U-17 | መድን በመሪነቱ ሲቀጥል ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል

የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከ17 ዓመት በታች ውድድር 2ኛ ዙር ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ሲጀምር መድን በመሪቱ የቀጠለበትን፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ድል የተመለሰበትን ድል አስመዝግበዋል።

በጎፋ ሜዳ 03:00 ላይ አዳማ ከተማ እና መከላከያን ባገናኘው ጨዋታ መከላከያዎች በጨዋታው የመጨረሻው ደቂቃ ባስቆጠሩት ጎል 3-2 አሸንፈው ሊወጡ ችለዋል።

ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በተመለከትንበት ጨዋታ ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት መከላከያዎች ናቸው። ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ በግንባሩ በመግጨት ለመከላከያ ያሬድ ማትዮስ ቀዳሚ ጎል አስቆጥሯል። በዛሬው ጨዋታ በእጅጉ ተዳክመው የቀረቡት አዳማዎች ብዙም ሳይቆዩ የመጀመርያ የሆነውን የጎል ዕድል በፈጠሩበት አጋጣሚ ፍራኦል ጫላ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ አዳማን አቻ ማድረግ ችሏል። በውድድሩ ጎልቶ መውጣት የቻለው ፍራኦል ጫላ እስካሁን ያስቆጠረውን የጎል ብዛት 15 በማድረስ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትቱን እየመራም ይገኛል።

ከዕረፍት መልስ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ብልጫ ወስደው በመጫወት የተሻሉ የነበሩት መከላከያዎች ቢሆኑም ጎል በማስቆጠር ያልተቸገሩት አዳማዎች በነቢል ኑሪ አማካይነት ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር መሪ ሆነዋል። ሆኖም የመከላከያን ጥቃት መቋቋም ሳይችሉ ቀርተው ተቀይሮ የገባው ናትናኤል ኄኖክ ከማዕዘን ምት ተደርቦ የተመለሰውን ኳስ ወደ ጎልነት በመቀየር መከላከያን አቻ አድርጓል። ጫና ፈጥረው መጫወታቸው ፍሬ አፍርቶ የጨዋታው መጠናቀቂያ የዳኛው ፊሽካ በሚጠበቅበት ጊዜ የመከላከያ ጠንካራ አጥቂ መሆኑን እያሳየ የሚገኘው ምስግናው መላኩ ከመሐል ሜዳ የተጣለለትን ኳስ ከተከላካዮች መሐል በፍጥነቱ በመውጣት በጥሩ አጨራረስ ጎል አስቆጥሮ መከላከያ 3 – 2 እንዲያሸንፍ አስችሏል። የመከላከያው አጥቂ ምስግናው መላኩ በውድድሩ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ወደ 12 ከፍ ማድረግ ችሏል።

05:00 ላይ በጎፋ ሜዳ በቀጠለው ኢትዮጵያ መድንን ከሠላም ያገናኘው ጨዋታ በኢትዮጵያ መድን 3 – 1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ደካማ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ጎል ለማስቆጠር ያልተቸገሩት መድኖች ከግራ መስመር ጌታሁን ተጫዋቾችን በመቀነስ ያሻገረውን ኳስ ዳዊት እንድርያስ ወደ ጎልነት ቀይሮት መድኖችን መሪ ማድረግ ችሏል። ኳሱን ተቆጣጥሮ በመጫወት ብልጫ የነበራቸው ሠላሞች ጎል ለማስቆጠር የነበራቸው ጥረት በውጤት ያልታጀበ በመሆኑ ጥረታቸው ሳይሳካ ቀርቷል። የሠላሞች ግብጠባቂ ከግብ ክልልሉ መውጣቱን ተከትሎ ነፃ የግብ ዕድል ያገኘው ተመስገን ያዕቆብ ተረጋግቶ ለመድኖች ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል።

ከዕረፍት መልስ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ከቅጣት ምት ሳሙኤል ገረመው ግሩም ጎል አስቆጥሮ የሠላሞችን የግብ መጠኑን ማጥበብ ችሏል። ከደቂቃዎች በኃላ ተቀይሮ የገባው ይትባረክ ሠጠኝ ለመድን ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በመድን 3 – 1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በሠላሞች በኩል የግራ እግር አጥቂው ያአብስራ ደረጄ እና በኢትዮጵያ መድን በኩል በውድድሩ 11 ጎሎች በከፍተኛ ኮከብ ጎል አስቆጣሪነት እየተፎካከረ የሚገኘው ጌታነህ ካሣይ ወደ ፊት ተስፋ የሚጣልባቸው ተጫዋቾች ናቸው።

በአካዳሚ ሜዳ 03:00 በጀመረው የወጣቶች አካዳሚ እና የአፍሮ ፅዮን ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል። ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት በከድር አሊ አማካኝነት አካዳሚዎች የነበሩ ቢሆንም ከዕረፍት መልስ ለአፍሮ ፅዮኖች በኃይሉ ንጉሴ የአቻነት ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

05:00 በቀጠለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ኢትዮጵያ ቡና ያገናኘው ጨዋታ በኢትዮ ኤሌክትሪክ 2 – 0 አሸናፊነት ተጠናቋል። አኑዋር ሙራድ ከዕረፍት በፊት ባስቆጠረው ጎል መምራት ጀምረው በሁለተኛው አጋማሽ በረከት ምትኩ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በኢትዮ ኤሌክትሪክ 2 – 0 አሸናፊነት ተፈፅሟል።

10:00 በጃንሜዳ በተካሄደው የመጨረሻ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሀሌታ ያገናኘው ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-1 አሸንፏል። ከቅጣት ምት ፀጋዬ አበራ ባስቆጠረው ጎል መምራት ሲችሉ ከደቂቃ በኃላ ከማዕዘን ምት ሀብታሙ ደሴ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ከዕረፍት መልስ አላዛአር ሳሙኤል ሦስተኛ ጎል አክሎ ፈረሰኞቹ ቢመሩም ለሀሌታ ማስተዛዘኛ የሆነች ጎል ሐብታሙ ዓለማየሁ አስቆጥሮ ጨዋታው 3 – 1 አሸናፊነት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡