የአሰልጣኞች ገጽ | ክፍሌ ቦልተና [ክፍል 3 – ቀጣይ የአሰልጣኝነት ጉዞዎች]

የሀገሪቱ ውጤታማ እና አንጋፋ አሰልጣኞችን የሥራ ህይወት፣ ተሞክሮ እና አስተሳሰብ የሚዳስሰው “የአሰልጣኞች ገፅ” ክፍሌ ቦልተናን ቃለ-ምልልስ በሁለት ክፍሎች ማቅረባችን ይታወሳል። ሦስተኛው ክፍልን ለማቅረብ በእጅጉ በመዘግየታችን ይቅርታ እየጠየቅን በዚህ ክፍል ከመድን ከለቀቁ በኋላ ስላሳለፉት የሥራ ጊዜ ቆይታ አድርገናል


ከመድን አስቸጋሪ ቆይታህ በኋላ እንደገና የአሰልጣኝነት ህይወትህን በስኬታማ ሒደት ማስቀጠል የጀመርከው በአየርኃይል ነው፡፡ እዚያ ያሳለፍከውን ጊዜ እናንሳ?

★ ከመድን በኋላ ያመራሁት ወደ አየር ኃይል ነው፡፡ ክለቡ ማስታወቂያ አውጥቶ ሃያ አምስት አሰልጣኞች አወዳድሮ ነበር፡፡ ማመልከቻችንን ደብረዘይት ሄደን ነበር የምናስገባው፡፡ ወደ ግቢው ውስጥ መግባት ስለማይቻል በር ላይ ለሚመለከተው አካል እንሰጣለን፡፡ የክለቡ ፕሬዘዳንት ኮሎኔል ገብረሥላሴ እኔ ማስረጃዎቼን ማስገባቴን እንዳወቁ ደወሉልኝ፡፡ እርሳቸው ሲደውሉ በኮተቤ እነ ዳዊት እስጢፋኖስን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ የፕሪምየር ሊግ ክለብ ተጫዋቾች የሚሳተፉበት ደስ የሚል የፉትሳል ውድድር እያየሁ ነበር፡፡ ” ክፍሌ አንተ መወዳደርህን ሰምቻለሁ፤ እኛ እንስማማለን፤ ወዲህ ወዲያ እንዳትል! እኛ ጋር ትገባለህ፤ ቃል ግባ፡፡” ሲሉኝ ‘እሺ!’ አልኳቸው፡፡ ከዚያም ” ይኸውልህ ክፍሌ ቃልህን ብታጥፍ ያለህበት መጥቼ ነው የማስይዝህ፡፡” ብለው ሁሉ ቀለዱብኝ፡፡ እንዳሉትም አሰልጣኞች ማወዳደሩን ትተው ጠሩኝ፤ ተስማማን፤ ተፈራርሜ ስራ ጀመርኩ፡፡ ይህ ሁኔታ በእኔ ላይ ትልቅ እምነት እንደነበራቸው አሳየኝ፡፡ ክለብ እምነት ሲያሳድርብህና ክብር ሲሰጥህ በጣም ትሰራለህ፡፡ ኮሎኔሉ የጊዮርጊስ ደጋፊ ናቸው፤ ስታዲየም አይጠፉም፤ በቡና የሰራሁትንም ያውቃሉ፡፡ እኔም አላሳፈርኳቸውም፤ በሁለት ወር የዝግጅት ጊዜ ውስጥ ወጣቶችን ሰብስቤ ጥሩ ቡድን ሰራሁ፡፡ ከዚያ ክለቡ የደብረዘይት ህዝብን ትኩረት ሳበ፤ በኳስ እንቅስቃሴያችንም ጥሩ ነበርን፡፡ ሆኖም ከድሬደዋ አሸንፈን እየመጣን ያልታሰበው የመኪና አደጋ ደረሰብን፡፡ የፋሲካ በዓልን ቤተሰብ ጋር ለማክበር ተቻኩለናል፤ በጊዜ ለመግባት አስበን በለሊት ጉዞ ጀመርን፤ “አውሮፕላን የለም፡፡” ተብለው ሶስት የአየርኃይል አብራሪዎችም ከእኛ ጋር ነበሩ፡፡ በአጠቃላይ ከሰላሳ በላይ እንሆናለን፡፡ ቁልቢን ተሳልመን ትንሽ ወረድ እንዳልን ቁልቁለቱ ላይ የመኪናችን ፍሬን ተበጠሰ፡፡ የመንገዱ ዳር ገደል ነው፡፡ ሁሉም ሰው በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ሆኖ ግማሹ ጸሎት ያደርሳል፤ ግማሹ ወንበር ሥር ይገባል፤ በቃ ሃይለኛ ጭንቀት ውስጥ ገባን፡፡ በመሃል ቡድን መሪው (ሙሉ ይባላል-አሁን መከላከያ ይገኛል፡፡) ለሹፌሩ “መኪናውን ወደ አንድ ጎን ጣለው፡፡” አለው፡፡ ሹፌሩ መኪናውን ከሆነ ጠርዝ ጋር ሲያጋጨው በአየር ላይ ሄዶ አስፋልቱ ላይ ቁጭ አለ፡፡ እኔ በመስኮቱ ወደ ውጪ ተወረወርሁ፤ የጎድን አጥንቶቼ ተሰባበሩ፤ ሌሎችም ከፍተኛ ጉዳት ደረሰባቸው፡፡ ወዲያው የአየር ኃይል ሄሊኮፕተር መጥቶ ወደ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል አመጣን፡፡ ለሁለትና ለሶስት ቀናት የማውቀው ነገር አልነበረም፤ እስካገግም ድረስ ተኛሁ፡፡ ያ አደጋ ከመከሰቱ አንድ ሳምንት በፊት ተመሳሳይ አደጋ በአዳማ ክለብ ላይ ደርሶ የክለቡ ቡድን መሪ ህይወት አልፎ ነበር፡፡ ፌዴሬሽኑም ለሁለት ወራት እረፍት ሰጥቶን ነገሮች ካለፉ በኋላ ክለቡ በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች መሸነፍ ሲጀምር ” በድጋፍም ቢሆን መጥተህ ልምምድ እይልን፤ ወደ ጨዋታ እኛ እንሄዳለን፡፡” አሉኝ፡፡ ልምምድ ላይ መጠነኛ ማስተካከያዎች አደረግን፤  እኔም ተሽሎኝ ወደ ስራዬ ተመለስኩ፤ ክለቡም ውጤት ማምጣቱን ጀመረ፡፡ 

በእርግጥ የደብረዘይት ህዝብ በዋነኝነት የሚደግፈው የከነማውን ክለብ ቢሾፍቱን ቢሆንም ለእኛም ድጋፍ ይሰጡ ነበር፡፡ እዚህ አዲስ አበባ ከአርባ ምንጭ ጋር ስንጫወት ወደ አስራ ስድስት በሚደርስ ኦራል ተጭነው በመምጣት ደግፈውናል፡፡ የኳስ አጨዋወት ዘይቤ የሰውን ትኩረት ይለውጣል፡፡ ልክ በቅርቡ ሰበታን ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዳመጣሁ አየርኃይልንም እንዲሁ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲያድግ አደረግሁ፡፡ በፕሪምየር ሊጉ አንደኛ ዙር ሰራሁና ነፍሱን ይማረውና ንጉሴ ደስታ ተቀጠረ፡፡ እናም በአየር ኃይል ጥሩ ጊዜ አሳልፌያለሁ፡፡ ከመብራት ኃይል <C> ቡድን በኋላ ደስ ብሎኝ የሰራሁበት ክለብ አየር ኃይል ነው፡፡ ተጫዋቾቹ ሲጫወቱ ሳይ እንኳ የሚሰማኝ ስሜት ልዩ ነበር፡፡ ሙሉ በሙሉ ራሴ የመለመልኳቸው ልጆች ናቸው፤ ወጣቶች ይበዛሉ፤ እንቅስቃሴያቸው ይማርካል፤ በምፈልገው መንገድ ነበር የሚጫወቱልኝ፤ እኔም በስራዬ እርካታ አግኝቼበታለሁ፡፡ አምና ሰበታ ምንም ሳይሸነፍ ዋንጫ እንዲወስድ አስችያለሁ፤ ነገርግን ተጫዋቾቹ የአየር ኃይልን ያህል አልተዋሃዱልኝም፡፡


ከአየር ኃይል በኋላ ወደየት አመራህ?

★ ወደ ብሄራዊ ሊጉ ደቡብ ፖሊስ ተጓዝኩ፡፡ እነርሱም እንዲሁ ጠርተውኝ ነበር የሄድሁት፡፡ ደቡብ ፖሊስ ዓመቱን ሙሉ ሳይሸነፍ ወደ ሱፐር ሊግ ገባ፡፡ ያኔ ከተለያዩ ምድቦች አስር የሚሆኑ ቡድኖች አንድ ክልል ላይ ይከትሙና ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት ይወዳደራሉ፡፡ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማደግ የሚደረገው ቶርናመንት ባህርዳር ላይ ተካሂዶ አዳማ አደገ፡፡ ሁለተኛውንም ዓመት እዚያው ቆየሁ፡፡ በዚህኛውም የውድድር ዘመን ድሬደዋ ላይ በተካሄደው የሱፐር ሊግ ቡድኖች ውድድር ድሬደዋና ሆሳዕና ወደ ፕሪምየር ሊጉ አደጉ፡፡ በድሬደዋው ውድድር ጥሩ ቡድን ሰርተናል፤ በተለይ ከመድን ጋር ባደረግነው ጨዋታ ቆንጆ እንቅስቃሴ አሳየን፡፡


ጅማ አባጅፋር ቀጣዩ ማረፊያህ ሆነ?

★ በድሬደዋው ውድድር በደቡብ ፖሊስ አሰልጣኝነቴ ያዩኝ የመቐለ፣ ጅማ አባጅፋርና ሰበታ ሰዎች አናገሩኝ፡፡ የሰበታው ቴክኒክ ኮሚቴ አባል የነበረ ያሬድ የተባለ ሰው ራስ ሆቴል ቀጠረኝ፤ እዚያ ተገናኘን ፡፡ ከጅማ የክለቡ ፕሬዘዳንት አቶ ሑሴን ደውሎ አወራን፤ መቐለዎች ደግሞ በምክትል አሰልጣኛቸው አማካኝነት ተነጋገርን፡፡ እኔ በደንብ አሰብኩበትና የጅማን ጥያቄ ተቀብዬ ለአንድ ዓመት ፈረምኩ፡፡ ጅማ በጣም ጥሩ ጊዜ አሳለፍኩ፤ በእርግጥ በዚያ ዓመት ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊግ አላሳለፍኩትም፤ አራተኛ ነበር የወጣነው፡፡ ክለቡ በጅማ በጣም የሚወደድ ቡድን ነው፡፡ በጅማ ውጤት ከሌለህ አልያም ጥሩ ጨዋታ ካላሳየህ ከፍተኛ ጫና ይገጥምሃል፡፡ በዚህ የተነሳ እኔ የሚያስቀጥሉኝ አልመሰለኝም ነበር፡፡ ነገርግን ደጋፊዎች ” ክፍሌ ጥሩ ነገር ሰርቷል፤ ራሱ ቡድኑን ይዞ ይቀጥል፡፡ አንድ ዓመት ቢጨመርለት ክለቡን ሊያሳልፍ ይችላል፡፡” አሉ፡፡ ሰፈሬ ጀሞ አካባቢ ነው፡፡ እዚያው እኔ ያለሁበት ቦታ መጥተው ለአንድ ዓመት ፈረምኩ፡፡ አንደኛውን ዙር በጥሩ ውጤት ጨረስኩ፤ ክለቡ እየመራ ውድድሩን አጋምሶ ነበር፡፡ ከዚያ የመጀመሪያ ዙር ግምገማ ተጠራ፤ ብዙ የማልግባባቸው ሰዎች በዙሪያዬ ነበሩ፡፡ እዚያው ስብሰባ ላይ ወሰንኩና “በዚህ ሁኔታ መሥራት አልችልም፡፡” አልኳቸው፡፡ ፕሬዘዳንቱ ሊያናግረኝና ሐሳቤን ለማስቀየር ሞከረ፡፡ እኔ ግን በአቋሜ ጸናሁ፡፡ ምክንያቱም ተግባብቼ መሥራት ካልቻልኩ ውጤት ላመጣ አልችልም፡፡ ተከታዮቻችን ጠንካሮቹ ወልቂጤ፣ ሆሳዕና እና ሰበታ ነበሩ፡፡ አብዛኛዎቹን የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ከሜዳችን ውጪ ነበር ያደረግነው፡፡ ቀሪዎቹ ጨዋታዎች በብዛት በጅማ የሚከናወኑ ስለሆኑ በደጋፊዎቻችን ፊት ማሸነፍ ይቀለን ነበር፡፡ ሳንስማማ ቀረን፡፡ ለአንድ ዓመት ከመንፈቅ የለፋሁበትን ቡድን ለቅቄ ወጣሁ፡፡ ክለቡ ግን በዓመቱ መጨረሻ ወደ ፕሪምየር ሊጉ አለፈ፡፡


ከጅማ አባጅፋር ለቀህ ወደ የትኛው ክለብ አቀናህ?

 ★ከጅማ እንደወጣሁ ፌደራል ፖሊስን አሰልጥኛለሁ፡፡ በእርግጥ በዚህ ክለብ ለስድስት ወራት ብቻ ነው የቆየሁት፡፡


በሃዲያ ሆሳዕናም ኮንትራት አቋርጠህ ነበር?

★ ከጅማ ከወጣሁ በኋላ ሃዲያ ሆሳዕናን ተረከብኩ፡፡ ሰበታ ከመግባቴ በፊት በሆሳዕና የአንድ ዓመት ኮንትራት ይቀረኝ ነበር፡፡ ለወጣቱ የክለቡ ፕሬዘዳንት አቶ መላኩ ” እኔ ለቤተሰቤ የሚቀርብ ክለብ አግኝቻለሁ፡፡” ብዬ ነገርኩት፡፡ እርሱ በጣም ጥሩ ሰው ነው፡፡ ” ካልፈለግህ አናስገድድህም፡፡” ብሎ መልቀቂያ ሰጠኝ፡፡ ስምምነቴ የዓመት ከስድስ ወር ቢሆንም ሁለተኛው ዙር ተጀምሮ ክለቡን በተቀላቀልኩ ሁለተኛ ወር ላይ ገና የአንድ ዓመት ቀሪ ኮንትራት እያለኝ ሆሳዕናዎች በስምምነት ለቀቁኝ፡፡


የቅርቡ ክለብህ ሰበታ ነው፡፡

★የመጨረሻ ክለቤ ሰበታ ሆነ ማለት ነው፡፡ ሰበታ ለመኖሪያ ቦታዬ ቅርብ ስለሆነ ክለቡን ለማሰልጠን ብዙ ስፈልግ ቆይቻለሁ፡፡ በአጋጣሚ ደጋፊዎቹ ተሰባሰቡ፤ ሥራ አስኪያጁ አቶ ታዬም አቀረበኝ፡፡ የቅጥር ውድድር ሳይኖር የእኔን ሹመት አጸደቁ፡፡ ክለቡን ስረከብ ብዙዎቹ ተጫዋቾች ለቀው አራት ልጆች ብቻ ነው የቀሩት፡፡ ክለቡ በርካታ ትልልቅ አሰልጣኞችን ቀጥሮ ለሰባትና ስምንት ዓመታት ወደ ላይኛው ሊግ ሊመለስ አልቻለምና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ይታይ ነበር፡፡ ሰበታ የተሟላ ፋሲሊቲ ያቀርባል፤ ብዙ ደጋፊዎች አሉት፤ ከፍተኛ የውጤት ማምጣት ጉጉት አለ፡፡ ነገርግን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደግ ተስኖት ሰንብቷል፡፡ እኔ ስደራደር ” ሰበታን ወደ ፕሪምየር ሊጉ አሳድገዋለሁ፡፡” አልኳቸው፡፡ ይሁን እንጂ ወዲያው ያን ለማሳካት በጣም አስቸጋሪ እንደሚሆን ተረዳሁ፡፡ አዳማ ለዝግጅት በሄድንበት ወቅት የተወሰኑ ልጆችን በማየት ብቻ መለመልኩ፤ ሌሎቹን ደግሞ ልምድ ያላቸው እንዲሆኑ አደረግሁ፡፡ በተናጠል ብቃት ጎልቶ የወጣ ተጫዋች ባይኖረኝም በቡድን ሥራ፣ በማሸነፍ ሥነ ልቦና እና በመሳሰሉት አሸናፊዎች ሆንን፡፡ እንዲያውም በቂ የዝግጅት ጊዜም አልነበረንም፡፡ ሃያ አምስት ቀናት ብቻ ነው የተዘጋጀነው፡፡ ሶስት የወዳጅነት ጨዋታዎች አድርገን ነው ውድድሩን የጀመርነው፡፡ አንደኛውንም ሆነ ሁለተኛውን ዙር በመሪነት አጠናቀቅን፤ ዋንጫውንም አሸነፍን፡፡ ሌላ ሃገር ቢሆን ትልቅ የብዙሃን መገናኛዎች ሽፋን ያገኝ ነበር፡፡ ለዓመት ያህል ሳይሸነፍ የቆየ የሚደነቅ ክለብ ሆኗል ሰበታ፡፡


ሰበታን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ስታሳልፍ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠኸው ቃለ ምልልስ ” ለፕሪምየር ሊጉ የተጋነነ ነገር አናስብም፡፡ በትንሽ ወጪ ጥሩ ቡድን ለመሥራት አስባለሁ፡፡” ብለህ ነበር፡፡ ያው ሳይሳካ ቀርቶ ክለቡን ለቀሃል፡፡ ባትለቅ ኖሮ ግን በምን መልኩ ነበር ቡድኑን ልታዘጋጅ ያሰብከው?

★ በሰበታ ጉዳይ እኔ ብቻ ሳልሆን ቤተሰቤም ተጎድቷል፡፡ ስታዲየሙ ከመኖሪያችን አካባቢ ስለሚቀርብ ልጆቼም ባለቤቴም ጨዋታችንን ያዩ ነበር፡፡ ‘ህዝቡም በጣም ይወደኝ ነበር፡፡’ ማለት እችላለሁ፡፡ ይህ መሆን የቻለው በየሳምንቱ ውጤት ስለማመጣ ነው፡፡ በከፍተኛ ሊጉ በሜዳም ሆነ ከሜዳ ውጪ ማሸነፍ ከባድ ነው፡፡ እኔ ውጤቱ የራሴ ብቻ ነው አልልም፤ ፈጣሪም አግዞኛል፡፡ መቶ በመቶ በራስ የመተማመን ስሜቱ ነበረኝ፡፡ የለፋሁትም እንደማሳካው ስለሚሰማኝ ነበር፡፡ በእርግጥ መሬት አለ፤ ገንዘብ ይሰጥሃል፤ የተለያዩ ሽልማቶች ልታገኝ ትችላለህ፡፡ ለእኔም ጥሩ ሽልማት ሰጥተውኛል፡፡ ይሁን እንጂ ፍላጎቴ ፕሪምየር ሊጉ ላይ ወጥቼ ለመሥራት ነበር፡፡ እንዲህ ለፍተህ፤ ቡድን ወደ ላይ አሳድገህ ስትሰራ የበለጠ በራስ የመተማመን መንፈስ ይኖርሃል፡፡ ምክንያቱም የምትመራው ራስህ ያሳደግኸው ቡድን ስለሆነ፡፡ ‘ዘንድሮ በማስበው የአጨዋወት መንገድ እሰራለሁ፡፡’ ብዬ ምልመላ ጀምሬያለሁ፤ አንዳንድ በአማካይነት የሚጫወቱ ወጣት ተጫዋቾችንም አነጋግሬያለሁ፡፡ አማካይ ክፍሉን ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቼ ነበር፡፡ ‘ክለቡ ወጪ ማውጣቱ ባይቀርም የተጋነነ እንዳይሆን በመካከለኛ ደረጃ ያሉ ተጫዋቾችን አምጥቼ ከበፊት ጀምሮ የማምንበትን አጨዋወት የሚተገብር ቡድን እሰራለሁ፡፡’ ብዬ አቅጄ ነበር፡፡ ግን ሳይሳካ ቀረ፤ በእውነት እኔ መሰናበቴን አላሰብኩም፡፡ ለሽልማት ተጠርቼ ስሄድ አንዳንድ ሰዎች እየመጡ ” ትናንት ስብሰባ ነበር፡፡ ተነስተሃል፡፡” ይሉኛል፡፡ በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙ ሶስት አራት የሚሆኑ ደጋፊዎች ” አዝነናል፤ አይዞህ!” ይሉኛል፡፡ እኔ ከክለቡ ምንም ስላልሰማሁ ‘ እንዴ! ምንድን ነው የሚያወሩት?’ እላለሁ በውስጤ፡፡ የሽልማት ስነ ሥርዓቱ በተካሄደበት ቦታ ቤተሰቤን ይዤ ነው የሄድኩት፡፡ በኋላ ልጆቼ ተከፍቼ እንዳያዩኝ እንደምንም ስሜቴን ደብቄ ወደ ቤታችን ሄድን፡፡ ማታ እንቅልፍ የሚባል ነገር አልወሰደኝም፡፡ በማግስቱ ተደውሎልኝ ተጠርቼ ስሄድ ሥራ አስኪያጁ ” ልምድ ስለሌለህ ካቢኔው በስብሰባ እንድትሰናበት ወስኗል፡፡ ቀሪ ኮንትራት ስላለህ በስምምነት እንለያይ፡፡” አለኝ፡፡ እንግዲህ በሽልማቱ ማግስት ነው ይህ የሆነው፡፡ ” በብስጭት ውስጥ ሆኜ ‘እኔ የምወስነው ከቤተሰቤ ጋር ተነጋግሬ ነው፡፡ እንዲያውም ኮንትራቴን እጠብቃለሁ፡፡’ አልኩ፡፡ ተናደድኩና ስሜታዊ ሆንኩ፡፡ እናንተ የምትፈልጉትን አድርጉ፤ እኔ ግን ኮንትራቴን እጠብቃለሁ፡፡’ ብዬ ከቢሮ ወጣሁ፡፡ እኔንና ምክትሌን ነበር የጠሩን፡፡ ከዚያ እኔ ቤተሰቦቼን ልጠይቅ ወደ ወንጂ ሄድኩ፡፡ ያው ሰዎች በእኔ ቦታ ጸጋዬ መተካቱን እንደሰሙ ይነግሩኝ ነበር፡፡ በእናንተ ሚዲያ ላይ ደግሞ ጸጋዬ “…..አናግረውኛል፡፡” አለ፡፡ እኔ ደግሞ “…..ኮንትራት አለኝ፡፡” ብያለሁ፡፡ በዚህ መሃል ደጋፊው “እንዴት?” የሚል ጥያቄ አነሳ፡፡ ያኔ የክለቡ ኃላፊዎች እንደገና ጠርተውኝ ” በስምምነት እንለያይ!” አሉኝ፡፡ እኔም

‘ አቋሜ ከዚህ በፊት እንደገለጽኩላችሁ ነው፡፡ እናንተ ማንንም መቅጠር ትችላላችሁ፤ እኔ ግን ኮንትራቴን ጨርሼ ነው የምለቀው፡፡” አልኳቸው፡፡ የትኛውም ክለብ የፈለገውን አሰልጣኝ መቅጠር መብቱ ነው፡፡ ነገር ግን ውሳኔያቸውን ቀደም ብለው ቢያሳውቁኝ ጥሩ ነበር፡፡ አንዳንድ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ማስታወቂያ አውጥተው ስለነበር እኔም እሳተፍ ነበር፡፡ ሰበታን ወድጄዋለሁ፤ ደጋፊው ደስ ይላል፤ ጥሩ ፋሲሊቲ አለው፡፡ በእርግጥ መጨረሻ ላይ ቅር ቢያሰኙኝም አብረውኝ የሚሰሩት ኮሚቴዎች ጥሩ ነበሩ፡፡ ስለዚህ መቶ በመቶ ሰበታ እንደምቆይ እርግጠኛ ሆኜ ተቀመጥኩ፡፡ ከዚያ በኋላ ክለብ የመፈለግ ጊዜው አለፈ፡፡ ሰዎች “እንዳትቀመጥ” ይሉኛል፡፡ እኔ ግን ገና ለገና ‘እቀመጣለሁ!’ ብዬ የማይሆን ቦታ አልሄድም፡፡ እንዲያውም ታንጸህ ትመለሳለህ፤ የሚፈልግህ ክለብ ይመጣል፡፡ አስበህ፣ ሰከን ብለህ፣ በብዙ ነገሮች ተዘጋጅተህ፤….. ስትሄድ በፍላጎት ትሰራለህ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ማንንም ልቀየም፥ ማንም እንዲቀየመኝም አልፈልግም፡፡ በወቅቱ ቤተሰብም ተጎድቶ፥ እኔም ተናድጄ ነበር፡፡ ክለቡ ቀድሞ ቢያሳውቀኝ፣ ከሰዎች ከምሰማም ለራሴ ቢነገረኝ መልካም ነበር፡፡ ምክንያቱም ክለቡ እኔን ማክበር አለበት፤ እኔም ክለቡን ማክበር አለብኝ፡፡ አሁን ግን ሁሉም አልፏል፡፡


ይህ ጉዳይ የተለመደ ነው፤ ከዚህ ቀደም በሌሎች ክለቦችም ተከስቷል፡፡ አሰልጣኞች ከከፍተኛ ሊጉ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ክለብ ካሳደጉ በኋላ ይሰናበቱና አዳጊ ክለቦቹ ለሌሎች “በፕሪምየር ሊጉ የማሰልጠን ልምድ አላቸው፡፡” ተብለው ለሚታሰቡ አሰልጣኞች ይሰጣሉ፡፡ እንዴት አንተ ይህን አልጠበቅህም?

★ አዎ! ተለምዷል፡፡ ደረጄ በላይ ወጥቷል፡፡ ካቻምና የሃዲያ ሆሳናው አሰልጣኝ ይኸው ዕጣ ደርሶበታል፡፡ አሁን ግን ከስህተታቸው ተምረው ለሁለተኛ ጊዜ አስቀጥለውታል፡፡ እኔ ከውጤቱ ፣ ከቡድኑ እንቅስቃሴ፣ ከሥራ አመራሩ ጋር ከመሰረትኩት ቅርበትና በከተማው ውስጥ ካለኝ ድጋፍ አንጻር ምንም አይነት ጥርጣሬ አላሳደርኩም፡፡ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካለፍን በኋላ ደስ የሚል ስሜት ውስጥ ነበርኩ፡፡ ነገሩ ሲከሰት ሚዲያው በጣም አጋነነው፡፡ የእናንተ ድረገጽ ላይ ብዙ አስተያየቶች ተጻፉ፡፡ የትሪቡን ስፖርት ፕሮግራም ላይም ፕሬዘዳንቱ ” ክፍሌ እንዴት ‘ልምድ የለውም፡፡’ ይባላል?” ተብሎ ተጠየቀ፡፡ ህዝቡ ደገፈኝ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን እኔ ክፍለ ሃገር ነበርኩ፡፡ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየት የሰጠሁትም በስልክ ነበር፡፡ ጸጋዬ

” አናግረውኛል፡፡” ማለቱና እኔ ደግሞ ” ኮንትራት አለኝ፡፡” ማለቴ ትርምስ ፈጠረ፡፡ በቃ ይህ ግን የአሰልጣኝ የሥራ ባህርይ ነው፡፡ ዋንጫ አጣህም-አገኘህም ትባረራለህ፡፡ ባለ ድል ሆነህም ትባረራለህ፤ ሳትስማማ ትለቃለህ፤ የተሻለ አግኝተህ ትወጣለህ፤….. የአሰልጣኝነት ሙያ አንድ አካል ነው፡፡ እነርሱ ማባረርም መቅጠርም መብታቸው ነው፡፡ ካላመኑብኝ አያባሩኝ አልልም፤ ነገር ግን ለሰራሁት ትንሽ ሥራም ቢሆን ክብር ሊሰጡኝ ይገባ ነበር፡፡ እኔ አሁንም በደጋፊው ትልቅ አክብሮትና ፍቅር አለኝ፡፡ አሁንም ወደዚያ ብሄድ እከበራለሁ፤ ጥሩ ሥራ ሰርቻለሁና፡፡ እግርኳስ ከደጋፊውና ከህዝቡ ጋር አግባብቶኛል፡፡ አንድም ቀን ክፉ ሳይናገሩኝ ኖረዋል፤ ዋንጫ በወሰድንበት የመጨረሻው ቀንም ተጫዋቾች ሳይሆኑ ደጋፊው ነው ከጎል እስከ ጎል ተሸክሞኝ የወሰደኝ፡፡ በፍቅርም መለያየት አንድ ትልቅ ነገር ነው፡፡


በየመሃሉ ያለ ሥራ የተቀመጥክባቸው ወቅቶች ነበሩ ማለት ነው?

★ አዎ! አሉ፡፡ አልፎ አልፎ ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ፦ ከጅማ ወጥቼ ሰበታ እስክመጣ ድረስ ወደ ዘጠኝ ወይም አስር ወራት ያህል አርፌያለሁ፡፡


ከአንድ ክለብ ወደ ሌላኛው ክለብ ለመዛወር ቢያንስ ስድስት ወራት ያህል ይፈጅብሃል?

★ አዎ! አሁን ራሱ’ኮ ተቀምጫለሁ፡፡ የሚመችህን ክለብ እስክታገኝ ድረስ ትቆያለህ፡፡ ዝም ብለህ ገፍተህ ሄደህ ብቻ ቡድን መረከብ የለብህም፡፡ በመድን ቆይታዬ ብዙ ተምሬያለሁ፤ ለገንዘብ ተብሎ ሲገባ ስምም ይታጣል፤ የያዝከው አቅም ላይ ጥርጣሬ ታጭራለህ፡፡


ይቀጥላል…


[ክፍል 1 – ቀደምት የአሰልጣኝነት ዓመታት]

[ክፍል 2 የኢትዮጵያ ቡና እና የኢትዮጵያ መድን ቆይታ]


©ሶከር ኢትዮጵያ