“ሻንጣዬ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ሄደ፤ እኔ ግን ተመለስኩ” የሥዩም ተስፋዬ አይረሴ አጋጣሚ

ባለፈው ሳምንት የሥዩም ተስፋዬን የሱዳን ትውስታ አቅርበንላቹ ነበር። አሁን ደግሞ ተከላካዩ በተጫዋችነቱ የመጀመርያ ዓመታት የገጠመው ያልተጠበቀ አጋጣሚን እንዲህ አሰናድተነዋል።

በሀገሯ የተዘጋጀችውን የሴካፋ ውድድር ያሸነፈችው ኢትዮጵያ በቀጣዩ ዓመት በሩዋንዳ በተደረገው ውድድር ላይ ለመካፈል በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ከተመረጡ ተጫዋቾች መካከል ሥዩም ተስፋዬ አንዱ የነበረ ቢሆንም በአስገራሚ ሁኔታ ከጉዞው እንዲቀር ተደርጓል። ብሔራዊ ቡድኑ የውድድሩ ቻምፒዮን በመሆን ቢመለስም በወቅቱ የተፈጠረው ሁኔታ በጊዜው ገና በተጫዋችነት መጀመርያ ዓመታት ላይ ለነበረው ሥዩም ለመቀበል የሚያስቸግር ነበር። ሆኖም ተጫዋቹ በሁኔታው ተስፋ ሳይቆርጥ ራሱን በማሻሻል ከዛ በኋላ በተደረጉ የብሔራዊ ቡድን አመዛኝ ጨዋታዎች ቀዳሚ ተመራጭ መሆንና ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈው ብሔራዊ ቡድን ወሳኝ ተጫዋች ለመሆን በቅቷል።

የቀኝ መስመር ተከላካዩ ወደ ኋላ በመመለስ ወቅቱን እንዲህ ያስታውሰዋል።

“ጊዜው ታዳጊ እያለሁ ያጋጠመ ነው። ታዳጊ ቡድን ውስጥ ሆኜ ጥሩ ብቃት ያሳየሁበት እና ለዋናው ብሔራዊ ቡድን የተመረጥኩበት ነበር። ለብሔራዊ ቡድን ተጠራሁና ሁሉም ነገር እንዳሟላ ተነገረኝ። ሁሉም ነገር አሟልቼ ቤተሰብ የሰፈር ሰው ሁሉም ተሰናብቼ ለጉዞ ተዘጋጀው ከቡድኑ ጋር ወደ ኤርፖርት ሄድኩ። እዛ የገጠመኝ ነገር ግን ከጠበቅቡት ውጭ ነበር። በወቅቱ ጋሽ ሰውነት ቢሻው ነበር አሰልጣኝ። እሱ ፈልጎኝ ነበር የተመረጥኩት። እዛ ስደርስ ግን በማላውቀው ምክንያት ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር እንደማልጓዝ ተነገረኝ። ጋሽ ሰውነት አይሆንም ልጁ መጓዝ አለበት ቢል ሰሚ አጣና በእኔ ቦታ ሌላ ሰው ተክተው እኔ ወደ ቤቴ ተመልስኩ።

” በጣም በጣም ከባድ ግዜ ነበር፤ እኔ ገና ታዳጊ ነበርኩ ምንም ነገር አላውቅም። ቤተሰቤን እና ጓደኞቼን ተሰናብቼ ሄጄ ከኤርፖርት ስመለስ ስሜቴ ተጎድቶ ነበር። ለአንድ ሳምንት ለሚሆን ጊዜ ከቤት አልወጣሁም ነበር። ስሜቴ ተጎድቶ ወደ እግር ኳስ መመለስ ራሱ አስጠልቶኝ ነበር፤ ወደ ቀድሞ ስሜቴ ለመመለስ ጊዜ ወስዶ ነበር። ደሞ የሚገርመው ነገር ነገ ጋዜጠኞች ስለሚመጡ ከነሱ ጋር ትመጣለህ፤ አሁን ፌደሬሽን ሄደህ አመልክት ነው ያሉኝ። እኔ ደግሞ በውቅቱ ምንም አላውቅም፤ እሺ ብዬ ፌደሬሽን አመለከትኩ። ኃላፊነቱን ከራሴ ለማውረድ ብዬ ፌደሬሽን ሄጄ አመለከትኩ። ስልክህን ስጥ ብለውኝ ሰጥቼ ብጠብቅ ብጠብቅ አልደወሉም። እኔ ከኤርፖርት ስመለስ ሻንጣዬ ግን ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ሄደ።

” በርግጥ በጊዜው ስሜቴ ተጎድቶ ነበር። እድለኛ ሆኜ ግን ከዛ በኃላ ጠንክሬ በመስራት ሀገሬን ወክዬ ብዙ ጨዋታዎችን አድርጌያለው። ብዙ ስኬትም አጣጥመናል እንደ ቡድን። በዚ አጋጣሚ አሁን ላለሁበት ደረጃ እንድደርስ የረዱኝ በሙሉ ማመስገን እፈልጋለው፤ በተጨማሪም የቡድናችን የመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊዎች ሁሌም ያበረታቱኛል። እነሱንም በጣም ማመስገን እፈልጋለው።”

በወቅቱ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ የነበሩት ሰውነት ቢሻውም በአሰልጣኝነት ዘመናቸው የማይረሱት አሳዛኝ ክስተት እንደነበር በ2007 በኢትዮጵያ የተስተናገደው የሴካፋ ውድድርን አስመልክቶ በመቅደላ ፕሮሞሽን በተዘጋጀው ” የሴካፋ ትውስታ መፅሔት” ላይ ስለዚህ ጉዳይ ይህንን ብለው ነበር።

“ሥዩም ተስፋዬ በጣም ጥሩ ብቃት ላይ የሚገኝ ወጣት ነበር። ወደ ሩዋንዳ ከሚጓዙት የቡድን አባላት ውስጥም አካትቼው ነበር። መጨረሻ ላይ አንዳንድ ግለሰቦች ሥዩም ወደ ሩዋንዳ እንዳይሄድ እንቅፋት ፈጠሩ። እኔ ልጁን ትቼው እንደማልሄድ ገለጽኩኝ። ፌዴሬሽኑ ግን ተጨማሪ ሌላ ሁለት ግለሰቦችን ለመጨመር ብሆ ሃያ ሁለት የቡድን አባላት ወደሩዋንዳ ለመሄድ ተዘጋጀ። ኤርፖርት ከገባን በኋላ የሥዩም ትኬት ጠፋ ተባለ። እኔ በወቅቱ አውሮፕላን ውስጥ ገብቼ ነበር። የሥዩም እቃ ተጭኖ ነበር። ሆኖም በነገው አውሮፕላን እንደሚመጣ ተነገረውና ፌዴሬሽን በመሄድ ሪፖርት አደረገ። እኔም ምንም ማድረግ አልቻልኩም ቀድሜ ስለሄድኩ። እኛም የሥዩምን ሻንጣ እና ዋንጫውን ይዘን አዲስ አበባ ገባን። በእግር ኳስ ሕይወቴ በጣም ያዘንኩበት ጊዜ ነበር። በአሰልጣኝ ሥራ ስልቃ እየገቡ ጫና በመፍጠር የልጆችን አዕምሮ የሚጎዱ አንዳንድ ግለሰቦች አሉ፤ ይህ ሊታረም ይገባዋል፡፡ አሁን ግን ሥዩም ጠንክሮ በመስራት ኮከብ ተጫዋች መሆን የቻለ አመለ ሸጋ ልጅ ነው። እኔም እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ ይህንን ስኬቱን በማየቴ።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ