የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ምድብ ሀ የመጀመርያ ዙር ዛሬ በተካሄዱ ጨዋታዎች ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡
የአንደኛው ዙር የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች እሁድ መደረግ የጀመሩ ሲሆን ወደ ድሬዳዋ ያቀናው ደደቢት 4-1 በማሸነፍ 1ኛውን ዙር በ100% ሪኮርድ አጠናቋል፡፡ የአምናው ቻምፒዮን ደደቢት ዘጠኙንም ጨዋታዎች በማሸነፍ በ30 የግብ ልዩነት የምድቡ አናት ላይ የተቀመጠ ሲሆን የአምና ክብሩን በሚያስጠብቅበት አቋም ላይ ይገኛል፡፡
አዳማ ከተማ ወደ አዲስ አበባ አቅንቶ ትላንት ከቦሌ ክፍለ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ 2-0 በማሸነፍ አንደኛውን ዙር በ2ኛ ደረጃነት አጠናቋል፡፡ አዳማ በዘንድሮው የወድድር ዘመን ከፍተኛ መሻሻል በማሳየት ካደረጋቸው 9 ጨዋታዎች 8 በማሸነፍ በጠንካራው ደደቢት ብቻ 1-0 ተረትቶ በ24 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ትላንት በአበበ ቢቂላ ስታድየም በተደረገ ጨዋታ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ጥረት ኮርፖሬትን አስተናግዶ 5-0 ተሸንፏል፡፡ እቴጌ ዘንድሮ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ስር ከተጠቃለለ በኋላ መሻሻል ቢያሳይም በ9 ጨዋታ ያገኘው 1 ነጥብ ብቻ ነው፡፡ በአንፃሩ ሙሉ ቡድኑን ከዳሽን የተረከበው ጥረት ከዚህ ቀደም በነበረው ጠንካራ ተፎካካሪነት በመዝለቅ በደረጃ ሰንጠረዡ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ አጠናቋል፡፡
ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም ኤሌክትሪክ ከ መከላከያ ያደረጉት ጨዋታ በኤሌክትሪክ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ጠንካራ ተመልካችን ቁጭ ብድግ ያደረገ እንቅስቃሴ በታየበት በዚህ ጨዋታ ኤሌክትሪክ የግብ ጠባቂዋ ማርታ በቀለን ስህተት ተጠቅሞ በፅዮን ፈየራ ግብ ቀዳሚ ሲሆን መከላከያ በሄለን አሸቱ ግብ አቻ በመሆን ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
ከእረፍት መልስ መከላከያ ሙሉ ለሙሉ ብልጫ ቢያሳይም የተደራጀውን የኤሌክትሪክ የተከላካይ መስመር መስበር ሳይችለል ቀርቷል፡፡ በመልሶ ማጥቃት ሲጫወቱ የነበሩት ኤሌክትሪኮች ማርታ በቀለ በድጋሚ የሰራችውን ስህተት ተጠቅመው በጤናዬ ወመሴ ግብ ከጠንካራው መከላከያ 3 ነጥብ መንጠቅ ችለዋል፡፡
አምና ታላላቆቹን ክለቦች ሳይቀር በመፈተን ጠንካራ ተፎካካሪ የነበረው መከላከያ ዘንድሮ ተቀዛቅዟል፡፡
በምድብ ሀ 1ኛ ዙር የመጨረሻ በሆነው ጨዋታ ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ከ ኢትዮጵያ ቡና 11:30 ላይ ተገናኝተው አካዳሚ በድንቅ እንቅስቃሴ 2-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡
የምድብ ሀ 9ኛ ሳምንት ውጤቶች
የደረጃ ሰንጠረዥ
የምድብ ለ 9ኛ ሳምንት ከእሁድ ጀምሮ የሚካሄዱ ሲሆን ሲዳማ ቡና እና አዲስ አበባ ከተማ በመጀመርያዎቹ 3 ተከታታይ ጨዋታዎች ያላደረጓቸው ተስተካካይ ጨዋታዎች ተካሂደው ጥር 29 የመጀመርያው ዙር ይጠናቀቃሉ፡፡
የምድብ ለ 9ኛ ሳምንት ፕሮግራም
የደረጃ ሰንጠረዥ
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ምድብ ሀ 1ኛ ዙር መጠናቀቁን በማስመልከት ስለ አንደኛው ዙር ፣ ስለ ቡድኖቹ እና ምርጥ አቋማቸውን ስላሳዩ ተጫዋቾች እንዲሁም የጎል እና የዲሲፕሊን ሪኮርዶችን አካተን ሰፋ ያለ ፅሁፍ በዚህ ሳምንት እንደምናስነብብ ከወዲሁ እንገልጻለን፡፡
በድረገፁ የሚወጡ ፅሁፎች ምንጭ ካልጠቀስን በቀር ሙሉ ለሙሉ የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ ፅሁፎቹን ለራስዎ ፕሮግራም /ፅሁፍ ሲጠቀሙ ምንጭ ጠቅሰው ይጠቀሙ፡፡