ሶከር ሜዲካል | የብሽሽት እና የዳሌ ጉዳቶች በእግር ኳስ

በጨዋታ ጊዜ የሚያጋጥሙ ጉዳቶች መንስኤና መፍትሄዎችን በምንዳስስበት የሶከር ሜዲካል አምዳችን ዛሬ በእግር ኳስ ተዘውትረው ከሚስተዋሉ ጉዳቶች መካከል የብሽሽት እና የዳሌ ጉዳቶችን እንመለከታለን፡፡

የብሽሽት ጉዳቶች በእግር ኳስ ከሚያጋጥሙ ጉዳቶች 10-11% ድርሻውን ይወስዳሉ፡፡ እነዚህ ጉዳቶች በተደጋጋሚ የሚያገረሹ ሲሆን የተጠቁ ተጫዋቾች ተመልሶ ለመጎዳት ያላቸው እድል ከሌላው ተጫዋች አንጻር በእጥፍ እንደሚጨምር ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

ብሽሽት የምንለው የሰውነት ስፍራ በእግራችን የላይኛው ክፍል ከመራቢያ አካላት ጎን የሚገኘውን እና የተለያዩ ጡንቻዎችን እና ጅማቶችን የሚያቅፈውን አካል ሲሆን የዳሌ ጉዳቶች ደግሞ የዳሌ መገጣጠሚያ ከምንለው (Hip Joint) ጋር የተያያዘ ነው፡፡

በብሽሽት ጉዳት ወቅት እግራችንን ለመክፈት እና ለመዝጋት የምንጠቀማቸው ጡንቻዎች (Adductor and Abductor muscles) እክል ይገጥማቸዋል፡፡ እነዚህ ጡንቻዎች በእግር ኳስ ጨዋታ ወቅት ጥቅም ላይ የሚውሉ በመሆናቸው ለጉዳት የመጋለጥ እድላቸው እጅጉን ከፍ ያለ ነው፡፡ 27% የሚሆኑት የብሽሽት ጉዳቶች በግጭት ምክንያት የሚከሰቱ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ ጡንቻዎቹ የእንቅስቃሴ እና የውድድር ጫና ሲበዛባቸው (overuse) የሚያጋጥሙ ናቸው፡፡

እነዚህ ጉዳቶች ወዲያውኑ የሚከሰቱ አልያም ለረጅም ጊዜ ቆይተው የሚስተዋሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከተለያዩ ቦታዎች ህመሙ ሊመጣ ስለሚችልም በቀላሉ ቦታውን መለየት እና ችግሩን ማወቅ ሊያስቸግር ይችላል፡፡ በርከት ያሉ ጡንቻዎች እና ጅማቶችም በአንድ ጊዜ ሊጎዱ የሚችሉበት እድል አለ፡፡ ለምሳሌ ኳስ በሚመታበት ወይም በሩጫ ወቅት ጡንቻዎች እና መገጣጠሚያዎች እንደዚሁም ጅማቶች በአንድ ላይ የሚጎዱበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል፡፡

ብዙውን ጊዜ ተጫዋቾች እንደዚህ አይነት ጉዳት በሚያጋጥማቸው ወቅት ለማፍታታት እና እግርን በመወጠር ህመሙን ለማስታገስ የሚደረጉ ሙከራዎች ይስተዋላሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ስራዎች ጉዳቱ እንዲባባስ ሊያደርጉ የሚችሉበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡ በተለይም ጉዳቱ ጅማቶች ላይ የተከሰተ ከሆነ ይህ ያጋጥማል፡፡

ተጫዋቾች ለረጅም ጊዜ ኳስን ያለ በቂ እረፍት እና ማሟቂያ በሚጫወቱበት ወቅት የዳሌ መገጣጠሚያቸው እና ጡንቻዎቻቸው ጋር የህመም ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ ቀስ በቀስም የመተርተር አልያም የመላቀቅ ነገር በጅማቶች እና በጡንቻዎች ላይ ያጋጥማል፡፡ ይህም ብሽሽት እና የዳሌን ጉዳት በአንድ ላይ ያቀፈ ነው፡፡

ተጫዋቾች በነዚህ ቦታዎች ላይ መጠነኛ ቢሆን እንኳን ህመም ቢያጋጥማቸው ወዲያውኑ የህክምና ባለሙያን ማማከር አለባቸው፡፡ እነዚህ ህመሞች በቂውን ክትትል እና ህክምና የማያገኙ ከሆነ በጨዋታ መሃል የማገርሸት እና የመባባስ እድላቸው እጅጉን ከፍ ያለ ነው፡፡