን ጥያቄ እንዳቀረበላቸው ሰምተናል። ጥያቄውን የተቀበሉት አሰልጣኙም አንድ አንድ የጉዞ ጉዳዮች እና የወረቀት ጉዳዮችን ጨርሰው በቀጣይ ሳምንት ወደ ስፍራው እንደሚያቀኑ አረጋግጠናል። አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከዚህ ቀደም የሊጉን ዋንጫ ባሳኩበት ኢትዮጵያ ቡና፣ አዳማ ከተማ፣ ደደቢት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ሰበታ ከተማ፣ ፋሲል ከነማ በውጭ ሀገርም የሱዳኑን አልአህሊ ሸንዲ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ማሰልጠናቸው ይታወቃል፡፡አሰልጣኙም ሹመቱን ካጠናቀቁ በኋላ የላይቤሪያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዋና አሰልጣኝነት በመምራት ላይ ከምትገኘው ኢንስትራክተር ሰላም ዘርዓይ ቀጥሎ በሀገሪቱ ያሰለጠኑ ሁለተኛ ኢትዮጵያዊ ይሆናሉ።