ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ (ምዕራፍ አራት-ክፍል ስድስት)

በእንግሊዛዊው የእግርኳስ ጸኃፊ ጆናታን ዊልሰን ደራሲነት በ2008 ለንባብ የበቃው Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics ን በሶከር ኢትዮጵያ በተከታታይ ክፍሎች እያቀረብንላችሁ እንገኛለን፡፡ በዛሬው መሠናዶም የምዕራፍ አራት የመጨረሻ ክፍል እንዲህ ይቀርባል፡፡

|| ያለፈውን ሳምንት ለማንበብ ይህን ይጫኑ LINK

የሲንድለር ህልፈት እና የቡና መጠጫ ቤቶች ፍፃሜ

የሲንድለር የጨዋታ ዘመን ወደ መጠናቀቁ ሲቃረብ፥ ሜይዝልም እድሜው እየገፋ ሲሄድ የዳኑቢያኑ የእግርኳስ አጨዋወት ስልት የመክሰም ምልክት አሳይተው ነበር፡፡ በፖለቲካው መስክ የተፈጠሩ እድገቶች ደግሞ ተወዳጁ የጨዋታ አቀራረብ ዘይቤ ከገደል አፋፍ ላይ መድረሱን ይበልጥ አረጋገጡ፡፡ ኦስትሪያ በጀርመን ማዕቀፍ ውስጥ መጠቃለሏን (Anschluss) ተከትሎ በማዕከላዊው አውሮፓ የከተሙ አይሁድ ምሁራን መመናመን፣ የቡና መጠጫ ቤቶቹ ደማቅ ድባብ መደብዘዝና የሲንድለር ሞት እግርኳሳዊው ብልጽግና ላይ ደንቃራ መሰናክል ፈጠሩ፡፡

1930ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ታላቁ ኦስትሪያዊ የመሐል አጥቂ ከብሔራዊ ቡድኑ እየራቀ ቢሄድም ሚያዝያ 3-1938 ለሚደረገው እና “እርቅ የማውረድ ጨዋታ” ተብሎ ለሚጠራው፣ በኦስማርክ ምርጥ አስራ አንድና በጀርመን መካከል ለሚካሄደው ግጥሚያ ራሱን አዘጋጀ፡፡ በዚያን ጊዜ የጀርመን እግርኳስ የአስትሪያን ያህል እድገት ባይኖረውም መጠነኛ መሻሻሎችን እያሳየ ነበር፡፡

ሐምሌ 1-1926 በሃገሪቱ የመጀመሪያ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ተደርጎ የተሾመው ኦቶ ነርዝ ከቀዳሚዎቹ የW-M ፎርሜሽን ደጋፊዎችና ተግባሪዎች መካከል አንዱ ነበር፡፡ በእርግጥ በሼልከ 04 የጂሚ ሆጋን መሰረታዊ የእግርኳስ አቀራረብ አስተምህሮ ሰርጾ ስለኖረ በሃገሪቱ ቀደም ብሎ ከ3-2-2-3 የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር ስርዓት ጋር የተያያዘ ግንዛቤ ተፈጥሯል፡፡ ነርዝ ከ1933-1942 በተከታታይ ከተካሄዱ አስር የጥሎ ማለፍ ሻምፒዮናዎች በዘጠኙ ፍጻሜ መድረስ የቻለ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ስድስቱን የዋንጫ ድሎች አሳክቷል፡፡

ሼልከዎች በኦስትሪያዊው አሰልጣኛቸው ጉስታቭ ዌይዘር አማካኝነት <ደር ክራይዘር> ተብሎ የሚጠራ፣ ፍጥነት ላይ ተመሰርቶ ተደጋጋሚ የምልልስ ዑደት የሚታይበትን እንቅስቃሴ የያዘ አጨዋወት መተግበር ጀመሩ፡፡ እንደ ተከላካዩ ሃንስ ቦርንማን ገለጻ በሼልከ ኳሱን እግሩ ስር ይዞ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ከሚመራው ተጫዋች ይልቅ ከኳስ ውጪ በሜዳው ውስጥ ወደሚገኙ ክፍት ቦታዎች የሚሮጡና ክፍተቶችን ለመጠቀም የሚሞክሩ ተጫዋቾች የማጥቃት ማዕዘኖችን ይወስናሉ፡፡ ” ሁሉንም የተጋጣሚዎቻችን ተከላካዮች ካለፍን በኋላ በመጨረሻው የማጥቃት ሲሶ ቀላል ቅብብሎችን ከውነን ግቦችን እናስቆጥራለን፡፡” ይላል ሃንስ ቦርማን የማጥቃት ሒደታቸውን ሲያብራራ፡፡ በእርግጥ የዚያን ጊዜ ሆጋን የአጨዋወት ዘይቤያቸውን ቢወድላቸውም የቡድኑን መዋቅራዊ ስርዓት በሚመለከት ግን ጥያቄ ማንሳቱ አልቀረም፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ገደቡን ያለፈ፣ ዝርክርክና በጥብቅ መዋቅራዊ ስርዓት ያልተደገፈ እግርኳሳዊ አካሄድ ነርዝን ረበሸው፤ ስለዚህም ሁለቱን የሼልከ አንጋፋ የፊት አጥቂዎች ኧርነስት ኩዞራና ፍሪትዝ ዝፓንን ወደ ብሄራዊ ቡድኑ ላለመቀላቀል ወሰነ፡፡ (በእርግጥ ዝፓንን ለ1934ቱ የዓለም ዋንጫ መርጦት ግራ በሚያጋባ ሁኔታ በመሐል ተከላካይ-አማካይነት /Centre-Half/) ሚና ተጠቅሞበታል፡፡) የአሰልጣኙን ውሳኔ በተመለከተ ኩዞራ ሲያስረዳ “ነርዝ ጠራኝና ‘የሆነ ነገር ልነግርህ እፈልጋለሁ፤ አንተ በሼልከ የምታሳየው ቅብብሎች ላይ ያተኮረው ለየት ያለ ቴክኒካዊ አቀራረብህና አጨራረስህ ቅንጣት ታህል  ምቾት አልሰጠኝም፤ አንተና ዜፓንን አንድ ላይ ባሰልፋችሁ ውጤቱ ያው ፋይዳ ቢስ ድሪብሊንግና አመርቂ ያልሆነ እንቅስቃሴ ነው፡፡’ አለኝ፡፡” ይላል፡፡ 

በ1934ቱ የዓለም ዋንጫ ጀርመን የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚ ነበረች፤ እናም በቀጣይ በሃገሯ የምታዘጋጀው የ1934 ኦሊምፒክ ላይ ብዙዎች የወርቅ ሜዳዩን እንደሚያሸንፉ ተስፋ የሚያሰንቅ ማበረታቻ ሆናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የታሰበው ሳይሆን ቀረና በውድድሩ የመጀመሪያው ጨዋታ ላይ ጀርመኖች በአሳፋሪ ሁኔታ በኖርዌይ 2-0 ተረቱ፡፡ ለነርዝ ያለመታደል ሆኖ አዶልፍ ሒትለር በህይወቱ ስታዲየም ተገኝቶ የተመለከተው ብቸኛው ጨዋታ በሽንፈት ተጠናቀቀ፡፡ 

የነርዝ ረዳት የነበረውና በ1954ቱ የዓለም ዋንጫ ምዕራብ ጀርመንን ወደ ድል ጎዳና የመራት ሴፕ ኸርበርገር በሌላ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ጣልያን ጃፓንን ስትገጥም ለማየት ሄዶ በስታዲየሙ አልታደመም፡፡ እዚያ እያለ አንድ አሰልጣኝ ወደ እርሱ ተጠግቶ የጀርመንን መሸነፍ ሲያረዳው በቡድኖቹ ማረፊያ የአሳማ ስጋና የተጠበሰ ጎመን የተቀላቀለበት እራቱን በመመገብ ላይ ነበር፡፡ ኸርበርገር ይህን ጉድ ሲሰማ የምግብ ገበታውን አሽቀንጥሮ ጣለው፤ ከዚያ ጊዜ በኋላም እድሜውን ሙሉ የአሳማ ስጋ ሳይመገብ ኖረ፡፡

ውድድሩ ከተጠናቀቀ በኋላ ነርዝ በሴፕ ተተካ፡፡ የቡድኑ አጨዋወትም ወዲያውኑ ወደ ዳኑቢያኑ ዘይቤ ተቀየረ፡፡ አዲሱ አሰልጣኝ አዶልፍ ኧርባንና ሩዲ ጊሌችን ከሼልከ አመጣ፤ በአልኮል መጠጥ ሱሰኝነቱ የሚታወቀው ድንቅ የፊት መስመር ተሰላፊ (Inside Forward) ኦቶ ሲፍሊንግን ከደቡባዊ ምዕራብ የሃገሪቱ ክለብ ማንሄይም ጠርቶ በመሃል አጥቂነት (Center-Forward) እንዲሰለፍ እድሉን ሰጠው፡፡ የለውጡ ውጤት ግንቦት 16-1937 ቡድኑ የብቃቱ ጫፍ ላይ ሲደርስ ታየ፡፡ በቀድሞ መጠሪያው ብሬስሎ (አሁን-ውሮክሎ) በተባለው ከተማ ጀርመኖች ከዴንማርክ ጋር ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ 8-0 ሲረቱ ታላቅ ወደ መሆን ተሸጋገሩ፡፡ ” የሮቦት ስሪት ያላቸው የሚመስሉት ሰዎች ጀርመን ከገናናነቷ ማማ ቁልቁል ስትምዘገዘግ መመልከትን ይሻሉ፤ ያም ሆኖ ጥበባዊ ይዘትን የተላበሰው እግርኳስ ድል ያደርጋል፡፡” ሲል ገርድ ክራመር የተባለው የሃገሪቱ ጋዜጠኛ ጻፈ፡፡ 

ይሁን እንጂ ጀርመኖች የኦስትሪያን ያህል  ባለክህሎት አልያም ውብ እግርኳስን የሚተገብሩ አልነበሩም፡፡ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ እርቅ ለማስፈን ተብሎ የሚካሄደውን ውድድር ኦስትማርክ ነገሰችበት፡፡ እውነታው እየተደጋገሙ በሚቀርቡ አፈታሪኮች ቢደበቅም ሲንድለር በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በርካታ፣ ተከታታይና የጠሩ እድሎችን ማምከኑ እሙን ነው፡፡ የተጋጣሚ ግብ ክልል ውስጥ ከጎሉ ቋሚዎች ጥቂት በራቀ የጎንዮሽ አቅጣጫ ኳሷን እግሩ ስር አድርጎ ብዙ ጊዜ ሲያንከባልላት ላስተዋለ እነዚያን ጥሩ ግብ የማስቆጠር ሙከራዎች ሆን ብሎ የሚያባክናቸው ይመስል ነበር፡፡ እንዲያውም የዚያን ዘመን ዘገባዎች ተጫዋቹ  ጀርመኖች ላይ እየቀለደ እንደሆነ፣ ግብ እንዳያስቆጥርም የበላይ ትዕዛዝ እንደደረሰው ሲያትቱ ታይተዋል፡፡ ይህም ሆኖ በጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ ዕኩሌታ ሲቃረብ ግን ሲንድለር ግብ አስቆጠረ፤ ጓደኛው ሻስቲ ሴስታ ደግሞ በቅጣት ምት ሁለተኛው ጎል አከለ፡፡ በዚህ ጊዜ ተጫዋቹ ደስታውን መቆጣጠር ተስኖት ከፍተኛ የናዚ ባለስልጣናት እና ዳይሬክተሮች በተቀመጡበት ስፍራ ሄዶ ጨፈረ፡፡ 

በቀጣዩ ወር ሃገር ያወቃቸው፥ ጸሃይ የሞቃቸው ማኅበራዊና ዴሞክራሲያዊ ዝንባሌዎች ቢኖሩትም ሲንድለር ለሴፕ ኸርበርጉሩ የተባበሩት የጀርመን ሃገራት ለመጫወት አቅማማ፤ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲደረግለትም “እምቢኝ!” አለ፡፡ በዚያው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ አዲስ በወጣው የንግድ መመሪያ መሰረት ለመስራት ፍላጎት ካጣ ሊኦፖልድ ድሪል የተባለ አይሁዳዊ ሰው በሃያ ሺህ የደች ማርክ አንዲት ትንሽ ካፌ ገዛ፡፡ ሻጩ የናዚን ባለስልጣናት ምስሎች ግድግዳው ላይ ለመለጠፍ ፍቃደኝነት ባለማሳየቱ ከፍተኛ ነቀፌታ ቀርቦበት ስለነበር ዋጋው ፍትሃዊ አልያም የተገኘውን አጋጣሚ የመጠቀም ተግባር ይሁን ማንም አካል የመረጠውን የማመን መብት ይኖረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጥቂቶች እንደሚገምቱት ተጫዋቹ የወቅቱን መንግስት ተቃዋሚ ብሎ መፈረጅ ነገሩን ከተገቢው በላይ ማራገብ ተደርጎ ሊታሰብ ይችላል፡፡ 

በጥር 23-1939 ማለዳ የሲንድለር ወዳጅ ጉስታቭ ኸርትማን ጓደኛውን ፍለጋ <አናጋሴ> ጎዳና አካባቢ ይኖር የነበረበትን አፓርታማ በር ቁልፍ ሰብሮ ሲገባ በሚያስደነግጥ ሁኔታ የተጫዋቹን እርቃን በድን አገኘ፡፡ ለአስር ቀናት ህሊናዋን ስታ የሰነበተችው ፍቅረኛው ካሚላ ካስቶኚላም ከጎኑ ተዘርራ ተኝታ ነበር፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሆስፒታል ውስጥ አረፈች፡፡ የሁለቱም የሞት መንስኤ ከተበላሸው የቤታቸው ማሞቂያ በሚወጣው ካርቦን-ሞኖክሳይድ በተባለ መርዛማ ጭስ መታፈናቸው እንደሆነ ተነገረ፡፡ 

ለሁለት ቀናት ብቻ ማስረጃዎችን የማፈላለግ ሒደት ቀጠለና ፖሊስ የሁለቱም ሰዎች ህልፈት ዋነኛ ምክንያት መርዛማው ጭስ እንደሆነ ካሳወቀ በኋላ ምርምራውን አቆመ፡፡ የናዚ ባለስልጣናት ከስድስት ወራት በኋላ የምርመራው ሰነድ እንዲዘጋ ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ አቃቤ ህግ ግን ገና ድምዳሜ ላይ አልደረሰም ነበር፡፡ በ2003 በBBC በተዘጋጀ ዘጋቢ ፊልም ኢጎን ኧልብሪች የተባለ የሲንድለር ጓደኛ ” የሃገሪቱ ፖሊስ የተጫዋቹን ሞት መንስኤ ድንገተኛ አደጋ አድርጎ እንዲያቀርብና በመዝገብ ላይ እንዲሰፍር በጉቦ ተደልሏል፡፡ በዚህም ብሄራዊ ስርዓተ-ቀብር እንዲደረግለት ሁኔታዎችን አመቻችቷል፡፡” ይላል ጥርጣሬውን ሲገልጽ፡፡ ሌሎች አካላትም እንዲሁ የየራሳቸውን ማብራሪያዎች ለማቅረብ ሞክረዋል፡፡ በጥር 25 ቀን <ክሮነን ዜይቱንግ> የተሰኘ የኦስትሪያ ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ጽሁፍ ” ሁሉም መረጃዎች የሚጠቁሙት ይህ ታላቅ ሰው በመርዛማ ጭስ ሳቢያ የሞት ሰለባ መሆኑን ነው፡፡” አለ፡፡ ጋዜጣው <ባላድ ኦን ዘ ዴዝ ኦፍ ኤ ፉትቦለር> በተባለው አወዳሽ የግጥም ቋጠሮው ተጫዋቹ በአዲሱ የመንግስት ስርዓት የመከዳት ስሜት ውስጥ ስለቆየ ራሱን አጥፍቶ ሊሆን እንደሚችል አተተ፡፡

የዝነኛውን ተጫዋች ህልፈት የተመለከቱ መላምቶች መውጣታቸውን ቀጠሉ፡፡ ሲንድለርም ሆነ ፍቅረኛው ካስቲኞላ የአይሁድ እምነት ተከታዮች በመሆናቸው የደረሰባቸው ምጣት ስለመሆኑ የገመቱም አልታጡም፡፡ በእርግጥ ሲንድለር በአይሁድ ከበርቴዎች በሚደገፈው ኦስትሪያ-ቪየና ክለብ ተጫውቷል፤ በርካታ አይሁዳውያን ወደ ርዕሰ መዲናዋ ከሚፈልሱባት ሞራቪያ የተባለች ከተማ ውስጥ መወለዱም እሙን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ቤተሰቦቹ ካቶሊኮች ነበሩ፡፡ የፍቅር አጋሩ ጣልያናዊቷ ካስቲኞላም የአይሁድ ዘር እንዳለባት  ይታሰብ ይሆናል፤ ዳሩ ግን ከመሞቷ አንድ ሳምንት በፊት የአንድ መጠጥ ቤት የጋራ ባለቤትነት ፍቃድ እስከማግኘት ደርሳለች፡፡ ይህም ጥንዶቹ ድብቁን ሃይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ ስብዕና በአግባቡ ስለማሰንበታቸው ምስክር ይሆናል፡፡ እጅጉን የሚገርመው ደግሞ በነሲንድለር ቤት ከተገጠሙ ጪስ ማውጫዎች መካከል አንደኛው ችግር እንደነበረበት የሟቾቹ ጎረቤቶች አደጋው ከመከሰቱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ቅሬታ ሲያቀርቡ እንደነበር የሚያሳብቁ መረጃዎች መውጣታቸው ነው፡፡  

እንግዲህ የሲንድለርን ሞት አስረጅ ሰነዶች በሙሉ ድንገተኛ አደጋ መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡ ያም ሆኖ ከተጫዋቹ ህልፈት ጋር ተያይዞ  “ጀግኖች እንዲሁ በቀላሉ አይሞቱም፡፡” የሚለው ብሂል ብዙ ተባለበት፡፡ ሆነም ቀረ እጅጉን ነጻነት የተጎናጸፈ አዕምሮ ባለቤት ከሆነው፣ ተወዳጁና ጥበበኛው የእግርኳስ ልሂቅ በላይ ከ1938 በኋላ በጀርመን ስር የተጠቃለለችው ሃገረ ኦስትሪያ ማን ተምሳሌቷ ሊሆን ይችላል? እንዴትስ ይህ የቪየናማውያን ማኅበረሰብ ውድ ልጅ ከአይሁዳዊት ፍቅረኛው ጋር በኬሚካላዊ አጸግብሮት ተመርዞ ተገኘ? “የመዲናይቱ ተደናቂ ልጅና የህዝቡ ኩራት የነበረው ሲንድለር አይቀሬውን ሞት ተቀበለ፡፡” በማለት ፖግላር ዜና እረፍቱን በማስመልከት ጻፈ፡፡ “ሲንድለር ከውስብስብና ጥልፍልፍ ያሉ ችግሮች ጋር ተቆራኝቶ ኖሮ ትብትብ ተግዳሮቶቹ ይበልጥ ሲከፉ አረፈ፡፡ ለመሞቱ በመንስኤነት የተጠቀሱት ማስረጃዎች እርሱ ለትውልድ ሃገሩ የነበረው ጥልቅ ፍቅርና ታማኝነት ራሱን ለማጥፋት የሚገፋፋ ውሳኔ ላይ እንደደረሰ የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡” ሲልም ጋዜጠኛው አከለ፡፡ ፖግላር ጥያቄውን ቀጥሏል፤ “የጭቆና በትር እጅጉን ባጎሳቆላት፣ በከፍተኛ ስቃይ በምታቃትትና የህዝቧ ሞራላዊ እሴቶች እንክትክት ባሉባት ከተማ እግርኳስን መጫወት ቪየና እና የሚወዳቸው ነዋሪዎቿ ላይ ክህደት መፈጸም ሆነበት፡፡ ያን ካደረገ ራሱን እንደ አሰፈሪ የሙት መንፈስ እንደሚያይ ቆጠረ፡፡ በዚህ ስሜት ውስጥ ያለ አንድ ሰው እንዴት አድርጎ እግርኳስ መጫወት ይችላል? ለእርሱ እግርኳስን ሳይጫወት የመኖር ፋይዳስ ምንድን ነው?” ሲልም ጠየቀ፡፡ 

በመጨረሻም ቡና መጠጫ ቤቶቹ ላይ የተጸነሰው ሃሳባዊው እግርኳስ በጀብደኝነት የሚታወስ ተወዳጅ ጨዋታ ሆኖ ዘለቀ፡፡ 

ይቀጥላል...


ስለ ደራሲው 

ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡  ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም የሚከተሉትን ዘጠኝ መጻህፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡

Behind The Curtain: Travels in Eastern European Football (2006)

Sunderland: A Club Transformed (2007)

Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics (2008)

The Anatomy of England (2010)

Brian Clough: Nobody Ever Says Thank You: The Biography (2011)

The Outsider: A History of the Goalkeeper (2012)

The Anatomy of Liverpool (2013)

Angels With Dirty Faces: The Footballing History of Argentina (2016)

The Barcelona Legacy: Guardiola, Mourinho and the Fight For Football’s Soul (2018)