የደጋፊዎች ገፅ | የአዳማ ከተማ ደጋፊዎች መኅበር ፕሬዝደንት አቶ ምስክር ሰለሞን

ከምስረታው ጀምሮ ብዙ እግርኳሰኛ ኮከብ ትውልዶችን አፍርቷል፣ በእግርኳሱ ከፍተኛ ስም እና ዝናም ያተረፈ ትልቅ ክለብ ነው። ቡድኑ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ከነበረው ጥንካሬ ባለፈ የክለቡ አስራ ሁለተኛ ተጫዋች በመሆን ውበቶቹ እና ድምቀቶቹ ደጋፊዎቹ መሆናቸው ይታወቃል። ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ምክንያቶች ደጋፊው ከሜዳ እየሸሸ ይገኛል። እነዚህ ክለቡ እየገጠሙት ያሉትን ተግዳሮቶች ለማለፍ ከክለቡ ሥራ አመራር ቦርድ ጋር በመሆን የደጋፊ ማኀበሩ የክለቡን ወቅታዊ ችግሮች ለመቅረፍ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል። ይህን ስራ በመስራት ከፍተኛውን ጥረት እያደረገ የሚገኘው ከሃያ ዓመት በላይ ክለቡን በመደገፍ የሚታወቀው እና ቀድም ባሉ ዓመታት ደጋፊ ማኀበሩን በምክትል ፕሬዝደንት ይመራ የነበረው እና ከአንድ ዓመት ወዲህ ፕሬዝደንት በመሆን የደጋፊ ማኀበሩን እያገለገለ የሚገኘው አቶ ምስክር ሰለሞን የዛሬው የደጋፊዎች ገፅ እንግዳችን ነው። ይህ በርካታ ደጋፊ ያለውን ክለብ ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ እና በቀጣይ የደጋፊ ማኀበሩ ሊሰራቸው ባቀዳቸው ስራዎች ዙርያ ያደረግነውን ቆይታ ይዘን ቀርበናል።

የአዳማ የደጋፊዎች ማኀበር አወቃቀር ምን እንደሚመስል በመጠየቅ ልጀምር?

ደጋፊ ማኀበሩ በዘጠኝ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት እና ሦስት ንዑሳን ክፍሎች የተከፋፈለ ነው። የአቀባበል ፣ የገቢ አሰባሳቢ እና የፀጥታ ክፍሎች አሉት። ደጋፊ ማኀበሩ ተጠሪነቱ ለክለቡ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ነው። ዘንድሮ ደግሞ በተለየ መልኩ ከዚህ ቀደም ባልነበረ አሰራር በክለቡ ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ውስጥ ድምፅ አግኝተን እየተሳተፍን ነው። ከዚህ ቀደም ክለቡ ያቀደውን ነገሮች ብቻ ነበር ስናስፈፅም የቆየነው። አሁን ግን ከማስፈፀም ባሻገር የክለቡን ዕቅድ በጋራ አብሮ በመሆን በማውጣት ደጋፊ ማኀበሩ ትልቅ ሚና እየተወጣ ይገኛል። በተጨማሪም ያለፉትን ዓመታት የክለቡ ህልውናን ለማስጠበቅ ፣ ክለባችን የገጠመውን የፋይናስ ችግር መሠረት በማድረግ የክለቡ የበላይ አካሎች እንዲረዱ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። እንግዲህ ደጋፊ ማኀበሩ በእንደነዚህ ያሉ ሁኔታዎች ላይ ተሳትፎ እያደረገ ነው። በ2013 ደግሞ ምን አቅደን በምን ዓይነት ሁኔታ መምጣት አለብን በሚለው ጉዳይ እየሰራን እንገኛለን።

አዳማ ትልቅ ክለብ ነው። በእግርኳሱ ብዙ ትውልዶችን መፍጠር የቻለ ነው። በቀጣይም ይሄን ያስቀጥላል ተብሎ ይታመናል። ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ባልተለመደ ሁኔታ የፋይናስ ችግር እያጋጠመው ነው። የችግሩ ምክንያት ምድነው ?

እኛ እንደ ደጋፊ ማኀበር ስናየው ከአስራ ስድስቱ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ሁለቱ ብቻ ናቸው በምሳሌነት ህዝብ ግኑኝነት ያላቸው። ወደ አዳማ ስመጣልህ በዚህ ደረጃ ገልፆ የሚናገር ሰው ስለሌለ እንጂ እኔ እንደ ደጋፊ የማስበው የአዳማ ችግር የተለየ ሆኖ አይደለም። ሁሉም ፕሪሚየር ሊግ ላይ ያሉ ክለቦች በመንግስት ድጎማ የሚተዳደሩ ናቸው። አዳማ ከፋይናስ ጋር ተያይዞ ያጋጠመው ችግር በተመለከተ የተለያዩ መረጃዎችን ከሚዲያው እንሰማለን። ሆኖም አንደ አንድ ጋዜጠኛ ወይም የስፖርት ባለሙያ ‘ያጋጠመው ችግር የቱ ጋር ነው ? ‘ብሎ ክለቡን መጥቶ የሚጠይቅ የለም። በግለሰብ ደረጃ ወይም በሦስተኛ ወገን በሚሠጡ መረጃዎች የክለቡ ስም ብዙ ጊዜ ሲብጠለጠል እንሰማለን። ግን በተቃራኒው በኮሮና ዘመን ምንም ዓይነት ገቢ ሳይኖረው ደመወዝ የከፈለ ብቸኛው ክለብ አዳማ ነው። ለምን ይህ እንደማይወራለት ግን አይገባኝም። ቅድም እንደተናገርኩት የመረጃ አሰጣጥ ክፍተት እንጂ አዳማ የተለየ የፋይናስ ችግር ኖሮበት አይደለም።

የፋይናንስ ችግር ክለቡን አጋጥሞት አያውቅም እያልክ ነው ?

እርግጥ ነው የፋይናንስ ችግር ገጥሞናል። ይህ ችግር ያጋጠመን ደግሞ ፌዴሬሽኑ ባወጣው አዲሱ የደመወዝ አከፋፈል ማሻሻያ መሠረት ነው። በአዲሱ የደመወዝ አከፋፈል ዘንድሮ ክለቡን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች አሉ። እንዲሁም በ2011የፈረሙ አስራ ዘጠኝ ውል ያላቸው አዲሱ የደሞዝ አከፋፈል የማይመለከታቸው ልጆች አሉ። የ2011 የግንቦት እና የሰኔ ደመወዝ አልተከፈለም። ምክንያቱም በወቅቱ የነበሩ አመራሮች በስፖንስር እንከፍላለን ብለው ባለመክፈላቸው የተነሳ የክለቡን የፋይናስ አቅም ተፈታትኖ ቆይቷል። ይህም ቢሆን ያልተከፈላቸው ደመወዝ በአዲሱ የደሞዝ አከፋፈል ሥርዓት ይከፈላቸው በማለት የክለቡ አመራር በሰጠው አቅጣጫ መሠረት ሊከፈላቸው ችሏል። አስቀድሞ ውል ባለቸው ልጆች አዲሱ የደመወዝ አከፋፈል የማይመለከታቸውን ተጫዋቾች ወደ አዲሱ የደመወዝ አከፋፈል አለማስገባት የፈጠረው ክፍተት እንጂ አዳማ የተጋነነ የፋይናስ ችግር አላጋጠመውም።

አዳማን መደገፍ መቼ ጀመርክ ? መነሻህ ምክንያትህ ምንድን ነው ?

አዳማ ለኔ ልዩ ቦታ አለው። አዳማን ለመደገፌ መነሻ ምክንያቴ ምን እንደሆነ ብጠቅስልህ ዛሬ ድረስ ሜዳ ላይ ላያቸው የምፈልጋቸው ልጆች ዘጠናዎቹ መጀመርያ ተነስተው ነበር። አሰልጣኝ ተስፋዬ ገብሩ በሚያሰለጥኑበት ወቅት ብርሐኑ ቃሲምን የመሳሰሉ ተጫዋቾች የአዳማ ፍቅር በውስጤ እንዲያድር አድርገውልኛል። ይኸው ከዛን ጊዜ ጀምሮ ክለቡን በተጫወተባቸው ሜዳዎች ሁሉ በመገኘት ስደግፍ ኖሬአለው። አሁን ከደጋፊነት በዘለለ እና ተወልደን ያደግንበት ከመሆኑ አንፃር አጋጣሚዎች ተመቻችተው ክለቡንም ሆነ የደጋፊ ማኀበሩን ለመምራት በቅቻለው። እኔ ለውጪ ሀገር ኳስ ምንም ዓይነት ቦታ የለኝም። ለሀገር ውስጥ ኳስ ግን ትልቅ ቦታ አለኝ። ከልጅነት ጀምሮ ስንደግፈው ኖሬ ካደግኩ በኃላ አስተዋፆኦ ማድረግ ጀምሬ ስራውም እየሰፋ መጥቶ እዚህ ደረጃ የደረሰ አመራር በመሆኔ በጣም ያስደስተኛል።

ከ20 ዓመት በላይ አዳማ ከተማን ደግፈሀል በዚህ ሁሉ የደጋፊነት ዘመንህ የተደሰትክበትን ቀን ታስታውሰዋለህ?

አዳማ ከፕሪምየር ሊግ ወርዶ ዳግመኛ በዓመቱ ባህርዳር ላይ በተካሄደው የብሔራዊ ሊግ ውድድር የተመለሰበት አጋጣሚ እጅግ የተደሰትኩበት ልዩ ቦታ የምሰጠው አጋጣሚ ነው።

የዛንክበት ጊዜስ?

የተደሰትኩበት ምክንያት ተቃራኒ ነው። በወቅቱ የነበሩ በአንዳንድ አስተዳደራዊ ችግር ምክንያት አዳማ ከፕሪሚየር ሊጉ የወረደበት ዕለት እኔ በጣም ያዘንኩበት ቀን ነው። ሆኖም በፍጥነት አዲስ የመጣው አስተዳደር አቅጣጫ አስቀምጦ ክለቡ ቶሎ መመለስ አለበት በማለት ክለቡ በወረደበት ዓመት መመለሱ ትልቅ ደስታ የሚፈጥር አጋጣሚ ነበር።

አዳማን በተመለከተ መረጃ በቀጥታ ከክለቡ ማግኘት በጣም አዳጋች ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ የሚወጡት መረጃዎች ግልፅ እና ተአማኒነት የጎደላቸው ከመሆናቸው በተጨማሪ አወዛጋቢ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህን ችግር ለመቅረፍ የመረጃ አሰጣጥ ችግሩን ለመቅረፍ ምን አስባቹሀል ?

ትልቅ ነጥብ ነው ያነሳህው እንደ ደጋፊ ማኀበርም የመረጃ አሰጣጥ ክፍተትን ለማስተካከል የበኩላችንን አስተዋፆኦ ለማድረግ እየጣርን ነው። አዳማ ማለት የህዝብ ቡድን ነው። እንዲህ ያለ ክለብን ሊፈርስ ነው ብሎ በዜና ማወጅ አስገራሚ እና አስደንጋጭ ነው። የብዙ ክለቦች በሚስጢር ተይዞ እንጂ ከአዳማ በላይ የገዘፈ ችግር ያለባቸው ክለቦች አሉ። አዳማ አሁን ባለው አሰራር በለውጥ ላይ ያለ ክለብ ነው። የክለብ በቦርድ አስተዳደር ከሚመሩት መዋቅር ጀምረህ እስከ ደጋፊ ማኀበሩ ድረስ ለውጥ ላይ ያለ ክለብ ነው። ሁልጊዜም ወደ ለውጥ ስትገባ መንገራገጭ ይኖራል። በተለይ የክለቡ አዲሱ ፕሬዝዳንት አቶ ገመቹ ከመጡ በኃላ ‘የክለቡ ችግር የቱ ጋር ነው ? ምን ያስፈልገዋል ? ምን ይጎድለዋል ? ‘ በሚል ዓምና ክለቡን ከሚመሩት አካላት እና በከተማው አስተዳደር መካከል የነበረውን ክፍተት በመሙላት ችግሮችን ለመቅረፍ ብዙ እየጣሩ ነው። ለምሳሌ በጊዜው ለሚዲያ አልተገለፀም እንጂ ከአንበሳ ቢራ ጋር በመነጋገር የሃምሳ አራት ሚሊዮን ብር የስፖንሰር ስምምነት ተፈራርመን ነበር። የኮሮና በሽታ በሀገራችን ተከስቶ እንጂ ጥሩ ጅምር ነበር። አሁንም ሌሎችም አማራጮችን በመጠቀም ክለቡን ስፖንሰር የሚያደርጉ አካላት በመፈለግ ጥረት እየተደረገ ነው። አዳማ በታሪኩ እንዲህ ያለ ቆራጥ መሪ (ፕሬዝደንት) ከዚህ ቀደም አግኝቶ ቢሆን ኖሮ እነዚህ ችግሮች ባልተጋረጡበት ነበር። አዳማ ቤት ጠፍቶ የነበረው ይሄ ነው። እሳቸውን ለማሞካሸት አይደለም። አብሪያቸው ስለምሰራም አይደለም። ስለዚህ እንደ ደጋፊ ማኀበርም እንደ ክለብም ለሚዲያው ግልፅ የሆኑ መረጃዎችን ለማድረስ እየሰራን ነው።

በርከት ያሉ ልጆች ክለቡን ለቀው እየሄዱ ነው። ይህ ክለቡን አይጎዳም ? ለመመለስስ ጥረት እያደረጋቹ ነው? በቦርድ ውስጥ ደጋፊ ማኀበሩ ድምፅ ያለው ስለሆነ የታሰበ ነገር ካለ ?

አዎ ጥረት እያደረግን ነው። በሀድያ ሆሳዕና ቅድመ ስምምነት ያደረጉ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ ለመመለስ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። ይህም በቅርብ ተሳክቶ የምታዩት ይሆናል። ጎን ለጎን ደግሞ አዳማ የትውልድ ችግር የለበትም ፤ ከታችኛው ቡድን ጥሩ ጥሩ ልጆችን ለማሳደግ እየሰራን ነው። ደጋፊውን የሚመጥን ቡድን ይዞ ለመምጣት ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ነው። ይህንን ወደፊት ሥራችንን ስናጠናቅቅ ግልፅ የምናደርገው ይሆናል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደጋፊዎች መካከል ክፍተት እንዳለ እና ከሜዳ የሸሹ ደጋፊዎች እንዳሉ ይነገራል። አሁን ለሚዲያ የማይመጥኑ በእግርኳሱ አካባቢ መሰማት የሌለባቸው ነገሮች ይሰማሉ። ይህን ለመቅረፍ እና ደጋፊውን ወደ አንድ ለማምጣት ምን ታስቧል?

እዚህ ጋር በግልፅ ለመናገር የምፈልገው ነገር ክለቡ ያለ ደጋፊ ማህበር ምንም ወይም ባዶ ነው ማለት ይቻላል። ደጋፊ በሌለበት ክለብ ውስጥ ስለ ደጋፊ ብታወራ ትርጉም የሌለው ነገር ነው። ሀገራችን ይሄን ሁለት ዓመት ካለችበት የለውጥ እንቅስቃሴ አንፃር ከተማችን ውስጥ ብዙ ነገሮች ተፈጥረዋል። አሁን እንዲህ ነው ብዬ በማልገልፅልህ ምክንያቶች ክፍተቶች ነበሩ። እነዚህን ችግሮች አስተካክሎ ክለቡን ወደአንድ ማመምጣት አስፈላጊ ነው። ለዚህም ክለቡን ያሻግራል ብለን በማመን ባለፈው እሁድ ከደጋፊዎች ጋር ተቀራርበን ለመነጋገገር አንድ ብለን ጀምረናል። ቅር የተሰኘ የተከፋም የተለያየ አስተሳሰብ ያለው ደጋፊ ከሁን በኋለ ልዩነቱን ወደ ጎን በመተው አዳማን ለመደገፍ መዘጋጀት አለበት። አዳማን የሚመጥን ገንቢ የሆነ የተሻለ ሀሳብ ይዞ ለመጣ በሩ ክፍት ነው። እኛ እንደሌሎቹ ክለቦች ብንሆን ብለን የምንመኛቸው መንፈሳዊ ቅናቶች አሉብን። ከአዳማ በኋላ የተፈጠሩ ቡድኖች ለክለባቸው አስፈላጊውን ድጋፍ ሲያደርጉ እንመለከታለን። በዚህ ደረጃ ደጋፊያችንን አሰባስበን ፣ አንድነቱን ጠብቀን ክለባችን በተሻለ ጎልቶ እንዲወጣ ለማድረግ ሥራዎችን እየሰራን ነው። ደጋፊው ከሜዳ የቀረበትን ምክንያት ለመቅረፍ ደጋፊውን ቁጭ አድርገን ማወያየት ጀምረናል። ከፈጣሪ ጋር በ2013 ያሉት ችግሮች ተቀርፈው ክለብ እና ደጋፊውን ይዘን እንደምንቀርብ መናገር እፈልጋለው።

በደጋፊነት ዘመንህ ለአንተ ምርጡ ተጫዋች ማነው?

ለኔ በህይወቴ ዛሬም ድረስ ነው የምነግርህ ምርጡ ተጫዋች የምለው ብርሀኑ ቃሲም ነው። እግርኳስን በእግሩ ሳይሆን በእጁ የሚጫወት የሚመስለኝ ድንቅ ተጫዋች ነው። የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎችን እና ተቃራኒ ቡድን ላይ የሚፈጥራቸውን ስሜቶች ሳስታውስ ዛሬም ድራስ ቀልቤን ይገዙኛል።

በመጨረሻ…

በመጨረሻ መናገር የምፈልገው የሀሳብ ልዩነቶች ካሉ ከአሁን በኋላ ለአዳማ ሲባል እንዲተዉ ጥሪዬን አቀርባለው። ደጋፊውን በማናገር ወደ አንድነት በማምጣት ክለቡን ወደ ሚጠቅሙ ሀሳቦች ልንመጣ ይገባል። መቼም ሁሉን ማስደሰት አይቻልም። ለአዳማ ሲባል ግን ልዩነቶቻችንን መፍታት አለብን። ሚዲያውን በተመለከተ በኃላፊነት ስሜት
ትክክለኛ ጥያቄዎችን ፣ ክለቡን ወደ ፊት ያራምዳሉ የሚባሉ ጥያቄዎችን ፣ ደጋፊውን የሚመለከት ነገር ካለ በቀጥታ የምትፈልጉትን መረጃ እንሰጣለን። በዚሁ አጋጣሚም የክለቡም ፕሬዝደንት መልስ ለመስጠት ቢሮቸው ክፍት መሆኑን እንጠቁማለን። አዳማ ከተማ ህዝባዊ አደረጃጀት እንዲኖረው ከዚህ በፊት በአፍ ከሚወራው በላይ በተግባር ወርደን ለመስራት ቁርጠኛ መሆናችንን እንገልፃለን። መላው ደጋፊም ከጎናችን እንዲቆም ጥሪዬን እስተላልፋለው።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!