ዋሊያዎቹ ለመልሱ ጨዋታ ድሬዳዋ ላይ ልምምድ ጀምረዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከጅቡቲ ጋር ለሚያደርገው የቻን ማጣርያ የመልስ ጨዋታ ድሬዳዋ ላይ የመጀመርያ ቀን ልምምዱን አከናውኗል።

በአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) ቅድመ ማጣርያ ከጅቡቲ ብሔራዊ ቡድን ጋር ጨዋታ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመርያ ጨዋታውን ጅቡቲ ላይ በአስቻለው ታመነ ብቸኛ የፍ/ቅ/ምት ጎል 1-0 በማሸነፍ መመለሱ ይታወሳል። ከጅቡቲ መልስ ወደ ድሬዳዋ ያቀናው ቡድኑ ዛሬ ዝግጅቱን ሲጀምር በጠዋቱ መርሐግብር የብሔራዊ ቡድኑ አባላት በድሬዳዋ ከተማ ከአርቲስቶች እና የተለያዩ አካላት ጋር በጋራ ችግኝ በመትከል አመሻሹን በድሬዳዋ ስታዲየም በመገኘት የዕለቱን ልምምዳቸውን አከናውነዋል።

ለአንድ ሰዓት በቆየው ጠንከር ያለ ልምምዳቸው ሙጂብ ቃሲም (ፋሲል ከነማ)፣ መስፍን ታፈሰ (ሀዋሳ ከተማ) እና ረመዳን ናስር (ድሬዳዋ ከተማ) ብሔራዊ ቡድኑን የተቀላቀሉ አዲስ ተጫዋቾች ሲሆኑ አቤል ያለው እና አቡበከር ናስር በጉዳት ምክንያት በዛሬው ልምምድ ያልተገኙ ተጫዋቾች ሆነዋል።

ተጋጣሚው የጅቡቲ ብሔራዊ ቡድን ቅዳሜ በባቡር ተጉዞ ድሬዳዋ የገባ ሲሆን ዛሬ 18 ተጫዋቾችን በመያዝ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ልምምድ በሰራበት ተመሳሳይ ሰዓት በሌላ ሜዳ ልምምዱን ሰርቷል።

በጅቡቲ ስብስብ ውስጥ ሁለት አስቀድመው ድሬዳዋ ላይ ይጫወቱ የነበሩ አብዲ መሐመድ እና መሐመድ ሙሐመድ የተባሉ ተጫዋቾች ይገኛሉ። አብዲ መሐመድ ከአሰልጣኝ መሠረት ማኒ የአሰልጣኝነት ዘመን ጀምሮ ከ2008-2010 ድረስ ለሦስት ዓመት በድሬዳዋ ከተማ ዋናው ቡድን በቢጫ ቲሴራ ያገለግል የነበረ ሲሆን የመሰለፍ እድል በማጣቱ በአሁኑ ወቀት የጅቡቲ ብሔራዊ ቡድን ቁልፍ ተጫዋች በመሆን እያገለገለ ይገኛል። መሐመድ መሐሙድ ደግሞ በናሽናል ሲሜንት እና በድሬዳዋ ፖሊስ መጫወት ችሏል። በ2011 የውድድር ጅማሮ ወቅት በአሰልጣኝ ዮሐንሳሌ ሳህሌ የሙከራ ዕድል እንዲያገኝ ከዋናው ቡድን ጋር በመሆን ለዝግጅት በባህር ዳር እና በመቐለ ከቡድኑ ጋር ቢቆይም አሰልጣኙን ማሳመን ባለመቻሉ በመቀነሱ ወደ የጅቡቲ በማቅናት በአሁኑ ወቅት የብሔራዊ ቡድን ዋሳኝ ተጫዋች እንደሆነ ለማወቅ ችለናል።

የኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ብሔራዊ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ ድሬዳዋ ላይ እሁድ ሐምሌ 28 ቀን 10:00 ላይ የሚካሄድ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡