የአፍሪካ ዋንጫ ዳሰሳ | ምድብ ስድስት

አራት የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት የያዘው የመጨረሻው ምድብ ከሞት ምድብ ቀጥሎ አጓጊ ምድብ ነው። ቻምፒዮኗ ካሜሩን፣  ጋና፣ ቤኒን እና ጊኒ ቢሳዋን የሚያገናኘው ይህ ምድብ ጠንካራ እና እልህ አስጨራህ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

🇨🇲 ካሜሩን

የተሳትፎ ብዛት – 19

ምርጥ ውጤት – 5 ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ (1984, 1988, 2000, 2002, 2017)

በቀድሞ የኤስሚላን ጀግና ክላረንስ ሲዶርፍ የሚመሩት የባለፈው ውድድር አሸናፊ ካሜሩን ይሄ ውድድር እንደባለፈው ፉክክር አልባ አፍሪካ ዋንጫ አልጋ በአልጋ እንደማይሆንላቸው የታወቀ ነው።

በማጣርያው በምድብ ‘B’ ከሞሮኮ፣ ኮሞሮስና ማላዊ ተደልድለው በደካማው ምድብ ሳይፈተኑ ወደ ውድድር ያለፉት ካሜሩኖች የፓሪ ሰን ጀርመው አጥቂ ቾፓ ሞቲንግን ይዘው ወደ ግብፅ ሲያመሩ ቡድኑ ቻምፒዮን በሆነበት ዓመት በፍፃሜው ጨዋታ የቡድኑ የነብስ አዳኝ የነበረው ቪንሰንት አቡበከር እና ባለፈው የውድድር ዓመት ከሊቨርፑል ጋር ድንቅ ዓመት ያሳለፈውና የሃገሩን ጥሪ አልቀበልም በማለቱ በሃገሩ ልጆች እንደ ከሃዲ የታየው ቀውላላው ተከላካይ ዮኤል ማቲፕ በክላረንስ ሲዶርፍ ጥሪ አልደረሳቸውም።

የቅድመ ዝግጅታቸው በስፔን እና ኳታር ያደረጉት ካሜሩኖች በአቋም መለኪያ ጨዋታ ዛምቢያ እና ኤዲ ኮርኮን የተባለ የስፔን ክለብ ሲያሸንፉ ከማሊ ጋር አቻ ተለያይተዋል።

የማይበገሩት አናብስት ከአያክስ ጋር ድንቅ ዓመት ያሳለፈው ግብጠባቂው አንድሬ ኦናና እና በሃገሩ ማልያ ጥሩ የጎል ክብረወሰን ያለው ማክሰም ቾፓሞቲንግ ላይ ተስፋ ጥለዋል።

🇬🇭 ጋና

የተሳትፎ ብዛት – 22

ምርጥ ውጤት
– 4 ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ (1963 ,1965 ,1978 1982)

ሃገራችን ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሴራሊዮን ከነበሩበት ምድብ ‘F’ ምድቡን በበላይነት በማጠናቀቅ በቀላሉ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ያለፉት ጥቋቁር ከዋክብቶች በውድድሩ በተከታታይ አምስት ጊዜ ለፍፃሜ በመድረስ ባለ ታሪክ ናቸው። አንድሬ አየው አምበልነት ወደ ግብፅ የሚያቀኑት ጥቋቁር ከዋክብቶች በዱባይ በቆዩባቸው የዝግጅት ቀናት ሶስት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች አድርገው አንድ ድል ፣ አንድ አቻ እና አንድ ሽንፈት ቀምሰዋል።

ሁሌም በውድድሩ ተጠባቂ ከሆኑት ሀገራት ተርታ ብትሰለፍም 37 ዓመት ያስቆጠረችው ሀገር ታሪኳን ለማደስ አስር ለውድድሩ እንግዳ የሆኑ ተጫዋቾችን ከማካተት ባሻገር እንደ አትሌቲኮ ማድሪዱ ቶማስ ፓርተይ፣ ባለልምዶቹ ክዋዱ አሳሙሃ፣ አንድሬ አዬው እና አሳሞሃ ጅያን ባሉ ተጫዋቾች ላይ ተስፋ ጥለዋል።

ሳይጠበቅ አዳዲስ ፊቶች ይዞ ወደ ውድድሩ ለማቅናት የወሰነው ክዌሲ አፒያ እነ ባባ ኣህማን ፣ ጆናታን ሜንሳህ ፣ ጆሴፍ አይዶ እና ዓብዱልመጅድ ዋሪስ ወደ መጨረሻው ስብስቤ ሳያካትት ወደ ግብፅ ያመራል።

🇧🇯 ቤኒን

የተሳትፎ ብዛት – 3

ምርጥ ውጤት – የምድብ ጨዋታዎች

አልጀርያ ፣ ቶጎ እና ኮሞሮስ ከነበሩበት ምድብ ‘ D’ ከምድቡ መሪ አልጀርያ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብላ በሁለተኛነት በማጠናቀቅ ከዘጠኝ ዓመት በኃላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የተመለሰችው ቤኒን የማጣርያ ጉዞዋን መሰረት በማድረግ ቀላል ተጋጣሚ እንደማትሆን መገመት አያዳግትም።

በማጣርያው ጨዋታዎች ላይ አምስት ግቦች ብቻ ያስቆጠሩት ቤኒኖች እንደ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሃገራት ግብ የማስቆጠር እና ንፁህ የግብ ዕድል በመፍጠር ረገድ ቀላል የማይባል ክፍተት አለባቸው።

ለቅድመ ዝግጅት ሞሮኮ የቆዩት ቤኒኖች ሶስት ጨዋታዎች አድርገው ሶስቱም በድል ተወጥተዋል።

በርከት ያሉ ተጫዋቾች ከፈረንሳይ የመረጡት ቤኒኖች በአንጋፋው ስቴፈን ሴሴኞ እና በሃደርስፊልዱ ስቲቭ ሞውኔ ላይ ተስፋ ጥለዋል።

🇬🇼 ጊኒ ቢሳው

የተሳትፎ ብዛት – 2

ምርጥ ውጤት – የምድብ ጨዋታዎች

ዛምቢያ ፣ ናሚቢያ እና ሞዛምቢክ ከነበሩበት ምድብ ‘ k ‘ ሳትጠበቅ ምድቡን በበላይነት ያጠናቀቀችው ጊኒ ቢሳው ትላቋን ዛምቢያ ጨምሮ ሌሎቹን ሁለት ሃገራት ረምርማ ወደ ውድድሩ ታልፋለች ብሎ የገመታት አልነበረም። ከሞዛምቢክ ጋር በነበረው ድራማዊ ክስተት በተሞላበት ጨዋታ በአስደናቂ ብቃት አቻ ከተለያየች በኃላ የብዙዎች ትኩረት ስባ የነበረችው ጊኒ ቢሳው ሽንፈት ሳትቀምስ ነበር ወደ ውድድሩ ያለፈችው።

በአሰልጣኝ ካንዴ እየተመራች ለሁለተኛ ጊዜ በውድድሩ የምትሳተፈው ጊኒ ቢሳው በማጣርያው ሶስት ግብ ያስቆጠረላት ፍሬድሪክ ሜንዲ ኮከብ ተጫዋቿ ነው።

የምድቡ ተጠባቂ ጨዋታ፡ ካሜሩን ከ ጋና

ሁለቱ በውድድሩ ትልቅ ታሪክ ያላቸው የምንግዜም ተቃናቃኞች የሚያገናኘው ይህ ጨዋታ በታሪክም በወቅታዊ አቋም ረገድም ተጠባቂ ጨዋታ ነው።

ተመሳሳይ አጨዋወት የሚከተሉት ሁለቱ ቡድኖች የሚያገናኘው ይህ መርሐ ግብር የምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ ነው።

ከምድቡ የሚጠበቅ ኮከብ ተጫዋች: ቶማስ ፓርቲይ

ከምድብ ስድስት የሚጠበቀው ተጫዋች ጋናዊው የአትሌቲኮ ማድሪዱ ወሳኝ አማካይ ቶማስ ፓርተይ ነው። በምድቡ በርካታ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው እና ከዚ በፊት በውድድሩ ልምድ ያላቸው እንደነ አሳሞሃ ጅያን የመሳሰሉ ተጫዋቾች ቢኖሩም እንደ የሃያ ስድስት ዓመቱ ውጤታማ አማካይ የሚያክል ግን አይጠበቁም። በአትሌቲኮ በበርካታ ሚናዎች ላይ የሚጫወተው አይደክሜው ተጫዋች በጋናም ተመሳሳዩ ሚና ከተሰጠው እንደሚያንፀባርቅ ይጠበቃል።

የምድቡ ጨዋታዎች

ማክሰኞ ሰኔ 18 ቀን 2011

ካሜሩን 2:00 ጊኒ ቢሳው

ጋና 5:00 ቤኒን

ቅዳሜ ሰኔ 22 ቀን 2011

ካሜሩን 2:00 ጋና

ቤኒን 5:00 ኢኳቶርያል ጊኒ

ማክሰኞ ሰኔ 25 ቀን 2011

ቤኒን 1:00 ካሜሩን

ጊኒ ቢሳው 1:00 ጋና

*ይፋዊ የተጫዋቾች ስብስብ እንደደረሰን እናካትታለን