የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ዐበይት ትኩረቶች

7ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በሳምንቱ አጋማሽ ተካሂደው ወልዋሎ ዳግም መሪነቱን ሲረከብ ሀዲያ ሆሳዕና በአንፃሩ የውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን አስመዝግቧል። እኛም በሳምንቱ አጋማሽ የተካሄዱ የሊግ ጨዋታዎችን መነሻ በማድረግ ተከታዮቹን ነጥቦች ለማንሳት ወደናል።

1. ክለብ ትኩረት

*ሲዳማ ቡና ከሽንፈት መንቃት አልቻለም

ዐምና ከቻምፒዮኖቹ መቐለ 70 እንደርታዎች በአንድ ነጥብ አንሰው በ58 ነጥቦች ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ባጠናቀቁበት የውድድር ዓመት በጥቅሉ በዓመቱ 6 ጨዋታዎችን ብቻ ነበር የተነሸፉት። ስድስቱም ሽንፈቶች ደግሞ ከሜዳ ውጭ በተደረጉ ጨዋታዎች የተመዘገቡ ነበሩ።
ዘንድሮ በተቃራኒው ገና ከወዲሁ በ7 ሳምንት የሊጉ ጉዞ 3 ጨዋታዎች ተሸንፏል። ከእነዚህ ውስጥ ደግም ሁለቱን በሜዳው መሆኑ ትኩረትን የሚስብ ነው። በዚህኛው ሳምንት በሊጉ እስካሁን ማሸነፍ በተሳነው ሀዲያ ሆሳዕና ተከታታይ ሁለተኛ ሽንፈታቸውን አስተናግደዋል።

*ቅዱስ ጊዮርጊስና የሜዳ ውጭ ድል ተራርቀዋል

ባሳለፍነው ሳምንት በክለቡ አመራሮች ማስጠንቀቂያ የደረሳቸው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾችና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት በእሁዱ የመቐለው ጨዋታ ላድ መነቃቃትን ማሳየት ችለው 2-1 ማሸነፍ ችለው ነበር። ነገር ግን አሁንም ቡድኑ ከሜዳው ውጭ ደካማ ከሆነ እንቅስቃሴ ጋር ማሸነፍ ተስኖት ይገኛል። ዘንድሮም ከሜዳው ውጭ ባደረጋቸው 4 ጨዋታዎች በአንዱ ሲሸነፍ በሦስቱ ደግሞ አቻ ተለያይቷል። አምና በ27ኛ ሳምንት ወደ መቐለ ተጉዘው ደደቢትን 3-2 ከረቱበት ድል ወዲህ እስካሁን ቡድኑ ከሜዳ ውጭ ምንም ድል ማስመዝገብ አልቻለም።

*ግራ አጋቢው ድሬዳዋ

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ሲዳማ ቡናን በከፍተኛ ትግል አሸንፎ ያስደመመው ቡድን በዚህኛው ሳምንት ደግሞ በሜዳው በወልዋሎ 2-0 ተሸንፏል። ከሜዳ ውጭ ባሉ ሁነቶች በደጋፊዎች ከፍተኛ ተቃውሞ እያስተናገደ የሚገኙት የክለቡ አመራሮች በሜዳ ላይ የቡድኑ ውጤት አላምር ብሏቸዋል። ካለፉት ሁለት የሜዳቸው ጨዋታዎች አንድ ነጦብ ብቻ ያሳኩት ድሬዎች የሜዳ ድል ሁነኛ የነጥብ ማግኛ በሆነበት ሊግ ተደጋጋሚ ነጥቦችን መጣል በሒደት ዋጋ ሊያስከፍላቸው ይችላል።

*የሀዲያ ሆሳዕና የመጀመርያ ድል

በሊጉ አስከፊ አጀማመር ያደረጉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በዚህኛው ሳምንት ሲዳማ ቡናን 2-1 በማሸነፍ በተወሰነ መልኩ ጫናዎችን ማርገብ ችለዋል። ቡድኑ ይህ በዚህኛው ሳምንት ያስመዘገበው ድል የማንቂያ ደውል ሆኗቸው የውድድር ዘመናቸውን ደግም ወደ ትክክለኛው መስመር ይገቡ ይሆን የሚለው ጥያቄ በቀጣይ ሳምንታት የሚታይ ይሆናል።

* የወልዋሎ ዳግም መሪነት መረከብ

ከአስደናቂ ጅማሮ በኋላ በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ማግኘት ከነበረበት 9 ነጥብ ሁለት ብቻ አሳክቶ ባለፈው ሳምንት ከመሪነቱ ተንሸራቶ የነበረው ወልዋሎ ከሜዳው ውጪ ድሬዳዋ ከተማን 2-0 በማሸነፍ ወደ መሪነቱ ተመልሷል። ቡድኑ እስካሁን ካገኛቸው ሦስት ድሎች ሁለቱን ያገኘው ከሜዳው ውጪ ሲሆን የአቀራረቡ እና የተጫዋቾች ምርጫው ተገማች አለመሆን ለባለሜዳ ቡድኖች ፈታኝ ሆኖ እንዲቀርብ አስችሎታል። ሆኖም ቡድኑ በፉክክሩ ለመግፋት ይህን የሜዳ ውጪ ጥሩ ጅማሮ በትግራይ ስታዲየም በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይም መድገም ይጠበቅበታል።

*በቁጥር ብልጫ ያልተበገረው ኢትዮጵያ ቡና

በዚህኛው ሳምንት ከተደረጉ መርሐግብሮች በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም ባህር ዳርን ከኢትዮጵያ ቡና ያገናኘውና በባለሜዳዎቹ የ3-2 ድል የተጠናቀቀው ጨዋታ እጅግ አዝናኝ ሆኖ ያለፈ ጨዋታ ነበር። 3-1 እየተመሩ ወደ መልበሻ ክፍል ያመሩት ቡናማዎቹ በ53ኛው ደቂቃ የመስመር አጥቂያቸውን አቤል ከበደን በቀይ ካርድ ቢያጡም በጎዶሎ የቸጫዋቾች ቁጥር ሳይበግራቸው በቀሪው የጨዋታ ክፍለጊዜ የነበራቸውን ፍፁማዊ የበላይነትን ለተመለከተ የኢትዮጵያ ቡናን አቀራረብ ለማድነቅ ያስገድዳል።


2. ተጫዋች ትኩረት

*የወሳኝ ተጫዋቾች ጉዳት

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በርከት ያሉ የተጫዋቾች ጉዳት እየታዩ ይገኛሉ። በዚህ ሳምንት ደግሞ ፍፁም ዓለሙ፣ አዳማ ማሳላቺ እና መስፍን ታፈሰ ጉዳቶች ያስተናገዱ ሲሆን ከመጎዳታቸው ባሻገር ከሜዳ የሚያርቃቸው የጊዜ መጠን መብዛት እና ማነስ በቡድኖቹ ላይ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ትከረት የሚስብ ጉዳይ ነው።

ሽረ ከ ሰበታ ባደረጉት ጨዋታ ላይ የተጎዳው ጋናዊው ተከላካይ አዳማ ማሳላቺ በሽረ በጉልህ የሚታይ ተፅዕኖ እየፈጠረ የሚገኝ ተጫዋች እንደመሆኑ በቀጣይ ጨዋታዎች የቡድኑን የመከላከል ጥራት እንደሚያጎድለው አያጠራጥርም። ዘንድሮ ድንቅ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘውና ከጉዳት ጋር ባህር ዳር ከ ኢትዮጵያ ቡና ባደረጉት ጨዋታ ላይ ተሰልፎ ሁለት ጎሎች ያስቆጠረው ፍፁም ዓለሙ በቀጣይ ጨዋታዎች ላይ አለመሰለፍ በባህር ዳር ውጤታማነት ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል። በተመሳሳይ ሀዋሳ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ባደረጉት ጨዋታ ላይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረውና በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የወጣው መስፍን ታፈሰም ሀዋሳ በቀጣይ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ የመሰለፉ ነገር ማጠራጠሩ በቡድኑ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም።

* አቡበከር ናስር

በሊጉ የመጀመርያ ጨዋታዎች በጉዳት ተቀዛቅዞ ነበረው አቡበከር ናስር ወደ ድንቅ አቋሙ እየተመለሰ መሆኑን እያሳየ ይገኛል። በስድስተኛው ሳምንት ሁለት ጎሎችን ያስቆጠረው አቡበከር በ7ኛው ሳምንትም ጥሩ ከመንቀሳቀሱ ባሻገር ጎል አስቆጥሯል። በተጨማሪም የቅጣት ምት ጎል ማስቆጠሩ ወደተሟላ ተጫዋችነት እየተሸጋገረ መሆኑን ፍንጭ የሚሰጥ ይመስላል። ተጋጣሚን በቁጥጥሩ ስር አድርጎ በራሱ መንገድ የሚጫወተው ኢትዮጵያ ቡና እንደቡድን ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ ከመሆኑ አንፃር የአቡበከር ወደ ጥሩ አቋም መመለስ በቀጣይ ኡድኑ በሚቸገርበት ወቅት ልዩነት ፈጣሪ ይሆንላቸዋል ተብሎ ይገመታል።

* ፍፁም ዓለሙ

በኢትዮጵያ እግርኳስ ጎል ከአጥቂዎች ብቻ የሚጠበቅበት ተለምዷዊ ዕምነትን የሚያፋልሱ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾች አልፎ አልፎ በሊጉ ይታያሉ። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከነዓን ማርክነህ በዚህ ረገድ የሚጠቀስ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ የባህር ዳር ከተማው ፍፁም ዓለሙ ተጠቃሽ ተጫዋች ሆኗል።

ሊጉ ከተጀመረ ወዲህ በሰባት ጨዋታዎች ስድስት ጎሎች ያስቆጠረው ፍፁም ዐምና የክለቡ አጠቃላይ ዓመት ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ፍቃዱ ወርቁ ጋር ገና ከወዲሁ በቁጥር መስተካከሉ አስገራሚ ነው።

*ጃፋር ደሊል፣ ባህሩ ነጋሽ እና ሰዒድ ሀብታሙ ከ ውጪ ግብ ጠባቂዎች

ዘንድሮ በሊጉ ክስተት ከሆኑ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው የጅማ አባ ጅፋሩ እብ ጠባቂ ሰዒድ ሀብታሙ በዚህ ሳምንት በጉዳት ወልቂጤን ካሸነፈው ስብስብ ውጪ ሆኗል። በትምኩም ጋናዊው ግዙፍ ግብ ጠባቂ መሐመድ ሙንታሪ የፓስፖርት ጉዳዩን አጠናቆ ለመጀመርያ ጊዜ ተሰልፎ ጥሩ መንቀሳቀስ ከመቻሉ በተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት ወጥቷል። በቀጣይም ሰዒድ ከጉዳት ሲመለስ በገሰሉ መሐል የሚሰለፈውን ግብ ጠባቂ መምረጥ የጳውሎስ ጌታቸው ፈተና ይሆናል። 

የወልዋሎው ጃፋር ደሊል ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች የጊኒያዊው አብዱላዚዝ ኬይታ አለመኖርን ተጠቅሞ ጥሩ ብቃቱን አሳይቶ በሁለቱም ጨዋታዎች ጎል ሳያስተናግድ ወጥቷል። በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኙ ተጫዋቾችን ዕድል ከመስጠት ወደኋላ ማይሉት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌም ኬይታ ከቅጣት ሲመለስ ቀጣይ ምርጫቸው የሚጠበቅ ይሆናል። 

የቅዱስ ጊዮርጊስን ጎል ለሰባት ጨዋታዎች የጠበቀውና በአምስቱ ጨዋታዎች ግብ ያላስተናገደው ባህሩ ነጋሽ በዚህ ሳምንትም ጎል ሳይቆጠርበት ወጥቷል። የኬንያው ኢንተርናሽናል ፓትሪክ ማታሲን ከጉዳት መመለስ ተከትሎ በተሰላፊነቱ ይዘልቃል ወይስ ይቀጥላል የሚለው በቀጣይ ሳምንታት የሚመለስ ቢሆንም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ማታሲ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ሆኖ ጨዋታውን መመልከቱ ባህሩ የመሰለፍ ዕድሉን ጠብቆ ሊቀጥል እንደሚችል ፍንጭ የሚሰጥ ይመስላል። 


3. ድህረ ጨዋታ አስተያየቶች

*ዘርዓይ ሙሉ ስለ ሜዳ እና ዳኝነት

“እጅግ አሳፋሪ ጨዋታ ነው። ኳስ እኛ እያመላለስን የምንጫወትበት ጨዋታ ነበር። ገና ከእረፍት ጀምሮ አንድ ኳስ እንዳገቡ ኳስ መደበቅ ጀመሩ። አራተኛ ዳኛው ይሄን ደግሞ ማስጠንቀቅ ነበረበት። ከእረፍት በኋላም ሙሉውን ደቂቃ እኛ እያመላለስን ነው የተጫወትነው። ከሰላሳ ደቂቃ በኃላ ምንም አልተጫወቱም፤ ጨዋታውን ገደሉት። ከዛ ፌዴሬሽኑ ራሱ የሚያሳፍር ነው። ይሄን እርሻ ሜዳ ሜዳ ነው ብሎ መፍቀዱ። ከዛ ደግሞ አሳፋሪ ዳኝነት፡፡”

*አዲሴ ካሳ በተደጋጋሚ በሜዳ ላይ ነጥብ ስለመጣል

“ነጥብ መጣል ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም። ይሄ ኳስ ጨዋታ ነው። በኳስ ጨዋታ ነጥብ ታገኛለህ፣ ነጥብ ታጣለህ። እዚህ ስትጥል ውጪ ላይ እየያዝን ነው እኮ። እዚህ ነጥብ ጥለህ ከሜዳው ውጪ የምትጥል ከሆነ ጥያቄው ልክ ነው፡፡ ቡድናችን ግን ኮንክሪት የሆነ ቡድን ነው። ከኢትዮጵያ ቡና እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ በስተቀር አምስት ጨዋታ ላይ ሁለት ጎል ነው የገባብን። ሆሳዕና ላይ በፍፁም ቅጣት ምት እና እዚህ የመጀመሪያ የድሬዳዋ ጨዋታ ላይ… ስለዚህ ተከላካያችን ጥሩ ነው፡፡ ክፍተቶች አሉብን እሱ ላይ እንሰራለን።

*ሰርዳን ዚቮጅኖቭ ጎል ስላለማስቆጠራቸው

“ላለማስቆጠራችኝ ግብ ጠባቂው ረድቷቸዋል፤ ከአስር በላይ መሞከር ችለናል፡፡ ወደነሱ ግብም በተደጋጋሚ ደርሰናል። የበረኛቸው ጥንካሬ ማስቆጠር እንዳንችል አድርጎናል። በአጠቃላይ ዕድለኛች አልነበርንም፡፡”

*ካሣዬ አራጌ ስለ ብቃት ቀጣይነት

በሆኑ አጋጣሚዎች ግብ ልታስቆጥር ትችላለህ። መመዘን ያለበት ግን አጠቃለይ ያለው እንቅስቃሴ ነው። አስተማማኝ የሚሆነው የምታገባቸው ግቦች ሳይሆን በዘጠና ደቂቃ ውስጥ ተጋጣሚህ ላይ የነበረው የበላይነት ነው። አንድ ለዜሮም አሸንፈህ ያ የበላይነቱ ካለ በሚቀጥለውም ማሸነፍ ትችላለህ። ስድስት ሰባትም አግብተህ ያ የበላይነት ከሌለ ያንን ውጤት አስጠብቀህ መሄዱ ከባድ ነው የሚሆነው። ስለዚህ ብዙ ትኩረት የምናደርገው እንቅስቃሴው ላይ ነው። ግጥሚያውን የመቆጣጠር ሂደቱ ምን ይመስላል የሚለውን ነው። ከዛ አንፃር ሲታይ ዛሬ ጥሩ ነበርን ብየ ነው የማስበው።”


4. የበዓል ሰሞን ጨዋታዎች

በሌሎች ሀገራት በተለይም በእንግሊዝ የበዓል ሰሞን ጨዋታዎች ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው እና ተጠባቂ ናቸው። በየዓመቱም ስለሚካሄዱም የባህል ያህል ተይዘዋል። በኢትዮጵያም አልፎ አልፎ በበዓል ሰሞን (ዋዜማ፣ ዕለት እና ማግስት) ጨዋታዎች የሚደረጉ ሲሆን በዘንድሮው የልደት (ገና) በዓል አንድ ጨዋታ እንዲሁም በማግስቱ ሰባት ጨዋታዎች ተከናውነዋል።

ጨዋታዎችን በማንኛውም ወቅት ማከናወን እግርኳስን ሥራ ብለው ለሚሰሩ አካላት (ክለቦች፣ አወዳዳሪ አካል እና ሚዲያ) ግዴታ ቢሆንም በሀገራችን ለበዓል አከባበር የሚሰጠው ግምት ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጨዋታዎች በሚደረጉበት ወቅት የሚገባው ተመልካች ቁጥር ዝቅተኛ ሲሆን ይታያል። መቐለ ላይ ስሑል ሽረ ከ ሰበታ ከተማ ያደረጉት ጨዋታም ለዚህ እንደ ማሳያ መቅረብ ይችላል።


5. መርሐ ግብር

በቅድሚያ በወጣውና ለክለቦች እንዲሁም ለሚዲያ የተበተነው የሊጉ መርሐ ግብር የ7ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ማክሰኞ (3) እና ረቡዕ (5) እንደሚካሄዱ ቢያሳይም ሁለት የበዓል ዕለት ጨዋታዎች ወደ ረቡዕ ተሸጋግረው መካሄዳቸው ይታወሳል። ሆኖም ጨዋታዎቹ ወደ ቀጣዩ ቀን መሸጋገራቸው በይፋ ባለመገለፁ ደጋፊዎችን እና የሚድያ አካላትን ለውዥምብር አጋልጦ አልፏል። ዘንድሮ ሊጉን እየመራ የሚገኘው ዐቢይ ኮሚቴ በርካታ መልካም ሥራዎች እየሰራ የመገኘቱን ያህል እነዚህን አይነት ክፍተቶች በቀጣይ ሊያርም ይገባል። 

ዐቢይ ኮሚቴው በቀጣይ ሊጉን የተመለከቱ መረጃዎችን ከፌዴሬሽኑ ህዝብ ግንኙነት ጋር በመናበብ ለህዝብ የማድረስ አልያም ተከታትሎ የሚያሳውቅ የራሱ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ወይም ባለሙያ መቅጠር እንደ መፍትሄ ሊወሰድ ይችላል።


© ሶከር ኢትዮጵያ