“ይህ ትውልድ ብሔራዊ ቡድኑ ከ11 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የደረሰበትን ከባድ ሽንፈት ቀይሮ..”

በ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ውድድር
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የምትጫወተውን ሳኦቶሜ ፕሪንሲፔን በማሰልጠን ላይ የሚገኙት ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ሪካርዶ ሞንሳንቶ ከጨዋታው በፊት ስለ ተጋጣሚያቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ያተኮረ ቆይታ አድርገዋል።
አሰልጣኙ ከጆርናል ዴስፖርቲቮ የተባለ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሐን ባደረጉት ቆይታ ላይ ቡድናቸው ከኢትዮጵያ ጋር ለሚደርገው ጨዋታ በከፍተኛ የራስ መተማመን እና ቁርጠኝነት እየተዘጋጀ እንዳለ በመግለፅ ብሔራዊ ቡድኑ ወደ 2027 የአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ህልም እንዳለውም ጠቅሰዋል።
ከላይቤሪያ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ ጋር ባደረጓቸው ጨዋታዎች የተመዘገቡ ጥሩ ውጤቶች እንዲሁም ታሪካዊ ብለው የጠቀሱት ማላዊን ያሸነፉበት ጨዋታ ተደማምረው የቡድኑን በራስ መተማመን ከፍ እንዳደረገው የገለፁት አሰልጣኙ የአሰልጣኞች ቡድን አባላት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የቅርብ ጊዜ ጨዋታዎች እንደተመለከተ በመግለፅ በሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል ስላለው ታሪክም የሚከተለውን ብለዋል፤ ” ከ11 ዓመታት በፊት በብሔራዊ ስታዲየም ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ 1 ለ 0 አሸንፋ ነበር፤ ነገር ግን ከሜዳ ውጭ በተካሄደ ጨዋታ 3 ለ 0 ተሸንፋ ከውድድሩ ውጭ ሆናለች ፤ ሆኖም አሁን ያለው ሁኔታ የተለየ ነው” ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።
እንደ አሰልጣኙ ገለፃ “የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ11 ዓመታት በፊት ከነበረበት የበለጠ ጠንካራ ነው፣ ሆናም ብሔራዊ ቡድናችንም በጣም ጠንካራ ነው፤ ይህ በወጣቶች የተገነባ ቡድን በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ እና አወንታዊ ጉዞ በማድረግ ላይ እንዳለ ይሰማኛል” ብለዋል። አሰልጣኙ “የጥሎ ማለፍ ውድድሩ የሚወሰንው በሁለቱ ጨዋታዎች ነው፤ እነዚህ ጨዋታዎች ከ180 ደቂቃ ውጊያ ጋር እኩል ናቸው” የሚል ሃሳብ የሰጡ ሲሆን በማስቀጠልም ” የድሬዳዋ ስታዲየም ከአምስት ዓመታት እገዳ በኋላ ፍቃድ ማግኘቱ አስገርሞናል ይህም የሁለተኛውን ጨዋታ ሁኔታ ይቀይረዋል” ብለዋል።
በመጨረሻም “ማላዊ ላይ የተቀዳጀነው ታሪካዊ ድል ሊደገም እንደሚችል ማመን አለባቹህ፤ ይህ ትውልድ ብሔራዊ ቡድኑ ከ11 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የደረሰበትን ከባድ ሽንፈት ቀይሮ ለቀጣይ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያዎች ለመድረስ ብርቱ ፍልሚያ የማድረግ ፍላጎት አለው” ሲሉ በአፅንዖት ተናግረዋል።

