የፕሪምየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት ቁጥሮች እና እውነታዎች

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንትን የተመለከቱ ቁጥራዊ መረጃዎች እና እውነታዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ጎሎች በቁጥራዊ መረጃ

– በአምስተኛ ሳምንት በአጠቃላይ 22 ጎሎች ተቆጥረዋል። ይህም በ2ኛው ሳምንት ጋር በጋራ ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል። 

– በዚህ ሳምንት በሁሉም ጨዋታዎች ላይ ጎሎች ተቆጥረዋል። (ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ ነው)

-በዚሀ ሳምንት ጎል ሳያስቆጥሩ የወጡ ቡድኖች 3 ብቻ ሲሆኑ ይህም ሊጉ ከተጀመረ ወዲህ ዝቅተኛው ነው። ጎል ያላስቆጠሩ ሦስቱም ቡድኖች የተጫወቱት በሜዳቸው ነው።

– በዚህ ሳምንት 20 ተጫዋቾች ጎል በማስቆጠር ተሳትፈዋል። የዘንድሮው ሊግ ከተጀመረ ወዲህም ከፍተኛ የጎል አስቆጣሪዎች ቁጥር ነው።

– ጎል ካስቆጠሩ 22 ተጫዋቾች መካከል 15 ጎሎች በአጥቂ (የመሐል እና የመስመር) ተጫዋቾች ሲቆጠሩ 6 ጎሎች በአማካይ ሥፍራ ተጫዋቾች ተቆጥሯል። 1 ጎሎች ደግሞ በተከላካይ ሥፍራ ተጫዋች ተቆጥሯል።

– ሙጂብ ቃሲም እና ጌታነህ ከበደ ሁለት ጎሎች በማስቆጠር ከፍተኛውን የጎል ቁጥር ሲያስመዘግቡ ቀሪዎቹ 18 ተጫዋቾች አንድ ጎል አስቆጥረዋል።

– ከ16 ጎሎች መካከል 12 ጎሎች ከክፍት ጨዋታ እና ከተሻሙ ኳሶች (ከቅጣት ምት እና ማዕዘን ምት) ሲቆጠሩ 5 ጎል ከፍፁም ቅጣት ምት፣ 1 ጎል ደግሞ ከቀጥታ ቅጣት ምት የተገኙ ናቸው።

– ከዚህ ሳምንት 22 ጎሎች መካከል 20 በእግር ተመትተው ሲቆጠሩ ሁለት ጎሎች ብቻ በግንባር ተገጭተው ተቆጥረዋል።

– ከ22 ጎሎች መካከል 18 ጎሎች ከሳጥን ውስጥ ተመትተው ሲቆጠሩ 4 ጎሎች ከሳጥን ውጪ ተመትተው ጎል ሆነዋል።


ካርዶች

– በዚህ ሳምንት 31 ቢጫ እና 0 ቀይ ካርዶች ተመዘዋል።

– ስሑል ሽረ፣ ሀዋሳ ከተማ እና አዳማ ከተማ እያንዳንዳቸው 4 ቢጫ ካርዶች በመመልከት ቀዳሚው ናቸው። ኢትዮጵያ ቡና እና ወልዋሎ ደግሞ የማስጠንቀቂያ ካርድ ያልተመለከቱ ቡድኖች ሆነዋል።

የሀዲያ ሆሳዕና ታሪካዊ ድል

ባለፈው ሳምንት የዐመቱን የመጀመርያ ድል ያሳካው ሀዲያ ሆሳዕና በዚህ ሳምንት ደግሞ በታሪኩ የመጀመርያ የሆነውን የፕሪምየር ሊግ የሜዳ ውጪ ድል አስመዝግቧል።

ቡድኑ ለሁለተኛ ጊዜ በሊጉ እየተሳተፈ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን የመጀመርያ የሜዳ ውጪ ድል ለማሳካት 17 ጨዋታዎች ጠብቆ በ18ኛው ተሳክቶለታል።


በዚህ ሳምንት…

– ሙጂብ ቃሲም በተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ላይ ኳስና መረብን አገናኝቷል።

– ሀዲያ ሆሳዕና በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ተከታታይ ድል አሳክቷል።

– ባህር ዳር ከተማ ለአምስተኛ ተከታታይ ጨዋታ ከሜዳው ውጪ ሳያሸንፍ ተመልሷል። ቡድኑ ባለፉት 13 ጉዞዎቹ ማሳካት የቻለው አንድ ድል ብቻ ነው።

– አሰልጣኙን ያሰናበተው ወላይታ ድቻ ያለፉትን ሰባት ተከታታይ ጨዋታዎች ከድል ርቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ