“ይህ ለእኛ ጥሩ ጊዜ ነው” ሙጂብ ቃሲም

ፋሲል ከነማ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ሆኖ ለማጠናቀቅ ለሚያደርገው ግስጋሴ ትልቁን ሚና እየተወጡ ካሉት ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። ዐፄዎቹ በዘንድሮ የውድድር ዘመን ወደ ክለባቸው ሲያመጡት የግብ ክልላቸውን በንቃት እንዲከላከል በማሰብ እንደሆነ ይታመናል። ሆኖም አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በአጥቂ ስፍራ ላይ የሚጫወቱ ተጫዋቾቻው በሚፈልጉት ደረጃ ጎል የማስቆጠር አቅማቸው እንዳሰቡት ሆኖ አለማግኘታቸውን ተከትሎ በሒደት (በተለይም በሁለተኛው ዙር) በፊት አጥቂነት በማጫወት ውጤታማ እየሆኑ መጥተዋል። ሙጂብ በሲዳማ ቡና፣ በሀዋሳ ከተማ እና በአዳማ ከተማ መከላከል በሚያስፈልግበት ወቅት በጠንካራ መከላከልን፤ ማጥቃት በሚያስፈልግ ጊዜ ደግሞ በማጥቃቱ ላይ እገዛ እያደረገ አቅም እንዳለው አሳይቷል። ዘንድሮም በዐፄዎቹ መለያ እስካሁን 12 ጎሎችን በማስቆጠር ለከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ክብር እየተፎካከረ ይገኛል። በትናትናው ዕለት ፋሲል ከነማ ጅማ አባጅፋርን በበላይነት 6-1 ባሸነፈበት ጨዋታ አራት ጎሎችን በማስቆጠር ደምቆ የዋለው ሙጂብ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በወቅታዊ አቋሙ ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ወቅቱ የቅዱሱ ረመዳን የፆም ወር ነው። ፆም እና እግርኳስ መጫወት እንዴት ነው? ይከብዳል?

ከባድ ነው። ፆም እና እግርኳስን አንድ ላይ ማስኬድ ይከብዳል። የረመዳን ወርን ከቤተሰብ ጋር ሆነህ ብታሳልፍ መልካም ነው። ከባድ የሆኑ ስራዎችን እየሰራህ፤ በተለይ እግርኳስ ደግሞ ያወጣኸውን ጉልበት ለመተካት መመገብ ፣ ፈሳሽ ነገሮችን መውሰድ አለብህ። ያው ከባድ ቢሆንም የፈጣሪን ትዕዛዝ ተቀብለን ከፆም ጋር ፈጣሪም ረድቶኝ የተሻለ ነገር አድርጌ መውጣት ችያለው።

የፋሲል ከነማ በሊጉ እያደረገ ያለው የዘንድሮ ዓመት ጉዞ እንዴት ትገልፀዋለህ? ለቡድኑ አዲስ ተጫዋች እንደመሆንህ መጠን…

አሪፍ ነው። ጥሩ ነገር እየሰራን እንገኛለን። ወደ ውድድሩ ጅማሮ አካባቢ በሜዳችንም ከሜዳ ውጭ ነጥቦችን እንጥል ነበር። ይሄ ደግሞ አሁን ላይ ሆነን ስናስበው ከዚህ በላይ መራቅ የምንችልበትን እድል ነው ያበላሸነው። ሆኖም ይህን አስተካክለን በተሻለ መልኩ ሁለተኛው ዙር ካደረግናቸው ጨዋታዎች በአንድ ጨዋታ ብቻ ነው ነጥብ ተጋርተን የወጣነው እንጂ አጠቃላይ ጨዋታዎችን አሸንፈን ወጥተናል። ይህ ለእኛ ጥሩ ጊዜ ነው።

ክለብህ ሲያስፈርምህ በእርግጠኝነት ተከላካይ አድርጎህ ነው። ሆኖም በአስገዳጅ ሁኔታ በአጥቂነት እንድትጫወት ተደርገህ ጎሎችም እያስቆጠርክ ነው። ይህንን ሽግሽግ እንዴት ትገልፀዋለህ?

አዎ። ፋሲል ከነማ ለመጫወት ፊርማዬን ያኖርኩት እንደሚታወቀው በተከላካይ ስፍራ ቡድኑን ለማገዝ ነው። የእኔም ውስጤ የሚያምነው ፍላጎቴም በተከላካይ ስፍራ መጫወትን ነው። ሆኖም እንደ አሰልጣኝ ደግሞ አምኖብህ በዚህ ቦታነው መጫወት ያለብህ ስትባል ያንን የመቀበል ኃላፊነት አለብህ። ስለዚህ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ባዘዘኝ መልኩ ፍላጎቱን ለማሟላት ያለኝን አቅም አውጥቼ እያገለገልኩ እገኛለው። ስራ እስከሆነ ድረስ የትም ቦታ ተጫውተህ የሚጠበቅብህን አቅም አውጥተህ መስራት አለብህ። በዚህም ደስተኛ ነኝ።

ሙጂብ በእግርኳስ ህይወቱ ባለፈባቸው ክለቦች በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተጫውቷል። ለምሳሌ ግብጠባቂ ፣ ተከላካይ እና አጥቂ። ይህ ሁለገብ ሆኖ የመጫት ልማድን ከየት ያዳበርከው ነው?

ወደ ክለብ ገብቼ መጫወት ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ ነው ይህ በተለያዩ ቦታዎች የመጫወት ልምድ የመጣው። በዋናነት ሁለገብ ሆኜ መጫወት የጀመርኩት በሲዳማ ቡና ነው። አንተም እንዳልከው ለደቂቃዎችም ቢሆን ግብ ጠባቂ ሆኜም መጫወት ችያለው። ያው እግርኳስ በሜዳ ውስጥ የሚፈጠረው ነገር ስለማይታወቅ ተጫዋች ስትሆን ለሁሉም ነገር ራስህን ማዘጋጀት ስላለብህ ከዚያ ይመስለኛል የተለያዩ ቦታዎችን ሸፍኜ የመጫወት ልምዱን ያዳበርኩት።

በሊግ ውድድሮች ላይ በአንድ ጨዋታ አራት ጎሎች አስቆጥረህ ታውቃለህ? አራት ጎል በአንድ ጨዋታ ማስቆጠር ስሜቱ እንዴት ነው?

በፍፁም አላውቅም፤ ይህ በእግርኳስ ህይወቴ የመጀመርያዬ ነው። እንኳን አራት ጎል ሦስት ጎል አስቆጥሬ አላውቅም። በአንድ ጨዋታ ሁለት ጎሎች ያስቆጥኩበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል። ስሜቱ ከባድ ነው፤ ዛሬ በጣም ነው ደስተኛ የነበርኩት። በተለይ አሁን ካለው ፉክክር መቐለ ተሸንፎ እኛ ወደ ሊጉ አናት ላይ መቀመጣችን ይበልጥ ደስታዬን እጥፍ ድርብ አድርጎታል።

በአስራ ሁለት ጎሎች ከአማኑኤል ገ/ሚካኤል እና ከአዲስ ግደይ በሦስት ጎሎች አንሰህ ለከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት እየተፎካከርክ ትገኛለህ። በቀጣይ ምን ታስባለህ?

በመጀመርያ እኔ የማስበው የቡድኑ ውጤት ላይ ነው። በውስጤ ያለው ሀሳብ ይሄ ነው። ምክንያቱም ኮከብ ጎል አግቢ እሆናለው አልሆንም እኔን አያሳስበኝም። እንደምታውቀው የውድድሩ ጅማሮ ላይ ተከላካይ ስለነበርኩ ይሄን ያህል ጎል አስቆጥራለው ብዬ አላሰብኩም። አቅጄም የተነሳሁት ነገር የለም። ቡድኔ ሲቸገር ነው ወደ ማጥቃቱ ያመራሁት አሁን ላይ 12 ጎሎች አሉኝ። ለክለቤ ጥቅም ቅድሚያ ሰጥቼ የተሻለ ነገር ለመስራት በቀሩት ጨዋታዎች የምችለውን ለማድረግ ነው የምፈልገው።

እንዳልከው ፋሲል ከነማ የሊጉ መሪነትን ከመቐለ ተረክቧል። በቀሪ አምስት ጨዋታዎች መሪነቱን አስጠብቆ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ እንደ ቡድን እንዲሁም በግልህ ምን ለማድረግ ታስባለህ ?

አሁን ቡድኑ ላይ ያለው መንፈስ ዋንጫውን ማሳካት ነው። ምክንያቱም በሁለተኛው ዙር ስንጀምር በእኛ እና በመቐለ መካከል የአስር ነጥብ ልዩነት ነበረን። ያንን የሚያክል የነጥብ ልዩነት አጥብቦ እዚህ ደረጃ መድረስ በመጀመርያ ትልቅ ነገር ነው። እዚህ ስብስብ ውስጥ የሊጉን ዋንጫ ያላየን ተጫዋቾች እንበዛለን። በቡድኑ ውስጥ ያለው መንፈስ የውድድሩ አሸናፊ ሆኖ ማጠናቀቅ ስለሆነ ያለንን አቅም ተጠቅመን የተሻለ ነገር ለማድረግ እንሰራለን። ግን ፉክክሩ ከባድ እንደሆነም እናውቃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡