ዐበይት ጉዳዮች 2 |  ሽንፈት አልባው የዐፄዎቹ ጉዞ

ዐበይት ጉዳዮች 2 |  ሽንፈት አልባው የዐፄዎቹ ጉዞ

አስከፊውን አጀማመር የቀለበሰው በሊጉ ሽንፈት ያልቀመሰ ብቸኛ ክለብ …ፋሲል ከነማ !

ፋሲል ከነማ ዘጠነኛ ሳምንት ላይ በደረሰው የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሽንፈት ያልቀመሰው ብቸኛ ቡድን ነው። በተከናወኑ ዘጠኝ ጨዋታዎች በአራቱ ድል አድርጎ በአምስቱ ነጥብ የተጋራው ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሁለት መርሐ-ግብሮች መሪነቱን ማስጠበቅ ሳይችል ቀርቶ ድል ማድረግ ባይችልም ያለመሸነፍ ጉዞውን ግን አስቀጥሏል።

ዐፄዎቹ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን ከቀጥሩ በኋላ በዓመቱ መጀመርያ በተካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ የህዳሴ ዋንጫ ላይ በምድብ ‘ሀ’ ከቅዱስ ጊዮርግስ እና መቻል ጋር ተደልድለው በምድብ ጨዋታዎች ላይ ሁለት ሽንፈቶች እንዲሁም በድምር 7 ግቦች  አስተናግደው  ከውድድሩ በጊዜ ሲሰናበቱ በቡድናቸው አጀማመር የተከፉ ደጋፊዎች ጥቂት አልነበሩም። ምንም እንኳን ውድድሩ የቅድመ ዝግጅት አንድ አካልና የአቋም መፈተሻ ቢሆንም ቡድኑ በሁለት ጨዋታዎች ላይ ያሳየው እንቅስቃሴ፣ የገጠመው ተከታታይ ሽንፈት እና የተቆጠረበት የግብ መጠን ሲታይ በወቅቱ በፕሪምየር ሊግ በዚህ የጥንካሬ ደረጃ ይቀርባል ብሎ መገመት አዳጋች ነበር። ሆኖም በጉዳት እና በቅጣት በተፈተኑባቸው ዘጠኝ ሳምንታት ውስጥ  በጠንካራ የመከላከል እና ጥብቅ የቡድን አደረጃጀት ሽንፈት ሳይቀምሱ አጀማመራቸውን አሳምረዋል።

በዐፄዎቹ ያለመሸነፍ ጉዞ ውስጥ እንደ ቡድን በርካታ አወንታዊ ጎኖች መጥቀስ የሚቻል ቢሆንም ካበረከቱት አስተዋፅዖ አንፃር ሲመዘን ግን ውጤታማውን የተከላካይ ክፍል የሚገዳደር የለም። በተለመደው የአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የጨዋታ መንገድ የተገነባው የቡድኑ የመከላከል ውቅር ካከናወናቸው 9 ጨዋታዎች ውስጥ በ6ቱ መረቡን ማስከበሩ፤ 3 ግቦችን ብቻ ማስተናገዱ እንዲሁም በዘጠኝ ሳምንታት ጉዞ በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ አለማስተናገዱም ስለ ጥንካሬው የሚነግረን ነገር አለ።

እግር ኳስ የቡድን ስራ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች የግለ-ሰብ አበርክቶ ከፍ የሚልበት አጋጣሚ እንዳለም ሁሉም የሚስማማበት ሀቅ ነው። በዚህ መሰረት ስለ ዐፄዎቹ ያለመሸነፍ ጉዞ ጥንካሬ ሲገለፅ የተከላካይ ክፍሉ ቁልፍ ተጫዋች መሆኑ እያስመሰከረ የሚገኘው አምበሉ ምኞት ደበበ፤ ከቡድኑ ጋር ለመዋሃድ ጊዜ ያልፈጀባቸው ግብ ጠባዊው ሞይስ ፖዋቲና ዋሳዋ ጂኦፍሪ፤ ዳግም ወደ ክለቡ የተመለሱት አምሳሉ ጥላሁን እና ሁለገቡ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ እንዲሁም በጣምራ 5 ግቦች ያስቆጠሩት በረከት ግዛው እና ቃልኪዳን ዘላለም አበርክቶ መጥቀስ ተገቢ ነው።

አሰልጣኝ ዮሐስን ሳህሌ በቅድመ ውድድር አስከፊ አጀማመር ያደረገውን ቡድናቸው ለማስተካከል ያደረጉት ፈጣን ምላሽ ሌላው በአወንታነቱ የሚጠቀስ ነጥብ ነው። ጅማሯቸውም ባለፈው ዓመት ቅጥ ያጣው የክለቡ ውጤት ታግሰው ለቆዩ ደጋፊዎቻቸው ተስፋ የሰጠ ሆኗል።

በ2010 በመቐለ 70 እንደርታ ቆይታቸው ከሰሩት ቡድን ጋር በብዙ ረገድ የሚመሳሰል ለተጋጣሚ ቡድን የግብ ዕድሎች የማይፈቅድ፣ ሳጥኑ እምብዛም የማያስደፍር እና በመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር የሚሞክር ቡድን የገነቡት ለወትሮ በጠጣር አቀራረባቸው የሚታወቁት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ከላይ ከተጠቀሰው ወቅት በኋላ የቡድናቸው አካሄድ ፈር ለማስያዝ ጊዜ አልፈጀባቸውም፤ እስካሁን ባለው ጉዞም በተለይም  የመከላከል አደረጃጀት ጥንካሬያቸው ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሩ የሚሆኑበት ዕድል እንዳለም ማሳያ ነው። ሆኖም ካላቸው የቡድን ጥራት እና ጥልቀት ችግር እንዲሁም ተደራራቢ የተጫዋቾች ጉዳት አንፃር የውድድር ዓመት በምን ዓይነት አኳኋን  ይዘልቁታል የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ ነው። በአንድ ወቅት የፊት አጥቂው አመለ ሚልክያስ የተዋጣለት ተከላካይ አማካይ ካደረጉበት ብዙዎችን ያስገረመው ውሳኔ ጨምሮ የበርከት ያሉ ተጫዋቾች ሚና እየቀያየሩ በመጠቀም የሚታወቁት አሰልጣኙ የሚና ለውጥ ጉዳት እና ቅጣት ላመናመነው ቡድናቸው እንደ አንድ መፍትሔ የሚጠቀሙበት ዕድል እንዳለም ይታመናል።

በሊጉ ለዘጠኝ የጨዋታ ሳምንታት ሳይሸነፉ የዘለቁት ዐፄዎቹ በቀጣይ ሳምንታት ከነገሌ አርሲ፣ ባህርዳር ከተማ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ አዳማ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ከመሳሰሉ  ክለቦች የሚገጥማቸውን ፈተና አልፈው ያለመሸነፍ ግስጋሴያቸው ያስቀጥሉ ይሆን? ጊዜ የሚመልሰው ጥያቄ ይሆናል።