​ሪፖርት | ደደቢት መከላከያን በሰፊ የጎል ልዩነት አሸንፏል

ከተላለፉ ጨዋታዎች ውጪ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ደደቢት እና መከላከያ በአዲስ አበባ ስታድየም ተገናኝተው የሊጉ መሪዎች ወደ አሸናፊነት የተመለሱበትን የ 4-0 ውጤት ማሳካት ችለዋል።

ደደቢት በጅማ አባ ጅፋር ሽንፈት ከቀመሰበት ጨዋታ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ጌታነህ ከበደን በቅጣት እንዲሁም አቤል ያለውን በጉዳት ምክንያት በአክዌር ቻሞ እና ኤፍሬም አሻሞ የተካ ሲሆን ከጉዳት የተመለሰው ስዩም ተስፋዬ በኩዌኪ አንዶህ እንዲሁም ብርሀኑ ቦጋለ እና ፋሲካ አስፋው በሰለሞን ሀብቴ እና አቤል እንዳለ ምትክ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ የገቡ ሌሎች ተጨዋቾች ሆነዋል። ከዚህ በተጨማሪ የሶስት ወር ቅጣት የተላለፈባቸው የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ በትሪቡን በመሆን ቅጣታቸውን የጀመሩ ሲሆን ም/አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ ቡድኑን መርቷል።  በመከላከያ በኩል ደግሞ ያለግብ ከተጠናቀቀው የሲዳማ ቡና ጨዋታ አማካይ ክፍል ላይ ቴውድሮስ ታፈሰ በመስፍን ኪዳኔ ከፊት ደግሞ የተሻ ግዛው በአቅሌሲያስ ግርማ የተተኩ ተጨዋቾች ናቸው።

ጨዋታው ግብ ያስተናገደው ገና በሁለተኛው ደቂቃ ነበር። በብቸኛ አጥቂነት የተሰለፈው አኩዌር ቻሞ መከላከያዎች የመከላከል ቅርፃቸውን ባልያዙበት ሰዐት ከኤፍሬም አሻሞ የተቀበለውን ኳስ ሁለት ጊዜ አሸማቆ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ በመምታት ነበር ግቧን ያስቆጠረው። አኩዌር 11ኛው ደቂቃ ላይም በቀኝ መስመር ከተነሳ የእጅ ውርወራ ከፋሲካ አስፋው ጋር በመቀባበል ሁለተኛ ጎል ደግሟል። ሁለቱም ቡድኖች ኳስ መስርተው ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክልል ለመግባት ሲሞክሩ በታዩባቸው የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በቀላሉ ወደ ግብ ዕድልነት መቀየር የሚችሉ አጋጣሚዎችን ቢያገኙም 3ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲካ አስፋው በደደቢት በኩል እንዲሁም 8ኛው ደቂቃ ላይ የተሻ ግዛው ከመከላከያ የሰሯቸው የቅብብል ስህተቶች አጋጣሚዎቹ እንደዋዛ እንዲያልፉ ምክንያት ሆነዋል። በፍጥነት ሁለት ግብ ያስተናገዱት መከላከያዎች ቀሪውን የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች በሙሉ ወደፊት ተጭነው ለመጫወት ሞክረዋል። ሆኖም የቡድኑ እጅግ የጠበበ የአማካይ ክፍል ኳሶችን እንደልብ ተቀባብሎ እና የተጋጣሚ ተከላካዮች መሀከል ያለውን ክፍተት እንዲሰፋ አድርጎ ሙከራዎችን ለማድረግ ፈፅሞ የተመቸ አልነበረም። በመሆኑም ቡድኑ የመጀመሪያውን ሙከራ ለማድረግ 22 ደቂቃዎች አስፈልገውታል። ይህም ሙከራ በሳሙኤል ሳሊሶ አማካይነት ከርቀት ተደርጎ በክሌመንት የዳነ ነበር። ከዚህ ውጪ የምንይሉ ወንድሙ የ33ኛ እና 4ኛ ደቂቃ የግንባር ኳሶች ኢላማቸውን ሳይጠብቁ ሲቀሩ ቴውድሮስ ታፈሰ 41ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ የመታው የቅጣት ምት በክሌመንት ጎል ከመሆን ድኗል። በደደቢት በኩል ከጎሎቹ በቀር የታየው ብቸኛ ሙከራ 37ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ጉግሳ ከቀኝ መስመር ባሻማው ኳስ የተገኘ ሲሆን ኤፍሬም አሻሞ ከሳጥን ውስጥ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ደደቢቶች 23ኛው ደቂቃ ላይ የተከላካይ አማካያቸው አስራት መገርሳ በጉዳት በአቤል እንዳለ ተቀይሮ መውጣቱን ተከትሎ ፋሲካ አስፋውን ወደ ኃላ እንዲሳብ ያደረጉ ቢሆንም በተደጋጋሚ የመከላከል ሚዛናቸው ሲፋለስ እና ለመከላከያ ጥቃቶች ሲጋለጡ ነበር የመጀመሪያውን አጋማሽ ያገባደዱት።

በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ሁለት ጎሎችን ማስቆጠር የቻሉት ደደቢቶች ከእረፍት መልስ ደግሞ በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ተጨማሪ ሁለት ግቦችን ማከል ችለዋል።  81ኛው ደቂቃ ላይ ስዩም ተስፋዬ ሽመክት ጉግሳ ከግራ መስመር ያሳለፈለትን እና መከላከያዎች ማፅዳት ያልቻሉትን ኳስ ከቅርብ ርቀት ሲያስቆጥር 88ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ኤፍሬም አሻሞ ኳስ ይዞ በመግባት እና አቤል ማሞን በአንድ ለአንድ ግንኙነት ሚዛን በማሳት የመጨረሻዋን ጎል አስቆጥሯል። ደደቢቶች ከነዚህ ግቦች ውጪ በጭማሪ ደቂቃ ሽመክት ካባከነው ግልፅ የግብ አጋጣሚ ውጪ ሌላ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ኳስ በአቤል እንዳለ እና የአብስራ ተስፋዬ እግር ስር ሲሆን የተሻለ አስፈሪነት የሚታይባቸው ደደቢቶች አጥቂያቸው አኩዌር ቻሞን ከፊት አስቀርተው እና የአማካይ ክፍላቸውን በብዛት ከራሳቸው ሜዳ እንዳይርቅ በማድረግ ተጠንቅቀው በመጫወት ነበር ጨዋታውን የጨረሱት። የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው መከላከያዎች በርካታ ወደ መጨረሻ የግብ ዕድልነት ሊቀየሩ የሚችሉ አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም ወደ ሙከራነት በመቀየሩ በኩል ግን እጅግ ተዳክመው ታይተዋል። የተጨዋቾች የግል የመጨረሻ ውሳኔ አሰጣጥ ችግር የታየበት ጦሩ በደደቢት ሳጥን ውስጥ በተደጋጋሚ እንደመገኘቱ ክሌመንት አዞንቶን የፈተነባቸው ጊዜያት ግን ጥቂት ነበሩ። ክሌመንት የሳሙኤል ታዬን እና ማራኪ ወርቁን ከግብ አፋፍ ላይ የተደረጉ ኳሶች ቢያመክንም ከዛ ውጪ ግን የተሞከሩበት ጥቂት ኳሶች ኢላማቸውን መጠበቅ ያልቻሉ ነበሩ። መከላከያዎች ይህን ብልጫ እንዲወስዱ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ሽመልስ ተገኝ የተሻለ የማትቃት ተሳትፎ ፣ ጥሩ ስኬት የነበራቸው ከቴዎድሮስ ታፈሰ የሚነሱ ኳሶች እና የቡድኑ ከመጀመሪያው የተሻለ ሊባል የሚችል የሜዳውን ስፋት የመጠቀም ሙከራ ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው። ቢሆንም ግን ቡድኑ ወደ ተጋጣሚው ሳጥን ከገባ በኃላ በተደጋጋሚ የመናበብ ስህተትን ሲሰራ አምሽቷል። ከዚህ በተጨማሪም የመከላከል አቅሙን ጥያቄ ውስጥ በሚጥል መልኩ ግቦችን ማስተናገዱም የጨዋታው ልዩነት እንዲሰፋ አድርጓል። 

በውጤቱ ደደቢት ከተከታዩ መቐለ ከተማ በሶስት ነጥብ የራቀ ሲሆን መከላከያ የመጀመሪያውን ዙር ከወራጅ ቀጠና ውጪ ለመሆን ተስፋውን በተስተካካይ ጨዋታዎቹ ላይ ለመጣል ተገዷል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

ም/አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ – ደደቢት

ዛሬ ቡድናችን ጥሩ ነበር። አስፈላጊውን ሶስት ነጥብም አግኝተናል። ሁለት ወሳኝ አጥቂዎቻችን በጉዳት እና ቅጣት ምክንያት አልነበሩም። ሆኖም ግን ከተስፋ ቡድን በመጡ ልጆች ተክተን ገብተናል። ጎሎቹን ያገባው ልጅም ከተስፋ ቡድን የመጣ ነው። ተጨዋቾቻችን ጥሩ እንቅስቃሴ አድርገው የሚያስፈልገውን ነጥብ አሳክተዋል። 

አሰልጣኝ ምንያምር ፀጋዬ – መከላከያ

ባለ በሌለን ሀይል አጥቅተን ለመጫወት ጥረት አድርገናል። ሆኖም ግን እነሱ ባገኙት አጋጣሚ ተጠቅመዋል። ሁልጊዜ እንደምንለው እኛ የምናገኛውን አጋጣሚዎች አንጠቀምም በተቃራኒው እኛ ላይ ይቆጠራል። ችግሩ ያ ነው። በመጀመሪያው አጋማሽ እነሱ ሁለቴ መጡ ሁለቴ አገቡ እኛ ግን አምስት ስድስቴ ሞክረን ማግባት አልቻልንም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *