የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ሳምንት ሲጠቃለል

የ2012 የውድድር ዘመን ከቅዳሜ እስከ ረቡዕ በተደረጉ አራት ጨዋታዎች ተጀምሯል። በሊጉ ዙርያ የተመዘገቡ ቁጥራዊ መረጃዎች ፣ እውነታዎች፣ የትኩረት ነጥቦች እና የ2ኛው ሳምንት መርሐ ግብር እንደሚከተለው አሰናድተናል።

የውድድር ዘመኑ በ12 ክለቦች እንደሚጀመር ቢጠበቅም በተለያዩ ምክንያቶች በ11 ክለቦች እየተካሄደ ይገኛል። በዚህም በየሳምቱ አንድ አራፊ ቡድን የሚኖር ሲሆን በአንደኛው ሳምንትም አዲስ አዳጊው መቐለ 70 እንደርታ አራፊ ሆኗል። በተመሳሳይ አምስት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ ተብሎ ቢጠበቅም ኢትዮ-ኤሌክትሪክ እገዳ ላይ በመሆኑ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ሊያደርገው የነበረው ጨዋታ ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል

ቅዳሜ ዲላ ላይ በጌዴኦ ዲላ እና አርባምንጭ ከተማ መካከል በተደረገውና ያለ ጎል በተጠናቀቀው የመክፈቻ ጨዋታ የተጀመረው ሊጉ በቀጣዩ ቀን አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1-1 በተለያዩበት ጨዋታ ቀጥሎ ማክሰኞ አቃቂ ቃሊቲ ከ ሀዋሳ በተመሳሳይ 1-1 ተያይተው ረቡዕ መከላከያ አዲስ አበባ ከተማን 3-0 በረታበት ጨዋታ ተደምድሟል።

የመጀመርያዎቹ

ጎል | የውድድሩ የመጀመርያ ጎል የተቆጠረው በኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ሽታዬ ሲሳይ ነው። እሁድ አዳማ ላይ ከአዳማ ከተማ ጋር በተደረገው ጨዋታ 38ኛው ደቂቃ ላይ ነበር ሽታዬ ያስቆጠረችው።

ሐት-ትሪክ | የመከላከያዋ አጥቂ ሔለን እሸቱ የዓመቱን የመጀመርያ ሐት-ትሪክ አስመዝግባለች። ተጫዋቿ አዲስ አበባ ከተማን 3-0 በረቱበት ጨዋታ ነው በ54ኛው፣ 55ኛው እና 60ኛው (ፍ/ቅ/ም) ጎሎቹን ያስቆጠረችው።

ፍፁም ቅጣት ምት | የአዳማ ከተማዋ አዲስ ፈራሚ ምርቃት ፈለቀ ቡድኗ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አቻ በተለያየበት ጨዋታ በ62ኛው ደቂቃ ባስቆጠረችው ጎል የመጀመርያዋ ፍ/ቅ/ም አስቆጣሪ ሆናለች።

– ቢጫ ካርድ | የአርባምንጭ ከተማዋ ትዕግስት ኢላላ የውድድር ዘመኑ የመጀመርያ የማስጠንቀቂያ ካርድ የተመዘዘባት ተጫዋች ሆናለች። ተጫዋቿ ቡድኗ ከጌዴኦ ዲላ ጋር ባደረገው የውድድር ዓመቱ የመክፈቻ ጨዋታ ላይ በ75ኛው ደቂቃ በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ አስናቀች ገብሬ ነው ቢጫ ካርድ የተመለከተችው።

ቁጥራዊ መረጃዎች

– በአራት ጨዋታዎች ሰባት ጎሎች ሲቆጠሩ መከላከያ በሦስት ጎሎች ከፍተኛ ነው።

– ከሰባቱ ጎሎች አምስቱ በክፍት ጨዋታ ሲቆጠሩ ሁለት ጎሎች በፍፁም ቅጣት ምት ተቆጥረዋል።

– ሰባቱ ጎሎች በአምስት የተለያዩ ተጫዋቾች ተቆጥረዋል።

– በአራቱ ጨዋታዎች በአጠቃላይ 9 የማስጠንቀቂያ ካርዶች ሲመዘዙ ምንም ቀይ ካርድ አልተመዘዘም።

የትኩረት ነጥቦች

– ባለፉት ዓመታት በስታዲየሙ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው ጠብታ አምቡላንስ ባልታወቀ ምክንየች በወንዶቹም በሴቶቹም ጨዋታዎች ላይ አገልግሎት ሲሰጥ አልታየም። ለጉዳት ተጋላጭ በሆነው የሴቶች እግርኳስ፤ በአመዛኞቹ ቡድኖች የህክምና ቡድን እጥረት ከመኖሩ ጋር ተጨምሮ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል።

– የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ለዓመታት ክፍት ቀን እና ቦታ በሚገኝበት ወቅት ሲደረግ ቆይቷል። በተለይም የወንዶች ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ 11:00 ላይ በሚኖርበት ወቅት ቀደም ብሎ 9:00 ሲደረግ የቆየ ሲሆን በዚህ ሳምንት የተደረጉ ጨዋታዎች ግን ቀደም ብለው 8:00 እንዲከናወን ተደርጓል። በሰዓቱ ከሚኖረው ሞቃታማ አየር ጋር በተያያዘ ለእንቅስቃሴ አስቸጋሪ መሆኑ በአሉታዊ ጎኑ የሚጠቀስ ሲሆን በሁለት የተለያዩ ጨዋታዎች መካከል የደቂቃዎች ፋታ እንዲኖር ማድረጉ ደግሞ በጥሩ ጎኑ ሊነሳ የሚችል ነው።

– የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ራሱን የቻለ ውድድር እንደመሆኑ የራሱ ተመልካቾች ያለው ሊግ ነው። ሆኖም ከወንዶች ፕሪምየር ሊግ ጋር በተመሳሳይ ቀን በሚደረግበት ወቅት የሴቶቹን ፕሪምየር ሊግ ለመመልከት ብቻ የሚመጡ ተመልካቾች ሲስተናገዱ አይስተዋልም። የስታዲየም በሮች ለወንዶች ፕሪምየር ሊግ ተመልካች ክፍት እስኪደረጉ ድረስም የሴቶቹ ጨዋታዎች ተመልካች አልባ ሲሆኑ ይስተዋላል። ይህም ችግር ትኩረት ተሰጥቶት ሊቀረፍ የሚገባ ጉዳይ ነው።

– የጨዋታ መርሐ ግብር በአወዳዳሪው አካል በአግባቡ እየተገለፁ አይገኙም። በአንደኛው ሳምንት ከየክለቡ መረጃ ካልተገኘ በቀር ይፋዊ የውድድር ቀን፣ ሰዓት እና ቦታን የሚገልፅ መርሐ ግብር በፌዴሬሽኑ አልተገለፀም። ይህ ደግሞ ለሚድያ አካላትም ሆነ ለተመልካች ለመከታተል አመቺ እንዳይሆን አድርጎታል። በተለይም የቦታ እና ሰዓት ለውጦች ሲደረጉ በፍጥነት ማሳወቅ ላይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

የሁለተኛ ሳምንት መርሐ ግብር

እሁድ ታኅሳስ 5 ቀን 2012

09፡00 ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪከ (ሀዋሳ)

09፡00 አርባምንጭ ከተማ ከ አዳማ ከተማ (አርባምንጭ)

ማክሰኞ ታኅሳስ 7 ቀን 2012

09፡00 መቐለ 70 እንደርታ ከ መከላከያ (መቐለ)

10፡00 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ አቃቂ ቃሊቲ (ባንክ ሜዳ)

10፡00 አዲስ አበባ ከተማ ከ ጌዴኦ ዲላ (አአ ስታድየም)

አራፊ ቡድን – ድሬዳዋ ከተማ

 


© ሶከር ኢትዮጵያ