የከፍተኛ ሊግ ወሳኝ ጨዋታዎች እና ሌሎች መረጃዎች

የምድብ ሐ ሁለት ጨዋታዎች አይከናወኑም

የከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ 20ኛ ሳምንት አራት ጨዋታዎች ነገ ሲደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ግን ወደ ሌላ ጊዜ መሸጋገራቸውን የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ አስታውቋል። በነቀምት ከተማው ተጫዋች ወንድወሰን ዮሐንስ ድንገተኛ ህልፈት ምክንያት ነቀምት ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው አርባምንጭ ከተማ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ የማይኖር በመሆኑ የመሪው ሀዲያ ሆሳዕና እና ከምባታ ሺንሺቾ ጨዋታ መራዘሙን አቶ ኢብራሂም አህመድ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል። ” ሊጉ ውበቱን ጠብቆ እንዲጓዝ የሁለቱ ጨዋታን በይደር አቆይተነዋል። ሌሎቹ ጨዋታዎች ግን ይደረጋሉ፤ በተመረጡ ጨዋታዎች ላይም ተጨማሪ ተቆጣጣሪዎች ተልከዋል። ” ያሉት አቶ ኢብራሂም በነቀምቱ ተጫዋች ወንድወሰን ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘንም በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስም ገልፀዋል።

ሁለት ተፎካካሪዎች የቀሩበት የምድብ ሀ ትንቅንቅ

በምድብ ሀ ባለፈው ሳምንት ደሴ ከተማ ተስተካካይ ጨዋታውን ከወሎ ኮምቦልቻ ጋር አድርጎ አቻ በመለያየቱ ከምድቡ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማለፍ የሚደረገው ፉክክር በሰበታ ከተማ እና ለገጣፎ ለገዳዲ መካከል ሆኗል። በ20ኛው ሳምንት ሁለቱም ቡድኖች ጠንካራ ጨዋታ የሚጠብቃቸው ሲሆን ሰበታ ከተማ ከ ደሴ ከተማ፤ ለገጣፎ ለገዳዲ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ይጫወታሉ።

የአራት ነጥብ ልዩነት ይዞ ምድቡን እየመራ የሚገኘው ሰበታ ከተማ አንድ እግሩን ወደ ፕሪምየር ሊጉ የማስገባት አላማን አንግቦ ደሴ ከተማን በሜዳው ያስተናግዳል። ሰበታ ይህን ጨዋታ አሸንፎ ለገጣፎ የሚሸነፍ ከሆነም ከ2003 በኋላ ዳግም ወደ ሊጉ መመለሱን የሚያረጋግጥ ይሆናል።

በአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና እየሰለጠነ የሚገኘው ሰበታ ከተማ በውድድር ዓመቱ እስካሁን ሽንፈት ያላስተናገደ ብቸኛው የከፍተኛ ሊግ ቡድን ሲሆን ደሴ በአንፃሩ በሁለተኛው ዙር ከየትኛውም ቡድን በተሻለ ከፍተኛ ማንሰራራት አሳይቶ ሦስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።

በጨዋታው ዙርያ የሰበታ ከተማው አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ለሶከር ኢትዮጵያ ይህን ብለዋል። ” ጨዋታው ከበድ ይላል። ምክንያቱም ደሴ ከተማ በሁለተኛው ውድድር አጋማሽ ተጠናክሮ የቀረበ ቡድን ነው። ሆኖም ቡድኔ ከመቼውም ጊዜ በላይ በሥነ ልቦናም ሆነ በአካል ብቃት እንዲሁም በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል። በልምምድ ሜዳ ሳለን ከንቲባው ሜዳ ድረስ በመምጣት ተጫዋቾቼንም ሆነ የአሰልጣኙን አባላት አበረታተዋል። አሁን ደጋፊው ላይ ትልቅ መነቃቃት ተፈጥሯል። ይህም ለኛ ሌላ ኃይል ነው። በሜዳችን ያለመሸነፍ ጉዛችንን አስጠብቀን እንጓዛለን። ” ብለዋል።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመርያው ዙር ደሴ ላይ ባደረጉት ጨዋታ ሰበታ 2-1 አሸንፎ ተመልሷል።

ለገጣፎ ለገዳዲ የሰበታን ነጥብ መጣል ተስፋ በማድረግ ከሜዳው ኢትዮ ኤሌክትሪክን ይገጥማል። በወጣቱ አሰልጣኝ ዳዊት የሚመራው ለገጣፎ በአራት ነጥብ የራቀው ሰበታ ከተማን በ21ኛ ሳምንት በሜዳው የሚያስተናግድ እንደመሆኑ ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማግኘት ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት ለሚያደርገው ጉዞ ስንቅ ይሆነዋል።

የለገጣፎው አሰልጣኝ ዳዊት ሐብታሙ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ተጋጣሚያቸው ተቀራራቢ አጨዋወት ያለው መሆኑ እንደሚያመቻቸው ተናግረዋል። ” ተጋጣሚያችን ኳስን መሰረት አድርጎ የሚጫወት ቡድን ነው። በመጀመሪያው ዙር ባደረግነው ጨዋታ በደንብ አይተናቸዋል። አጨዋወታቸው ከእኛ ጋር ተቀራራቢ እንደመሆኑ የስፖርት ቤተሰብ ጥሩ ጨዋታ የሚያይ ይመስለኛል። ቡድናችን አሁን ላይ አንድ ተጫዋች በቅጣት ከማጣቱ ውጪ ሁሉም በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ። ይህን ጨዋታ በማሸነፍ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ የምናደርገውን የትንቅንቅ አጠናክረን እንቀጥላለን። ተጫዋቾቼም ይህን ያደርጉታል። ” ብለዋል።

በመጀመሪያው ዙር መርሀ ግብር ለገጣፎ ላይ ባደረጉት ጨዋታ ለገጣፎ ለገዳዲ 1-0 ማሸነፉ ይታወሳል።

የሜዳ ለውጥ

መድን ሜዳ ላይ ጨዋታውን ሲከናውን የቆየው ኢኮስኮ በዚህ ሳምንት የሜዳ ለውጥ አድርጓል። ምክንያት ተብሎ የቀረበው የኢትዮጵያ መድን ሜዳውን ለጤና ቡድን በመሰጠቱ ሲሆን ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታም በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚያደርግ የቡድን መሪው ሙሉጌታ አሰፋ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል። የአቃቂ ቃሊቲ እና ቡራዩ ከተማ ጨዋታም በተመሳሳይ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በ4:00 ይካሄዳል።

የሳምንቱ ጨዋታዎች (20ኛ ሳምንት)

ምድብ ሀ
እሁድ ሰኔ 2 ቀን 2011

አቃቂ ቃሊቲ (9:00) ቡራዩ ከተማ
ፌዴራል ፖሊስ (9:00) ወልዲያ
አክሱም ከተማ (9:00) ወሎ ኮምበልቻ
አውስኮድ (9:00) ገላን ከተማ
ኢትዮ ኤሌክትሪክ (9:00) ለገጣፎ ለገዳዲ
ሰበታ ከተማ (9:00) ደሴ ከተማ

ምድብ ለ
እሁድ ሰኔ 2 ቀን 2011

ሀላባ ከተማ (9:00) ሶዶ ከተማ
ናሽናል ሴሜንት (9:00) የካ ክ/ከተማ
ድሬዳዎ ፖሊስ (9:00) ነገሌ አርሲ
ኢኮስኮ (9:00) አዲስ አበባ ከተማ
ዲላ ከተማ (9:00) ኢትዮጵያ መድን
ሀምበሪቾ (9:00) ወልቂጤ ከተማ

ምድብ ሐ
እሁድ ሰኔ 2 ቀን 2011

ቡታጅራ ከተማ (9:00) ቤንች ማጂ ቡና
ነገሌ ቦረና (9:00) ጅማ አባቡና
ሻሸመኔ ከተማ (9:00) ስልጤ ወራቤ
ካፋ ቡና (9:00) ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡