ዛሬ በይፋ ልምምዱን የጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሁናዊ ሁኔታ አስመልክቶ የተጠናከረ ዘገባ

በ2027 አፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ ከሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ጋር ለሚያደርጋቸው የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ፌዴሬሽኑ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ ለ2 ዓመታት የውል ጊዜ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ሲሾም ከቀናት በፊት ደግሞ አሰልጣኙ አብረዋቸው እንዲሰሩ አሰልጣኝ በለጠ ገብረኪዳን ምክትል እንዲሁም የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ መሐመድ ጀማል ሾመዋል።
ከቀናት በፊት ለ23 የተጫዋች ጥሪ ያደረጉት አሰልጣኙ በዛሬው ዕለት 21 ተጫዋቾችን በመያዝ የመጀመርያ ልምምዳቸውን ከተባለበት ሰዓት አርባ አምስት ደቂቃ ዘግይተው ሲኤሚሲ በሚገኘው በንግድ ባንክ ሜዳ መስራት ጀምሯል። ብሔራዊ ቡድኒ ለቀናት በዚህ መልኩ ዝግጅቱን ሲያደርግ ይቆይና ወደ ሞሮኮ የሚያቀናም ይሆናል።

ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በተያያዘ በኦማን ሊግ ለአል ሸባብ የሚጫወተው ከንዓን ማርክነህ እና በሳውዲ አረቢያ ሁለተኛ ሊግ በአል አረቢያ ስፖርት ክለብ የሚገኘው ጋቶች ፓኖም በዛሬው የመጀመርያው ልምምድ ላይ ሳይሳተፉ ቀርተዋል። ምክንያቱ እንዲሁም መቼ ቡድኑን እንደሚቀላቀሉም ትክክለኛውን ቀን አጣርተናል በተከታይ መረጃ ወደ እናንተ የምናደርስ ይሆናል።
ሌላው ከቡድኑ ጋር በተያያዘ የህክምና ባለሙያ በመሆን ፊዞትራፒስ ብሩክ ደበበ እንዲሁም በስነ ምግብ ባለሙያ ዳንኤል ባሉበት ሲቀጥሉ ይህን ዘገባ እስከ አጠናከርነበት ጊዜ ድረስ ከዚህ ቀደም በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ የነበሩ የአካል ብቃት እና የቪዲዮ አናሊስት ከቡድኑ ጋር እንደማይገኙ አይተናል።
የብሔራዊ ቡድኑን አደረጃጀት ለማዘመን እና ከሚዲያ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ፌዴሬሽኑ ዓለም አቀፍ አሰራርን ለመከተል ከዚህ ቀደም ከነበረው አሰራር በተለየ ሁኔታ የአሰራር ሂደቶችን በፌዴሬሽኑ ገፅ ላይ አስፍሯል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመርያ ጨዋታውን ሳኦቶሜ የሜዳ ጨዋታዋን ለማድረግ በመረጠችው ሞሮኮ ኤል አብዲ ስታዲየም መጋቢት 18 ከምሽቱ 1፡00 የሚካሄድ ሲሆን የመልሱ ጨዋታ ደግሞ በድሬዳዋ ስታዲየም መጋቢት 22 ከቀኑ 10፡00 ላይ ይከናወናል።
ከብዘሔራዊ ቡድኑ ጋር የተያያዘ መረጃ በቀጣይ ይዘን እንመለሳለን።

