ሶከር ሜዲካል | ፊዝዮ-ቴራፒ እና እግርኳሳችን

ፊዝዮቴራፒ ከጉዳት የማገገሚያን እና የመቅረፍያን እንደዚሁም ጤናማ እንቅስቃሴን የመተግበሪያን ዘይቤዎች ያቀፈ የህክምና ተጓዳኝ ዘርፍ ነው። ይህ ዘርፍ ሳይንሳዊን ዘዴ በተከተለ መልኩ ሰዎች አካላዊ እንቅስቃሴያቸውን ወይም የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን በጤናማ መልኩ እንዲጠብቁ እና እንዲያስኬዱ ይረዳቸዋል። ከፍተኛ ንክኪ ያለው አካላዊ እንቅስቃሴ በሚደረግበት እና ተጫዋቾቹም ለጉዳት የተጋለጡ በሆኑበት እንደ እግርኳስ ባለ ስፖርት ደግሞ የዚህ የህክምና ዘርፍ ሚና ቀላል አይደለም።

የፊዚዮቴራፒ ህክምና ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ እና ከተለያዩ ማህበረሰቦች ባህላዊ ህክምና ጋር ትስስር በመፍጠር አብሮ ሲሰጥ ቆይቷል። አካላዊ ህክምናም ‘የህክምና አባት’ በሚባለው ሂፖክራተስ ዘመን ጀምሮ እንደነበረ ጥናቶች ያመላክታሉ። በ460 አመተ አለም ግሪካዊው ሄክተር ‘ሃይድሮቴራፒ’ የሚሰኝን የፊዝዮቴራፒ አይነት አስተዋውቋል። ይህም የውሃ ህክምና እንደማለት ነው። ግሪኮች ብቻ ግን አልነበሩም ይህን የህክምና ዘይቤ የሚከተሉት። ጥንታዊ ፅሁፎች እንደሚያመላክቱት በፐርሺያ፣ ቻይና እና ግብፅ የአካል እንቅስቃሴ እና ማሳጅን በመጠቀም ህመሞችን ያክሙ ነበር። በሃገራችንም በተለምዶ ወጌሻ በመባል የሚጠሩ ባህላዊ ሃኪሞች ከዘመናዊ የፊዚዮቴራፒ ህክምና ጋር ተመሳሳይ መሠረት ያለው ህክምና ሲሰጡ ኖረዋል። ባህላዊው የወጌሻ ህክምና በዘመናዊ ትምህርት እየተደገፈም እስከ ክለቦቻችን ድረስ ዘልቆ ጥቅም ላይ ይውላል።

በአአ ስታድየም በሚደረጉ ጨዋታዎች ከየክለቦቹ የህክምና ባለሙያዎች በተጨማሪ የጠብታ አምቡላንስ አገልግሎት ይሰጣል

በእግርኳስ ደረጃቸው ከፍ ያሉት የአውሮፓ ሃገራት ክለቦች በህክምና ቡድናቸው ውስጥ ፊዝዮቴራፒስቶችን በማካተት ከአሠልጣኙ፣ ከአካል ብቃት አሠልጣኞች እና በግልም ከተጫዋቾቹ ጋር አብረው እንዲሰሩ ሲያደርጉ ይስተዋላል። ከፍተኛ ውጥረት ያለባቸው ጨዋታዎች፣ ተደራራቢ ጨዋታዎችን ለማድረግ የሚያስገድዱ ውድድሮች፣ እና ጠንካራ የልምምድ ክፍለጊዜዎች በሚደረጉበት ዘመናዊ እግርኳስ በሳይንስ በተደገፈ መልኩ ጉዳቶችን መከላከል፣ ሲያጋጥሙም ተገቢውን ህክምና በመስጠት ተጫዋቾቹ በበቂ ሁኔታ እንዲያገግሙ ማስቻል አስፈላጊ ነው። የቡድኑ ፊዚዮቴራፒስቶችም ተጫዋቾች ከጨዋታ በፊት ሰውነታቸውን የሚያሟሙቁበት እና ራሳቸውን ለጨዋታ የሚያዘጋጁበት፣ጉዳት ሲያጋጥምም የሚያገግሙበት ሂደት ላይ ትኩረት በማድረግ ይሰራሉ።

የፊዚዮቴራፒ ህክምና ምንን ያካትትታል?

1) ጉዳቶችን እና ተያይዘው የሚከሰቱ ችግሮችን (Disability) መቅረፍ

2) አፋጣኝ ሆነ የቆዪ ጉዳቶችን ማከም

3) ጤናማ የሆነ የሰውነት አቅምን መገንባት

4) ጉዳትን ከመከሰቱ አስቀድሞ መከላከል

5) ከተከሰቱም ደግሞ በቂ የሆነ የማገገሚያ ጊዜ እና መፍትሄ ማቅረብ

6) ታካሚዎች ጉዳቶች እንዳይደጋገሙባቸው ማድረግ የሚችሉበትን መንገድ ማሳየት እና ማስተማር

ከጡንቻ እና ከአጥንት ጋር የተያያዙ ህመሞች፣ ከነርቭ ጋር የተያያዙ ጉዳቶች፣ የመገጣጠሚያ አካላት ላይ የሚከሰቱ ጉዳቶች፣ እና ማንኛቸውም አይነት የህመም ስሜት በፊዝዮቴራፒ ከሚታከሙ ህመሞች ይመደባሉ። ጉዳቶችን ከማከም በተጨማሪ የአንድ ተጫዋች ብቃት ሳይዋዥቅ ወደ ሜዳ መመለስ የሚችልበትን የሰውነት ማጎልመሻ እና ማጠንከሪያ እንቅስቃሴዎች ዘርፉ አካቶ ይዟል። እንቅስቃሴዎቹ የተጎዳው የሰውነት ክፍል በፊት ይሰጥ የነበረውን ግልጋሎት በአግባቡ እንዲተገብር ያስችላሉ። በእግር ኳስ የጉልበት፣ የቁርጭምጭሚት እና የጡንቻ ጉዳቶች አዘውትረው የሚከሰቱ ናቸው። ከእነዚህ አይነት ጉዳቶች በበቂ ሁኔታ አገግሞ ወደ ሜዳ ለመመለስ ከሚደረጉ የቀዶ ጥግና ህክምናዎች በተጨማሪ የፊዝዮቴራፒ ሚና ላቅ ያለ ነው።

እንደ ሴቶች ሊጎች ባሉ እምብዛም ትኩረት የማይደረግባቸው ውድድሮች ላይ ከ18 ተጫዋች ዝርዝር ውጪ የሚገኙ ተጫዋቾች እንደወጌሻ ሲያገለግሉ ማየት የተለመደ ነው።

በፊፋ እና በካፍ የክለቦች ምዝገባ አሠራር (Club Licensing) መመሪያ መሰረት አንድ የእግር ኳስ ክለብ ማሟላት ካለበት አስፈላጊ ዝርዝሮች አንዱ የፊዝዮቴራፒ ባለሙያ ነው። በሀገራችን ክለቦች የሚታየው የዚህ ዘርፍ አተገባበር እጅጉን አናሳ ነው። ይህም ከባለሙያ እጥረትም ሆነ ለዘርፋ ትኩረት ባለመስጠት ምክኒያት የመጣ ሊሆን ይችላል። ይልቁንም ያለሙያቸው ወይም ብቃታቸው ባልተረጋገጠ መልኩ በተለምዶ ወጌሻ እየተባሉ የሚሰሩ ሰዎች በርከት ብለው ይታያሉ። በቅርብ ጊዜ ሙያውን በሀገራችን እንዲስፋፋ እና ተደራሽነቱ እንዲጨምር በማሰብ በተለያዪ ዪኒቨርስቲዎች ትምህርቱ መሰጠት ተጀምሯል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በዶክትሬት ኦፍ ፊዝዮቴራፒ ትምህርቱን በመስጠት ይገኛል።

ተጫዋቾች በአግባቡ የሚያስፈልጋቸውን የህክምና ክትትል እና በቂ የማገገሚያ ጊዜ አግኝተው ከሚያጋጥማቸው ማንኛውም ጉዳት ብቃታቸው ሳይዋዥቅ ወደ ሜዳ መመለስ እና የጫወታ ዘመናቸውን ያለ እከል ማገባደድ የሚችሉት በባለሙያ የሚሰጥ የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት ሲያገኙ ነውና ክለቦቻችን በትኩረት ሊመለከቱት ይገባል።

One thought on “ሶከር ሜዲካል | ፊዝዮ-ቴራፒ እና እግርኳሳችን

 • February 14, 2018 at 5:23 pm
  Permalink

  ባለመሰልቸት እና በጥልቀት አንብቡት ስላነበባችሁም በቅድሚያ አመሰግናለሁ
  እግር ኳስ መጫወት ብዙ የጤና ጠቀሜታዎች አሉት፤ ከነዚህም መካከል የተሻሻለ የአካዴሚያዊ አፈፃፀም፣ የጡንቻ መነቃቃት፣ የሜታቦሊክ እና የልብና የደም ቧንቧ ማስተካከያ እንዲሁም የህይወት ዘይቤ በሽታዎች የመያዝ አደጋን መቀነስ ተችሏል፡፡ ይሁን እንጂ እግርኳስ በአጠቃላይ ከሌላወ ስፖርት ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሰ ስፖርት ሆኖ ተገኝቷል::
  እንደ አለም አቀፉ የእግር ኳስ የበላይ ማህበር (FIFA) የሕክምና ዳሰሳ እና የምርምር ማዕከል (F-MARC) ዘገባ መሠረት, ጉዳት ማለት ማንኛውም በተጨዋች የሰውነት ክፍል ላይ የሚከሰት ህመም ተከትሎ ተጨዋቹን የሕክምና ክትትል አስፈላጊነት ግምት ውስጥ ሳይገባ ከውድድር ወይም ከልምምድ ወይም ከእግር ኳስ ህይወት የሚያርቅ በድግግሞሽ እንዲሁም በንኪኪ ውስጥ የሚከሰት ማንኛውም የአካል ጉዳት ነው፡፡
  በንኪኪ ስፖርት ውስጥ የሚከሰተው አጠቃላይ ጉዳት እስከ 1000 በሚደርሱ ሰዓታት ከ 10 እስከ 15 አደጋዎች እንደሚደርስ ይገመታል ሆኖም ግን በወንድ እግር ኳስ ተጫዋቾች ላይ የተደረገው ጥናት (epidemiological studies) በ 1000 ጨዋታ ሰዓታት ውስጥ ከ 10 እስከ 35 የሚደርሱ ጉዳቶች መኖራቸውን ያመልክቷል፡፡ እነዚህ አደጋዎች በጣም የተለመዱ ከውድድር እና ከልምምድ የመራቅ መንስዔዎች ናቸው እናም ተገቢ የመከላከያ ዘዴዎች ያስፈልጋቸዋል፡፡
  ለምሳሌ በዘንድሮው የኢትዮጲያ ፕሪሚየር ሊግ ለተለያዩ ቡድኖች ነባር እና አዳዲስ የፈረሙ ተጨዋቾች በመጀመሪያው ውድድር ዙር ግልጋሎት በጉዳት ያልሰጡት ምን ያህሉ ናቸው? የጉዳታቸው ምክንያትስ ምንድን ነው? በየቡድናቸው በትክክል የሰለጠነ የፊዚዮቴራፒስት ያላቸው፣ የጉዳታቸውን መጠን የሚከታተል ፣ለጨዋታ ብቁ መሆናቸውን ወደ ልምምድ እንዲመለሱ የሚመሰክር፣ ዳግም ጉዳት እንዳያጋጥማቸው የመከላከል ስራ የሚሰሩ ስንት ናቸው? ለሁሉም ቢታሰብበት!!!!! አከሌ የሚባል ተጨዋች ገና በመጫወቻ ጊዜው ከስፖርቱ ተገለለ እርዳታ ይደረግለት ከማለት ተጨዋቹን ብሎም ሀገራችንን ለመጥቀም የየቡድን አመራሮች፣ ባለቤቶች እንዲሁም ይመለከተኛል የምትሉ ሁሉ በተለምዶ ወጌሻ ተብሎ ለማሟያ የሚደረግ ስራ ይቁም ብዙ ባለሙያዎች ስላሉን እንጠቀም ከሁለተኛ ድግሪ እሰከ ሶስተኛ ድግሪ በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገር የተማሩም እየተማሩም ያሉ፡፡
  አመሰግናለሁ

Leave a Reply

error: