ከፍተኛ ሊግ | ባህርዳር መሪነቱን አጠናክሯል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ከተቋረጠበት የቀጠለ ጨዋታን ጨምሮ ሶስት ጨዋታዎች ተካሂደው ባህርዳር ከተማ መሪነቱን ያሰፋበትን ድል አሳክቷል።

በምድብ ሀ 20ኛው ሳምንት ደሴ ስታድየም ላይ እየተደረገ የተቋረጠው ጨዋታ ዛሬ በኦሜድላ ቀጥሎ ፍፃሜውን አግኝቷል። ጨዋታው ከመቋረጡ በፊት እስከ እረፍት መጫወት ችለው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን በ43ኛው ደቂቃ ፍቃዱ ወርቁ ባስቆጠረው ጎል ባህርዳር ከተማ እየመራ ነበር በፀጥታ ጉዳዮች ምክንያት የተቋረጠው። ዛሬ 4:40 ላይ በኦሜድላ ሜዳ ከተቋረጠበት የተጀመረው ጨዋታ ከሜዳው ጭቃማነት አንፃር ኳስን ሆነ ተጫዋቹችን እንደልብ የማያንቀሳቅስ ነበር። ውጤቱን ለማስጠበቅ በሚመስል መልኩ ባህርዳሮች ወደ አፍግፍገው የተጫወቱ ሲሆን ከፊት መስመር ሙሉቀን ብቻ በማስቆም አልፎ አልፎ ፍቃዱ በቀኝ መስመር ይዞት ከገባው ውጭ አብዘኛውን ተጨዋች በራሱ የግብ ክልል ላይ ተገድቦ መከላከልን ምርጫው አድረገው ነበር። 


በ56ኛው ደቂቃ እና በ69ኛው ደቂቃ ሙሉቀን የሞከረው እንዲሁም ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሀብታሙ ንጉሴ የሞከሩት በባህርዳር በኩል ተጠቃሽ ነው። በተቃራኒው ደሴ ከተማ ውጤቱን ለመለወጥ የጣሩ ቢሆንም መረጋጋት ግን ተስኗቸው ተስተውሏል። በተደጋጋሚ ከመስመር የሚያሻግሯቸውን ኳሶች በግንባር ለመጠቀም የሞከሩት ደሴዎች በአጥቂቸው ቢንያም ጌታቸው ሲፈጠሩት የነበሩት ጫና ከፍተኛ የነበረ ቢሆንም ከባህርዳር የመከላከል ጥንካሬ ጋር ተደምሮ ጥረታቸው ፍሬ ሳያፈራ ቀርቷል። ጨዋታውም ከመቋረጡ በፊት በተቆጠረው ብቸኛ ጎል አማካኝነት በባህርዳር 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ባህርዳር በድሉ ተጠቅሞ ከተከታዩ ሽረ እንዳሥላሴ ያለውን ልዩነት ወደ 8 ከፍ ማድረግም ችሏል። 

በምድብ ሀ 24ኛ ሳምንት ዛሬ ረፋድ የተከናወነው ሌላው ጨዋታ በነቀምት ከተማ እና አውስኮድ መካከል ተከናውኖ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል። በምድብ ለ የ23ኛ ሳምንት በዝናብ ምክንያት ከትላንት ወደ ዛሬ የተሸጋገረውና ቡታጅራ ላይ የተካሄደው የወልቂጤ ከተማ እና ዲላ ከተማ ጨዋታ 2-2 ተጠናቋል። ለወልቂጤ ከተማ ጌታሁን ባፋአ እና አክሊሉ ተፈሪ ሲያስቆጥሩ በተከታታይ ጎሎች እያስቆጠረ የሚገኘው ኄኖክ አየለ እና ሐብታሙ ፍቃዱ የዲላን ጎሎች አስቆጥረዋል።