ጋቦን 2017 | ባምላክ ተሰማ የምድብ 2 የመጀመርያ ጨዋታን ይመራል

ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል የመሃል ዳኛ ባምላክ ተሰማ የ2017 ቶታል የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ 2 መክፈቻ ጨዋታ እንዲመራ በካፍ ተመርጧል፡፡

አህጉሪቱ እግርኳስ የበላይ አካል ካፍ ዛሬ የዳኞችን ስም ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡ በውድድሩ ላይ የሚገኘው ብቸኛው ኢትዮጵያዊ አርቢተር ባምላክ በምድብ ሁለት የዋንጫ ከፍተኛ ግምትን ካገኙት ሃገራት መካከል የሆነችውን አልጄሪያ ከዚምባቡዌ ዕሁድ የሚያደርጉትን ጨዋታ ይመራል፡፡ የባምላክ ረዳቶች ሆነው ቡሩንዳዊው ጂያን ክላውድ ቢሩሙሳሁ እና ጊኒያዊው አቡበከር ዶምቦያ በካፍ ተመርጠዋል፡፡ ጨዋታው በፍራንስቪል ከተማ በሚገኘው ፍራንስቪል ስታዲየም ይደረጋል፡፡

ባምላክ በካፍ የዳኞች ደረጃ ኤሊት ኤ ላይ የሚገኝ ሲሆን ኤኳቶሪል ጊኒ ባዘጋጀቸው የ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ጨዋታዎችን በመሃል ዳኝነት እና በአራተኛ ዳኝነት መርቶ ነበር፡፡ በቻን 2016 ጨዋታዎች ማጫወት የቻለው ባምላክ በ2016 በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያዎች፣ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎች እና የኮንፌድሬሽን ዋንጫ ጨዋታዎች መምራት ችሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *