ከስምንተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታዎች መካከል በ09:00 አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በተደረገው ጨዋታ ደደቢት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በጌታነህ ከበደ ሁለት ግቦች ታግዞ 2-1 አሸፏል።
በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ግብ በማግባትም ሆነ በጨዋታ የተሻሉ ሆነው የታዩት ደደቢቶች በ5ው ደቂቃ ነበር የተጋጣሚያቸውን ግብ መፈተሽ የጀመሩት። ይህ የመጀመሪያ ሙከራም ዳዊት ፍቃዱ ከመሀል ሜዳ የተላከለትን ኳስ ወደ ንግድ ባንኮች የግብ ክልል ይዞ በመግባት ከጎሉ ጥቂት ሜትሮች ርቀት ላይ ሞክሮ ኢማኑኤል ፎቮ ሲመልስበት የታየ ነበር። የተመለሰውን ኳስም ኤፍሬም አሻሞ ደግሞ ቢሞክረውም ወደላይ ተነስቶበታል።
ከዚህም በኃላ ደደቢቶች በ12ኛው ደቂቃ ላይ ያገኙትን የማዕዘን ምት ብርሀኑ ቦጋለ ሲያሻማ ሽመክት ጉግሳ በግንባሩ ሞክሮ ከግቡ በላይ ተነስቶበታል። ይህ ከሆነ ከ5 ደቂቃዎች በኃላ ነበር በግራ መስመር ከኤፍሬም አሻሞ የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ የሊጉን የኮከብ ግብ አግቢዎች ፉክክርን እየመራ የሚገኘው ጌታነህ ከበደ ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገው።
በደደቢቶች 1-0 መሪነት ጨዋታው ሲቀጥል ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች የሚሰነዝሩት ጥቃት የደደቢትን ጠንካራ የመከላከል መስመር ማለፍ ተስኖት ታይቷል። ቡድኑ በመጀመርያው አጋማሽ የሞከረውም ብቸኛ ኳስ በ31ኛው ደቂቃ ታድዮስ ወልዴ ከቢንያም በላይ የተሻገረለትን የማዕዘን ምት በግንባሩ ሞክሮ ለጥቂት በግቡ አናት ሲወጣበት ነበር።
ደደቢቶች በበኩላቸው በጌታነህ ከበደ እና በኤፍሬም አሻሞ አማካይነት ሙከራዎችን ሲያከታትሉ ከቆዩ በኃላ በጨዋታው አጋማሽ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ዳዊት ፍቃዱ በቀኝ መስመር ይዞ የገባውን ኳስ ወደግብ ሲሞክር ኳሱ ኢላማውን ሳይጠብቅ ወደውጪ ከመውጣቱ በፊት በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ጌታነህ ከበደ አግኝቶት ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ አድርጓታል። ከዚህች ግብ መቆጠር በኃላም ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ የተጨዋቾች ሚና ሽግሽግ አርገው ወደሜዳ የተመለሱት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል። ቡድኑ ወደጨዋታው ለመመለስም በኳስ ቁጥጥር የተሻለ የበላይነት የወሰደ ሲሆን የተጋጣሚውን የተከላካይ መስመር በእንቅስቃሴ ሰብሮ ለመግባት ግን ከባድ ሆኖበት ታይቷል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከዚህ ጥረታቸው በግራ በኩል በደደቢቶች የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ጠርዝ ላይ ያገኙትን የቅጣት ምት በ63ኛው ደቂቃ ላይ አዲሱ ሰይፉ በቀጥታ መቶ አስቆጥሯል።
በተቀረው የጨዋታ ክፍለጊዜም በግቧ የተነቃቃው የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ቡድን ኳስን መሰረት አርጎ በማጥቃት ወደ አቻነት ለመምጣት ሲጥር ደደቢቶች በበኩላቸው በመልሶ ማጥቃት በተጨማሪ ግብ ውጤቱን ለማስፋት ተንቀሳቅሰዋል። ነገር ግን ጨዋታው በጉሽሚያዎች እና በቢጫ ካርዶች ታጅቦ በተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ ተጠናቋል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
” ተጋጣሚያችን ደደቢት በሁሉም ነገሮች የተሟላ ነው። ከግብ ጠባቂ እስከ አጥቂ ልምድ ያላቸው ፣ በግላቸው ተፅእኖ መፍጠር የሚችሉ እና ከምንም በላይ ደግሞ ሊጉን ከሚመሩ ቡድኖች መካከል የሚገኙ በመሆኑ እና በራስ መተማመናቸው ከፍ ያሉ ተጨዋቾችን የያዘ ቡድን በመሆኑ ጠንከር ብለው ሊገቡ እንደሚችሉ ገምተን ነበር። በአንፃሩ በኛ በኩል ከመጀመሪያ 11 ተሰላፊዎች ውስጥ ፒተርን ፍቅረየሱስን እና አንተነህን ማጣታችን የስኳድ ጥበት እንዳለበት ቡድን ጨዋታው አስቸጋሪ እንደሚሆንብን ገምተን ነበር። ”
” በመጀመሪያው 45 ደቂቃ ጌታነህ በግል ጥረቱ ያገኛቸውን አጋጣሚዎች ተጠቅሞ ሁለት ግቦች አስቆጥሮብናል ። በሁለተኛው አጋማሽም ከፊት መስመር ሁለት አጥቂዎችን እና በግራ በኩል ተፈጥሯዊ የግራ እግር ተጨዋቾችን በመጠቀም እና የተጨዋች ለውጥ በማድረግ ተጭነን በመጫወት ውጤቱን ለማጥበብ ሞክረን ነበር ያው አልተሳካም።”
” በግልፅ ለመናገር ከያዝናቸው 18 ተጨዋቾች በተቀያሪ ወንበር ላይ ከሙሴ በቀር ስድስቱ ከ ተስፋ ቡድን ያደጉ ናቸው።ለኛ ይሄ አመት ከባድ እንደሚሆን ቀደም ብዬም አውቄው ነበር። እነዚህን ወጣት ተጨዋቾች እያስገባን ልምድ እንዲያገኙ ለማድረግ ከመሞከር ውጪ ምንም አማራጭ የለንም። አሁን በሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ሊጀመሩ ነው። ጨዋታዎች እየተደራረቡ በሄዱ ቁጥር ይበልጥ ልንቸገር ስለምንችል ከክለቡ አመራሮች ጋር እየተነጋገርን ነው። ”
አስራት ኃይሌ – ደደቢት
” የዛሬውን ጨዋታ አሸንፌ ወጥቻለው ። ኳስ ያው ማሸነፍ ነው ትልቁ ነገር። መሸነፍ ነው ሚያስጠላው። አሸናፊ ቆንጆ ነው ተሸናፊ አስቀያሚ ነው። ስለዚህ ቆንጆ ሆነን ወተናል አሸንፈን ማለት ነው። ”
” የቡድኑ አደረጃጀት ጥሩ ነው ። ከበረኛ ጀምሮ የማጥቃት አጀማመራችን ጥሩ ነው። ያው እንዳየነው ጥሩ ጥሩ ጎሎች አስቆጥረን አሽንፈናል። ”
” ጌታነህ ብቻውን አይደለም አስራሀንዱን የገጠመው እግር ኳስ ጨዋታ የጊዜና የቦታ ጉዳይ ነው። የጌታነህ ትልቁ ብቃት ራሱን ነፃ አድርጎ ትክክለኛው ቦታ ላይ መገኘቱ ነው ። ነገር ግን ለግቦቹ መገኘት ከበረኛው ጀምሮ አጠገቡ ያሉት ተጨዋቾች ሁሉ አስተዋፅኦ አለው። “