የጨዋታ ሪፖርት | የአማራ ደርቢ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

በ5ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መልካ ቆሌ ላይ የተካሄደው የአማራ ደርቢ ያለ ግብ ተጠናቋል፡፡ ጨዋታው ከወትሮው የተለየ የተመልካች ብዛት እና የሞቀ የደጋፊዎች ድባብ ተስተናግዶበት አልፏል፡፡

ከጨዋታው  መጀመር አስቀድሞ የወልድያ ደጋፊዎች ለፋሲል ከተማ ደጋፊዎች የእንኳህ ደህና መጣችሁ መልእክት ያለው ባነር እና ስጦታ አበርክተውላቸዋል። በመቀጠል በዚህ ሳምንት ከዚህ አለም በሞት ለተለየው የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ዘላለም ተሾመ የ1 ደቂቃ የህሊና ጸሎት በማድረግ ጨዋታው ተጀምሯል፡፡

በሁለቱም በኩል የሚቆራረጡ ቅብብሎች እና ወጥ ያልሆነ እንቅስቃሴ በታየበት ጨዋታ እንግዶቹ ፋሲሎች የእንቅስቃሴ እና የጎል ሙከራዎች ብልጫ ወስደዋል፡፡

የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ ወልድያዎች ሲያደርጉ አንዱአለም ንጉሴ ከሳጥን ውጭ መሬት ለመሬት የመታው ኳስ በጎሉ ቋሚ ለጥቂት ወጥቷል፡፡ ፋሲሎች ደግሞ በ9 ደቂቃ በኤዶም ሆሮሶዎቪ አማካኝነት የመጀመርያውን ኢላማ የጠበቀ ሙከራ ሲያደርጉ ከ2 ደቂቃዎች በኋላ ኤዶም በድጋሚ በግንባሩ የሞከራትን አደገኛ ኳስ በጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ቢሌንጌ ኢኖህ አድኖበታል።

በ14ኛው ደቂቃ ታዬ አስማረ በግሩም ሁኔታ ያመቻቸውን መልካም የግብ ማስቆጠር አጋጣሚ አንዱአለም ንጉሴ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በ20 ደቂቃ ኤዶም ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታውን ኳስ ቢሌንጌ ሲያወጣበት በ28ኛው ደቂቃ አብዱራህማን ሙባረክ በመስመር በኩል ይዞ በመግባት የሞከረውኝ ኳስ በተመሳሳይ ቢሌንጌ አድኖታል።

በሁለተኛው አጋማሽ ወልድያዎች ከፋሲል ወደ ጎል በመድረስ ተሽለው የታዩ ሲሆን በአንፃሩ ፋሲል ከተማዎች እንደ መጀመሪያው አጋማሽ አስደንጋጭ ሙከራዎችን ማድረግ አልቻሉም። ወልድያዎችም የሜዳው 3ኛ ክፍል ላይ ሲደርሱ የውህደት እና የአጨራረስ ችግር ታይቶባቸዋል።

ከእረፍት መልስ ተቀይሮ የገባው በድሩ ኑርሁሴን በ70ኛው ደቂቃ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ሳይጠቀምባት የቀረው ኳስ ወልድዎችን የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች፡፡

ጨዋታው ከእረፍት በፊት በፋሲሎች ጥሩ እንቅስቃሴ ከእረፍት በኋላ በወልድያዎች ተሽሎ መገኘት የተጠናቀቀ ሲሆን በአጠቃላይ በሁለቱም በኩል ወጥ ያልሆነ እና ተመልካችን ያላረካ በርካታ የቢጫ ካርድ የተመዘዘበት እንዲሁም ሊመሰገን እና ሊቀጥል የሚገባው የደጋፊዎች ስፖርታዊ ጨዋነት ተስተውሎበታል።

ፎቶ – የወልድያ ፌስቡክ ገፅ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *