በ7ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና ድሬዳዋ ከተማን አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ አስተናግዶ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡
በ10፡00 ሰአት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በዚህ ሳምንት እንደተከናወኑት ሌሎች ጨዋታዎች ሁሉ ከትላንት በስቲያ ንጋት ላይ ከዚህ አለም በሞት ለተለየው ጀግናው አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጥር የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ ነበር፡፡
ከጨዋታው መጀመሪያ ጀምሮ ድሬዳዋ ከተማ ፍፁም በመከላከል ላይ ያተኮረ አጨዋወትን በመምረጥ ከኳስ ፊት አጥቂያቸውን ሀብታሙ ወልዴን ብቻ በማስቀረት ቀሪዎቹ ተጫዋቾች ከኳስ ጀርባ ሁለት የመከላከል አጥር ሠርተው ሲከላከሉ ተመልክተናል፡፡
በዚህም የመጀመሪያው አጋማሽ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ሙሉ በሙሉ በሚያስብል መልኩ የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን መውሰድ ቢችሉም ሜዳውን ወደ ጎን በመለጠጥ የተጠቀጠቀውን የድሬዳዋ ተከላካይ ለማስከፈት ከመሞከር ይልቅ አጥብበው በመጫወታቸው ይህ ነው የሚባል የግብ እድል ለመፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በ6ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጲያ ቡናዎች ሳዲቅ ሴቾ ከአማኑኤል ዮሀንስ ተቀብሎ የሞከራት እና ግብ ጠባቂው ሳምሶን አሰፋ በአስገራሚ ሆኔታ ካዳነበት ኳስ በስተቀር አብዛኛዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ የኢትዮጲያ ቡና ሙከራዎች የተደረጉት ከቆመ ኳስ ከሚሻሙ ኳሶች ነበር፡፡
በአንጻሩ ወደራሳቸው ግብ ክልል በጥልቀት ተስበው ሲከላከሉ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በቀኝ ተከላካያቸው ሄኖክ አዱኛ እና በረከት ይስሀቅን ፍጥነት በመጠቀም የመልሶ ማጥቃት ለመሰንዘር ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡ በድሬዳዋዎች በኩል በ19ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አዱኛ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ሀብታሙ ወልዴ የሸረፈውን ኳስ በረከት ይስሃቅ በመቀስ ምት የሞከራትና የግቡ ቋሚ ለትማ የተመለሰችው ኳስ የምታስቆጭ ነበረች፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ በአንጻራዊነት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከመጀመሪያው በተሻለ ጥሩ ጥሩ የግብ እድሎችን መፍጠር ችለዋል፤ ለዚህም እንደ ምክንያትነት ሊቀርብ የሚችለው ቡድኑን በቀኝ መስመር ተከላካይነት አብዱልከሪም መሀመድን ተክቶ የገባው ሳላምላክ ተገኝ በማጥቃቱ በኩል በይበልጥ ወደ ቀኝ ለጥጦ የድሬዳዋ ተከላካዮች ወደ ጎላቸው በመሳባቸው የሚፈጠረውን ክፍተት ሲጠቀም ተስተውሏል፡፡
ከመጀመሪያው በተሻለ ጫና ፈጥረው ለመጫወት የሞከሩት ቡናዎች በተለይም በ71ኛው እና 71ኛው ደቂቃ ላይ ሳላምላክ ተገኝ ከቀኝ መስመር ወደ መሀል ያሻማውን ኳስ ያቡን ዊልያም እንዲሁም ሳሙኤል ሳኑሚ ገጭተው ግብ ለማስቀጠር ቢሞክሩም በጨዋታው ኮከብ የነበረው የድሬዳዋ ከተማው ግብጠባቂ ሳምሶን አሰፋ የሚቀመስ አልሆነም፡፡
በጨዋታው መገባደጃ አካባቢ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ሙሉ ለሙሉ ለማጥቃት መሳባቸውን ተከትሎ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ የተገኘችውን እና ፉአድ ኢብራሂም በግሩም ሆኔታ አመቻችቶ የሰጠውን ለመሳት የሚከብድ የሚመስለውን ኳስ ሀብታሙ ወልዴ በማይታመን መልኩ አምክኗታል፡፡
በተመሳሳይ በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ ቡናዎች ያገኙትን አጋጣሚ ያቡን ዊልያም ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ ጨዋታውም ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተፈጽሟል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በተጫዋቾቻቸው እና የቡድኑ አሰልጣኝ ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
ኒቦሳ ቪሴቪች – ኢትዮጵያ ቡና
“የዛሬው ጨዋታ ከዚህ በፊት እንዳረግናቸው አምስቱ ጨዋታዎች ተመሳሳይ ነበር ፤ በርካታ የግብ እድሎችን መፍጠር ችለን ነበር ፤ ነገር ግን አሁንም ማስቆጠር አልቻልንም፡፡ ጥሩ የሆነ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች ቢኖረን በዚህ አመት ቢያንስ 20 ግብ አስቆጥሮ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ማጠናቀቅ እንደሚችል አምናለሁ፡፡ አሁንም በርካታ የግብ እድሎችን እየፈጠርን እንገኛለን ነገርግን አሁንም ማስቆጠር አልቻልንም፡፡”
“በዛሬው ጨዋታ ላይ እኔ እንኳን ተሰልፌ ብጫወት ሁለት ሶስት ግቦችን ማስቆጠር እችላለሁ፡፡”
“በቀጣዩ ሳምንት ወሳኝ ጨዋታ ይጠብቀናል፡፡ እንደከዚህ ቀደም ስናደርግ እንደነበረው አጥቅተን በመጫወት ለማሸነፍ እንጫወታለን፡፡ በተቻለን አቅም ይህን ጨዋታ ለማሸነፍ እንጫወታለን፡፡ ይህንን ጨዋታ አሸንፈን ደጋፊዎቻችን በማስደስት የእስካሁኑን አስከፊ ጉዞ ለማስረሳት የተቻለንን እንጥራለን፡፡”
ዘላለም ሽፈራው – ድሬዳዋ ከተማ
“መጀመሪያም ወደ ጨዋታው ስንመጣ አስበን የመጣነው በጥብቅ መከላከል እና በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ነበር ፤ ቡድኔን እንደተመለከታችሁት በመከላከሉ በኩል የተዋጣለት ነበር፡፡ ነገርግን ያገኘናቸውን የግብ እድሎች በመጠቀም በኩል አሁንም ክፍተቶች ይስተዋሉብናል፡፡ በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ እርግጥ ነው እነሱም የግብ እድሎችን አግኝተው ነበር ግን ከነሱ በተሻለ በተለይም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አግኝተን ሀብታሙ ወልዴ ሳይጠቀምባት የቀረችው ኳስ ፍፁም የምታስቆጭ ነበር፡፡ እንደ አጠቃላይ ግን የተጫዋቾቼ እንቅስቃሴ ጥሩ የሚባል ነው፡፡”
“ባሳለፍነው ሳምንት በሜዳችን ነጥብ በመጣላችን የተነሳ ይህንን ጨዋታ አሸንፈን በሜዳችን ላይ የጣልነውን ነጥብ ለማካካስ አስበን ነበር፡፡ ከሜዳ ውጪ አንድ ነጥብ ብዙም የሚያስከፋ አይደለም ፤ ነገርግን ማሸነፍ ነበረብን፡፡”