መረጃዎች | የ10ኛው ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

መረጃዎች | የ10ኛው ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

በኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች ተቋርጦ የነበረው የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ የ10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ይጀመራል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ አርባምንጭ ከተማ

በስምንት ነጥቦች በ15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች የውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ድላቸውን አስመዝግበው ደረጃቸውን ለማሻሻል አዞዎቹን ይገጥማሉ። በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በሲዳማ ቡና እና ወልዋሎ ሽንፈት ያስተገዱት ሀምራዊ ለባሾቹ ድል ካደረጉ አምስት የጨዋታ ሳምንታት አስቆጥረዋል። ቡድኑ በ8ኛው ሳምንት ጨዋታ በሲዳማ ቡና ሽንፈት ቢያስተናግድም ያሳየው እንቅስቃሴ ግን በአወንታነት የሚጠቀስ ነበር፤ በዛሬው ጨዋታም በመጨረሻው መርሐግብር ጨዋታ በመቆጣጠርም ሆነ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ደካማ የነበረውን እንቅስቃሴያቸው ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል።

በአምስት ነጥቦች 19ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አርባምንጭ ከተማዎች ዘጠነኛ ሳምንት ላይ በደረሰው የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ድል ማድረግ አልቻሉም። አራት ሽንፈቶች እና አምስት የአቻ ውጤቶች ያስመዘገበው ቡድኑ ከአስከፊው ጉዞ ለመላቀቅም ዘርፈ ብዙ ለውጦች ማድረግ ግድ ይለዋል። በተለይም ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ላይ አንድ ግብ ብቻ እንዲሁም በዘጠኝ መርሐግብሮች አራት ግቦች ያስቆጠረው የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት በብዙ ረገድ መሻሻል የሚገባው ነው። በረዣዥም ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት የሚያደርግ የማጥቃት አጨዋወት በመከተል ላይ የቆዩት አሰልጣኝ በረከት ደሙ በቀጣይ የግብ ዕድሎች በተሻለ ጥራት መፍጠር የሚችል አጨዋወት ማበጀት ይጠበቅባቸዋል።

በንግድ ባንክ በኩል ተከላካዩ ያሲን ጀማል ከቅጣት ሲመለስ ሌላኛው የመሃል ተከላካይ ካሌብ አማንክዋህ በቅጣት የማይኖር ይሆናል። በአዞዎቹ በኩል አንዱዓለም አስናቀ እና በርናርድ ኦቼንግ በጉዳት የዛሬው ጨዋታም ያመልጣቸዋል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ በአጠቃላይ 14 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 4 ጊዜ ሲያሸንፍ አርባምንጭ ከተማ በ3 ጨዋታዎች ድል ቀንቶታል በተቀሩት 7 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ንግድ ባንክ 17 ግቦች፣ አርባምንጭ 16 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ምድረ ገነት ሽረ ከ ባህር ዳር ከተማ

በመጨረሻዎቹ አራት የጨዋታ ሳምንታት ጥሩ መሻሻል ካሳዩ የሊጉ ክለቦች የሚጠቀሱት ምድረ ገነት ሽረዎች ወደ ሊጉ አናት ሊያስጠጋቸው የሚችል ድል ለማግኘት ዛሬ የጣና ሞገዶቹን ይገጥማሉ። በ4ኛው እና 5ኛው ሳምንት ላይ በፋሲል ከነማና ሲዳማ ቡና ከገጠመው ተከታታይ ሽንፈን በኋላ በመጨረሻዎቹ አራት መርሐ-ግብሮች ሽንፈት ያልቀመሰው ቡድኑ ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ የነበረው ጨዋታን የመቆጣጠር ድክመት እና በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የነበረው ውስን የትኩረት ማነስ ችግር መቅረፍ ይኖርበታል።

ባደረጓቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች ሦስት ሦስት ጊዜ ሦስቱም የውጤት ዓይነቶች አስመዝግበው በ አስራ ሁለት ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህርዳር ከተማዎች በአንድ ነጥብ ከፍ ብሎ የተቀመጠውን የዛሬ ተጋጣሚያቸውን ማሸነፍ የደረጃ መሻሻል ያስገኝላቸዋል። ወደ ሀዋሳ ከተማ ካመሩ በኋላ ባከናወኗቸው አራት ጨዋታዎች ሁለት ድልና ሁለት ሽንፈት ያስተናገዱት የጣና ሞገዶቹ በውጤትም ይሁን በእንቅስቃሴ ረገድ በወጥነት መዝለቅ ካልቻለው አካሄድ መላቀቅ ይጠበቅባቸዋል። ይህ እንዲሆንም በመጀመርያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች በማስቆጠር ዓመቱን በጥሩ ብቃት ከጀመረ በኋላ ቀጥለው በተካሄዱ ሰባት መርሐ-ግብሮች ላይ አምስት ግቦችን ብቻ ያስቆጠረውን የማጥቃት አጨዋወታቸው ማሻሻል ይኖርባቸዋል።

ምድረ ገነት ሽረዎች በዛሬው ጨዋታ ክፍሎም ገብረህይወት እና ኤቢሳ ከድርን በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም፤ ባህርዳር ከተማዎች ግን ከጉዳትም ሆነ ከቅጣት ነፃ የሆነ ስብስብ ይዘው ይቀርባሉ።

የተሰረዘው የ2012 ጨዋታ ሳይጨምር በሊጉ 4 ጊዜ የተገናኙት ቡድኖቹ ባህርዳር ከተማ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ድል ሲያደርግ ምድረ ገነት ሽረ አንድ ጨዋታ አሸንፎ በተቀረው አንድ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ ባህር ዳር ከተማ 4 ግቦች ሲያስቆጥር ስሑል ሽረ 1 አስቆጥሯል።

መቐለ 70 እንደርታ ከ ሀድያ ሆሳዕና

በአራት ነጥቦች በሊጉ ግርጌ የተቀመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች በውድድር ዓመቱ ድል ማድረግ አልቻሉም። ሀድያ ሆሳዕናን በሚገጥሙበት የዛሬው ጨዋታም የዓመቱ የመጀመርያ ድል ለማግኘት ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። በኢትዮጵያ ዋንጫ ኢትዮጵያ ቡናን አንድ ለባዶ በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍፃሜው መሻገር የቻለው ቡድኑ ድሉ በዛሬው ጨዋታ በተለየ ተነሳሽነት እንዲቀርብ ያስችለዋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ሙሉ ነጥብ ይዞ ለመውጣት ግን ዘርፈ ብዙ ለውጦች ማድረግ ይጠበቅበታል።  በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ጥቂት የግብ ዕድሎች የፈጠረው የማጥቃት አጨዋወት ማሻሻል እንዲሁም ከሚስተዋልበት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የማጠናቀቅ አባዜ መላቀቅ ይኖርበታል።

አንድ ድል እንዲሁም በእኩሌታ አራት አራት ሽንፈቶች እና የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ በሰባት ነጥብ 17ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀድያ ሆሳዕናዎች የውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ድላቸውን ለማስመዝገብ ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በኢትዮጵያ ቡናና ነገሌ አርሲ ተከታታይ ሽንፈት የገጠማቸው ነብሮቹ ካሉበት የስጋት ቀጠና ለመውጣት ድል ማድረግ አስፈላጊያቸው ነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ ጥራት ያላቸውን ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ያላቸውን ድክመት መቅረፍ ይኖርባቸዋል። ቡድኑ ተከታታይ ሽንፈት ባስተናገደባቸው ጨዋታዎች ጭምር ከተጋጣሚው ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችልም በፈጠራው በኩል ያለው ውስንነት ግን ከጨዋታዎቹን ነጥብ እንዳያገኝ አድርጎታል።

መቐለ 70 እንደርታዎች ጊትጋት ኮች በህመም ፣ ዮሐንስ ዓፈራ ደግሞ በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም። የዘርኢሰናይ ብርሃነ እና ሱሌይማን ሐሚድ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው። በሀዲያ ሆሳዕና በኩል የግብ ጠባቂው ኦውሱ አንድሪውስ እና የተከላካዩ ዳግም ንጉሤ መሰለፍ  አጠራጣሪ ሲሆን ሄኖክ አርፊጮ ከጉዳቱ አገግሞ የዛሬን ጨዋታ ለማድረግ የአሰልጣኝ ቡድኑን ውሳኔ ብቻ ይጠብቃል።

ቡድኖቹ በሊጉ 4 ጊዜ ተገናኝተዋል፤ ምዓም አናብስቱ በ 3 ድል ሲቀናቸው ነብሮቹ 1 ጨዋታ አሸንፈዋል። መቐለ 70 እንደርታ 5 ግቦች ሲያስቆጥር ሀድያ ሆሳዕና 2 አስቆጥሯል።