ባህርዳር ከተማ የአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸውን ውል አራዘመ

በ2010 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ሶስት ቀሪ ጨዋታዎች እየቀሩት በ2011 በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ መሆኑን ያረጋገጠው ባህር ዳር ከተማ ገና ውድድሩ ሳያልቅ የአሰልጣኙ ጉዳይ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቶ በዛሬው እለት እልባት አግኝቷል።

ከሀዲያ ሆሳህና ወደ ባህርዳር ከተማ በዘንድሮ የውድድር አመት ያመሩት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ባህር ዳር ከተማን ከምስረታው ከ1973 ጀምሮ ሳያሳካ የቆየውን ስኬት ያሳኩ ሲሆን ከክለቡ ጋር የነበራቸውን ውል በመጨረሳቸው ምክንያት ይቀጥሉ አይቀጥሉ ሳይታወቅ ቆይቶ ነበር። ክለቡ እና አሰልጣኙ ትላንት በፓፒረስ ሆቴል ድርድር አድርገው በክፍያ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ሳይደርሱ በይደር ጉዳዩን ወደ ዛሬ አዘዋውረውት ነበር። በዛሬው እለት ሁለቱ አካላት ከስምምነት መድረሳቸው የተነገረ ሲሆን አሰልጣኙ ለአንድ ዓመት ከክለቡ ጋር እንደሚቆዩ ለማወቅ ተችሏል።

አሰልጣኝ ጵውሎስ ስለ ስምምነቱ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት “ትላንት የነበረው አለመስማማት ብዙም ችግር አልነበረውም። ቤተሰብ መሀከል ግጭቶች እና አለመስማማቶች ይከሰታሉ። ነገር ግን ትላንት የነበሩትን ክፍተቶች ዛሬ በመነጋገር ፈተናቸዋል። በቀጣይም የከፍተኛ ሊግ ውድድሩ ስላላለቀ ጨዋታችን ጎን ለጎን እያከናወንን የቀጣይ ዓመት ዝግጅታችንን እንጀምራለን። ” ሲሉ አስረድተዋል። ስለ ምክትሎቻቸው እና ስለ አሰልጣኝ ቡድኑ አባላት አሰልጣኝ ጳውሎስ በመቀጠል ምላሽ የሰጡ ሲሆን ዘንድሮ አብረዋቸው ያሰለጠኑት አሰልጣኞች በቀጣይም አብረዋቸው እንደሚቆዩ ነገር ግን የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ እና ተጨማሪ ረዳቶችን ከክለቡ የቴክኒክ ክፍል ጋር በመተባበር እንደሚያመጡ ገለፀዋል።