ስለ ሞገስ ታደሰ በቅርበት የሚያውቁት ይናገራሉ

👉 “ሞገስ በጣም ጠንካራ ሠራተኛ፣ ሜዳ ላይ ለቡድኑ ሁሉን ነገር የሚሰጥ፣ ታዛዥ የዋህ ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ህልም የነበረው ተጫዋች ነው” አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ

👉 “በባህሪውም ከሁሉም ተጫዋቾች ጋር የሚግባባ ቀልድ አዋቂ ነው። ቤተሰቦቹን የሚረዳ ተጫዋች ነበር” ተጫዋች ምንተስኖት አዳነ

👉 “ከፀበል ከመጣ አንድ ወር ሆኖታል፤ ከአንድ ሳምንት በፊት ምንም ነገር መናገር የማይችልበት ደረጃ ደርሶ ድምፁን ዘግቶት ቆይቷል” የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና አንበል ኤፍሬም ወንድወሰን

ህዳር 5 ቀን 1983 የተወለደው ሞገስ ታደሰ እግርኳስ መጫወት የጀመረው ተወልዶ ባደገበት ጃንሜዳ አካባቢ ነው። በዚህ አካባቢ ሲጫወት የተመለከተውና በርካታ እግርኳሰኞችን በማፍራት የሚታወቀው አሰልጣኝ አለባቸው ኪዳኔ የእግርኳስ ክህሎቱን በመመለክት ኬር-ስኩዌር በሚባል የታዳጊ ቡድን እንዲጫወት አድርጎታል። በዚህ ቡድን ሲጫወት ቆይቶም ቅዱስ ጊዮርጊስ በ1999 በየአካባቢው ታዳጊዎች በተስፋ ቡድኑ ለማካተት በሚያደርገው ምልመላ ቅዱስ ጊዮርጊስን መቀላቀል ችሏል።

ሞገስ በቅዱስ ጊዮርጊስ በፍጥነት ባሳየው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ 2001 ላይ በዋናው ቡድን እና ተስፋ ቡድኑ እየተመላለሰ ሲጫወት ቆይቶ ከ2002 ከዋናው ቡድን ጋር ተቀላቅሎ መጫወት የቻለ ሲሆን ከፈረሰኞቹ ቆይታው በኋላ ወደ ሲዳማ ቡና በማምራት ጥሩ ጊዜያትን በማሳለፍ የብሔራዊ ቡድን ጥሪም ሊደርሰው ችሏል። በመቀጠል ከ2007 ጀምሮ በእግርኳስ ሕይወቱ ጥሩ ጊዜ ወዳሳለፈበት አዳማ ከተማ ካመራ በኋላ ለሁለት ዓመታት ተጫውቷል። በአዳማ በሚጫወትበት ወቅት አደጋ ደርሶበት ከተጎዳ በኋላ በ2010 በወልዲያ እና በመጨረሻም በኢትዮ ኤሌክትሪክ ለጥቂት ጊዜያት ተጫውቶ ጉዳቱ እየተባባሰ በመምጣቱ ከእግርኳሱ ርቆ ህክምናውን ሲከታተል ቆይቷል። ዛሬ ረፋድ 06:00 ላይም ህይወቱን ማትረፍ ሳይቻል ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

ሶከር ኢትዮጵያም ሞገስ ማን ነበር ስትል እርሱን በቅርብ ርቀት የሚያቁትን ጠይቃ ይህን ዘገባ አቅርባለች።

ከመነሻው የእግርኳስ ህይወቱ አንስቶ በተስፋ ቡድን እና በዋናው ቡድን ያሰለጠነው የአሁኑ የባህር ዳር ከተማ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ስለ ሞገስ እንዲህ ይናገራል።

” ሞገስ በጣም ጠንካራ ሠራተኛ፣ ሜዳ ላይ ለቡድኑ ሁሉን ነገር የሚሰጥ፣ ታዛዥ የዋህ ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ህልም የነበረው። ከታመመ በኃላ በተደጋጋሚ ስልክ እደውልለት ነበር። ድኖ ለመነሳት ያለው ህልም ጉጉት በጣም ትልቅ ነበር። አንዳንዴ መኖር ዋጋ እንዳለው ከእርሱ አይቻለው። እየዳነ እንደሆነ ይነግረኝ ነበር። በመጨረሻ ፈጣሪ የፈቀደው ሆኖ ህይወቱ ማለፉን ስሰማ በጣም ነው ያዘንኩት። ፈጣሪ ነፍሱን በገነት ያኑረው ለቤተሰቦቹም መፅናናትም እመኛለው።”

በተስፋ ቡድን አብሮት ተጫውቷል፤ ምንም እንኳ ሞገስ ቀድሞ ወደ ዋናው ቡድኑ ቢያድግም ኋላ ላይ አብሮት ለመጫወት ችሏል። በቅርብ ርቀት ሞገስን ከሚያቁት ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው የፈረሰኞቹ አንበል ምንተስኖት አዳነ ስለ ቀድሞ የቡድን አጋሩ ይህን ይላል።

” በመጀመርያ የሞገስን እረፍት ስሰማ በጣም ነው የደነገጥኩት፣ ከህመሙ እያገገመ እና እንደተሻለው ነበር የሰማሁት፤ ይህ በመሆኑ በጣም አዝኛለው። ሞገስ ጋር ከታዳጊ ቡድን እስከ ዋናው ቡድን ድረስ አብረን በተጫወትንባቸው ጊዜያት በጣም ታታሪ ጠንካራ ተጫዋች፣ ሁሌም ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ያስብ ነበር። በባህሪውም ከሁሉም ተጫዋቾች ጋር የሚግባባ ቀልድ አዋቂ ነው። ቤተሰቦቹን የሚረዳ ተጫዋች ነበር።”

የህመሙ ሁኔታ ከፍተኛ ደረጃ መድረሱ ከተሰማ ጊዜ አንስቶ ከህመሙ አገግሞ ወደሚወደው እግርኳስ እንዲመለስ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግለት በተጠየቀበት ጊዜ ሁሌም ለበጎ ነገር ቀድሞ የሚደርሰው የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና አንበል ኤፍሬም ወንድወሰንም ስለሞገስ የመጨረሻ የህይወቱ ጊዜያት አስመልክቶ ይሄን ይናገራል።

“ህመሙ ነርቭ እንደሆነና ከኢትዮጵያ ውጭ ሄዶ መታከም እንዳለበት ሲነገረን ኮሚቴ በማዋቀር ለህክምናው ወጪ የሚሆን ገንዘብ ለማሰባሰብ ችለናል። ሆኖም ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖረው ህክምና እንክብካቤ ብቻ እንደሆነ እና እንክብካቤው በተለያየ ወቅት እየተመላለሰ እንደሆነ አንዴ ሄዶ እስኪመለስ 7ሺህ የአሜሪካ ዶላር ወጪ እንደሚጠይቅ ተነግሮናል። ህክምናውን ውጭ ሀገር ሳይሄድ ሀገር ውስጥ ሆኖ በፊዚዮቴራፒስት እንክብካቤውን ማድረግ እንደሚችል ሲነገረን ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ከምናደርግ እዚሁ መከታተል ይችላል ብለን ህክምናውን በጥሩ ሁኔታ እየተከታተለ ለውጥም መመልከት ጀምረን ነበር። በኋላ ላይ የቤተሰብ ፍላጎት ሆኖ የእናቱ ቤተሰቦች ህመሙ የሆነ ነገር አድርገውበት ይሆናል በሚል ወደ አንድ የፀበል ቦታ ይዘውት ሄደዋል። በዚህም ለሦስት ወር ያህል ቆይቶ ተመልሷል። ፀበል ቦታ ቅዝቃዜ ስለሚኖር እና ህመሙ ክትትል የሚደረግለት ከሙቀት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ህመሙን ሊያብስበት እንደሚችል አስቀድሞ ተነግሮ የነበረ ቢሆንም ያው የታሰበው ሳይሆን ህመሙ ጠንቶበት ተመልሷል። ከፀበል ከመጣ አንድ ወር ሆኖታል። ከአንድ ሳምንት በፊት ምንም ነገር መናገር የማይችልበት ደረጃ ደርሶ ድምፁን ዘግቶት ቆይቷል። ትናንት ማታ ህመሙ ሲብስበት ወደ የካቲት ሆስፒታል ይዘነው በመሄድ የህክምና ባለሙያዎቹም ህይወቱን ለማትረፍ ከፍተኛ ርብርብ ቢያደርጉም ዛሬ ስድስት ሰዓት ላይ ህይወርቱ ሊያልፍ ችሏል። ”

ባለትዳር እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት የነበረው ሞገስ ታደሰ የቀብር ሥነ ሥርዓት ነገ (ዓርብ) የካቲት 6 ቀን 2012 በቀጨኔ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን የሚፈፀም ይሆናል።

©ሶከር ኢትዮጵያ