ከፍተኛ ሊግ ለ | ተጠባቂው ጨዋታ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ የወልቂጤ እና ዲላ ጨዋታ ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ 18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እሁድ ሲከናወኑ የወልቂጤ እና ዲላ ከተማ ጨዋታ በዝናብ ምክንያት ተቋርጦ ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል።

ዲላ ላይ ዲላ ከተማ ከወልቂጤ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 በሆነ ውጤት ላይ ሳለ በጣለው ዝናብ ምክንያት ተቋርጧል። በ16ኛው ደቂቃ ላይ ቢንያም በቀለ ለዲላ ጎል ሲያስቆጥር በአራት ደቂቃ ልዩነት ሐብታሙ ታደሰ ለወልቄጤ የአቻነቱን ግብ አስቆጥሯል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናግድበት የመጀመሪያው አጋምሽ ላይ በእለቱ በጣለው ዝናብ ሳይካሄድ ቀርቶ ለዛሬ ተላልፎ የነበረ ቢሆንም ማለዳ ላይ ተጨማሪ ዝናብ በመጣሉ ጨዋታው ሳይከናወን ቀርቷል። በዚህም በሀዋሳ ሜዳ ላይ ለማከናወን ታስቦ የነበረ ቢሆንም ዲላ በበጀት እና ትራንስፖርት ቀድሞ ባለማዘጋጀቱ ምክንያት በተስተካካይ መርሐ ግብር ወደፊት በፌዴሬሽኑ በሚገለፅ ቀን ይካሄዳል።

በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ኢኮስኮ እና ኢትዮጵያ መድን መድን ሜዳ ላይ ተጫውተው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል። ኢኮስኮች በ22ኛው ደቂቃ ላይ አባይነህ ፋኖ ባስቆጠራት ግብ መሪ በመሆን የመጀመሪያውን አጋማሽ ሲያጠናቅቁ በ62ኛው ደቂቃ ፈጣኑ አጥቂ አብዱልለጢፍ ሙራድ መድንን አቻ አድርጓል።

ዱራሜ ላይ ሀምበሪቾ ድሬዳዋ ፖሊስን 4-0 አሸንፏል። 25ኛው እና 76ኛው ደቂቃ ላይ ዘካርያስ ፍቅሬ እንዲሁም 30ኛው እና 65ኛው ደቂቃ ላይ ተስፋሁን ተሰማ ግቦችን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው። ሀላባ ላይ ሀላባ ከተማ ከየካ ያደረጉት ጨዋታ በመጨረሻው ደቂቃ በተቆጠረ ግብ ሀላባ 1-0 አሸንፏል። የሀላባን በረቸኛ የማሸነፍያ ጎል በ89ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው አቡበከር ወንድሙ ነው። ሶዶ ከተማ በሜዳው አዲስ አበባ ከተማን አስተናግዶ 1-0 አሸንፏል። በ44ኛው ደቂቃ አገኘው ከተፋ ብቸኛውን የድል ግብ አስቆጥሯል። አርሲ ነገሌ ላይ ነገሌ አርሲ ከ ናሽናል ሲሚንት ያለምንም ግብ የተጠናቀቀ የዚህ ሳምንት ላላው ጨዋታ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡