የጨዋታ ቀን ለውጥ ይደረግልን ጥያቄን እንደማይቀበል ዐቢይ ኮሚቴው አሳወቀ

አንዳንድ ክለቦች የፕሮግራም ለውጥ ይደረግልን በማለት የሚያቀርቡትን ጥያቄ የማያስተናግድ መሆኑን የሊጉ ዐብይ ኮሚቴ በደብዳቤ አሳወቀ።

ባህር ዳር ከተማ በአንደኛ ሳምንት በዕለተ ሰኞ ከጅማ አባጅፋር ጋር ተጫውቼ ሌሎቹ እሁድ ተጫውተው ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር የማደርገው ጨዋታ በአንድ ቀን ተገፍቶ ቅዳሜ ይሁንልኝ በማለት የጠየቀውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ጨዋታው አስቀድሞ በወጣለት መርሐግብር እንዲካሄድ ዐብይ ኮሚቴው ማድረጉ ይታወቃል።

ሆኖም እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች ሌሎች ክለቦች ወደ ፊት ሊያነሱ ይችላሉ በማለት የሊጉ ዐብይ ኮሚቴ ለ16ቱም ክለቦች ጠንከር ያለ ደብዳቤ በትኗል። “የትኛውም ቡድን አስቀድሞ ከወጣው ፕሮግራም ውጭ ምንም ዓይነት የፕሮግራም ይቀየርልን ጥያቄዎች የማናስተናግድ መሆኑን እየገለፅን አንድ ክለብ ውድድር ካደረገ ከ72 ሰዓት በኃላ በሚወጣለት ጨዋታ ፕሮግራም መሠረት የመጫወት ግዴታ ያለበት መሆኑን አውቃችሁ 16ቱም የፕሪምየረ ሊግ ክለቦች ለወጣው ፕሮግራም ተገዢ በመሆን ውድድራችሁን እንድታከናውኑ እናሳስባለን፡፡” ብሏል ዐብይ ኮሚቴው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: