​ቢኒያም በላይ ኤዘንበርገር አወ የሙከራ እድል አገኘ

ኢትዮጵያዊው አማካይ ቢኒያም በላይ እንደተጠበቀው በምስራቅ ጀርመን ለሚገኝ ፎትቦል ክለብ ኤዘንበርገር አወ የሙከራ እድልን አግኝቷል፡፡

ከዳይናሞ ድረስደን ጋር የነበረው የሁለት ሳምንታት የሙከራ ግዜ ቢኒያም ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ቢያሳይም ድረስደን ተጫዋቹን ለማቆየት ፍላጎት አላሳየም፡፡ ታዋቂው የጀርመን የስፖርት ጋዜጣ ቢልድ እንደዘገበው ከሆነ ቢኒያም ከሁለት ቀናት ያላነሰ ግዜያት በክለቡ እንደሚቆይ ታውቋል፡፡

ኤዘንበርገር አወ ተጫዋች የሆነው ኒኪ አድለር 4 ወራት በጉዳት ከጨዋታ ውጪ መሆኑን ተከትሎ ክለቡ ለቢኒያም እና የዩክሬን ዜግነት ላለው የ23 ዓመቱ ዩሪ ያኮቬንኮ የሙከራ እድል ሰጥተዋል፡፡ ቢልድ እንዳስነበበው ከሆነ ክለቡ ብዙ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን በመሞከር ላይ ይገኛል፡፡ የሳክሰኒ ግዛት ክለብ በሆነው ኤዘንበርገር አወ ቢኒያም በአውሮፓ የመጫወት ህልሙን እውን ለማድረግ ይጫወታል፡፡ የዳይናሞ ድረስደን የስፖርት ዳይሬክተር ስለቢኒያም ቀጣይ እድገት እንደሚከታተሉ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡

የቢኒያም የሙከራ እድልን አሁንም ያመቻቹለት በጀርመን መንግስት ድጋፍ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን የቴክኒክ አማካሪ የሆኑት ዩአኪም ፊከርት ናቸው፡፡

በሙሉ ስሙ ፉትቦል ክለብ ኤዘንበርገር አወ በመባል የሚታወቀው ክለቡ እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር 1946 ነው የተመሰረተው፡፡ የበርሊን ግንብ ከፈረሰ በኃላ ለረጅም አመታት በቡንደስሊጋ 2 ሲወዳደር ቆይቷል፡፡ በ2017/18 የውድድር አመትም ክለቡ በቡንደስሊጋ 2 የሚካፈል ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *