“ሲዮ ጋሞ ናዬ ታፌ ሲዮ…” የአምስት ጊዜ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪው ትውስታ በታፈሰ ተስፋዬ አንደበት

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለአምስት ጊዜያት ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ያጠናቀቀው ባለ ሪከርዱ ታፈሰ ተስፋዬ (ዶዘር) የዛሬ ትውስታ አምዳችን እንግዳ ነው።

በታዳጊነት ዕድሜው በጃን ሜዳ ሲጫወት አዛውንት፣ የቀን ሠራተኞች፣ ታዳጊዎች ሳይቀር የእርሱን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ለመመልከት ይሰበሰቡ ነበር። ይህ ጉልበተኛ እና ፈጣን አጥቂ ገና በታዳጊነቱ በቀድሞ ኢንተርናሽናል ዳኛ የአሁኑ የየካ ክ/ከተማ ም/አሰልጣኝ ዘካርያስ ግርማ ፕሮጀክት በ1992 በመግባት ይሰራ ነበር። ኢትዮ ኤሌክትሪክም አቅሙን አይቶ ከ1993-98 ድረስ በክለቡ አጫውቶታል። በጊዜው እነ ዮርዳኖስ ዓባይ፣ ስምኦን ዓባይ፣ ጥላሁን ታደለ የመሳሰሉ አጥቂዎች በቡድኑ ውስጥ ቢኖሩም ይህን ሰብሮ ለመግባት ያልተቸገረው ታፈሰ ተስፋዬ ትራንስ ኢትዮጵያ ላይ በ1993 በማስቆጠር ነበር የጎል አካውንቱን መክፈት የጀመረው።

ወደ ፊት ኳስ ይዞ ከሮጠ ተከላካዮች እርሱን ለማቆም የሚቸገሩበት ይህ ፈጣን አጥቂ ከአሳዳጊው ክለብ ጋር ተለያይቶ በ1998 ነበር ብዙ ወደተዘመረለት እና ከፍተኛ ተወዳጅነት ወዳገኘበት ኢትዮጵያ ቡና ያመራው። የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ለእርሱ ያላቸውን አክብሮት ለመግለፅ “ሲዮ ጋሞ ናዬ ታፌ ሲዮ ” ሲሉ በህብረት ዘምረውለታል። እስከ 2002 በኢትዮጵያ ቡና ቆይቶ ለአንድ ዓመት ወደ የመን ሊግ አምርቶ ሲመለስ በድጋሚ ለሁለት ዓመት ለኢትዮጵያ ቡና ተጫውቷል። በመቀጠል ሀዋሳ ከተማ፣ አዳማ ከተማ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እስከ 2011 ድረስ የተጫወተባቸው ክለቦች ናቸው። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በታዳጊ፣ በኦሊምፒክ እና ዋናው ብሔራዊ ቡድን ለረዥም ዓመት በመጫወት ሀገሩን አገልግሏል። ይህ አይተኬ አጥቂ አንድ ጊዜ የፕሪምየር ሊጉ ኮከብ ተጫዋች (2000) በመሆን ክብርን ካገኘበት ዝናው ይልቅ (1996, 1998፣ 2001፣ 2002 እና 2008) ለአምስት ጊዜ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ በማጠናቀቅ ባለ ሪከርድ ሆኖ ያጠናቀቀበት እና ብቸኛ ባለታሪክ የሆነበት ነው። በዛሬው የትውስታ አምዳችን ከዚህ ፈጣን አጥቂ ጋር ባደረግነው አጭር ቆይታ ስለ ሪከርዱ ያወጋናል።

” አንድ አጥቂ ወደ ሜዳ የሚገባው ጎል አስቆጥሮ ደጋፊውን ለማስደሰት ክለቡን፣ መጥቀም እና ውጤታማ ለማድረግ ነው። በዚህ ረገድ በጣም እድለኛ ነኝ። ብዙ ተዘምሮልኝ እኔም ጎል አግብቼ በብዙ ጨዋታዎች ላይ ወጥቻለው። ከምንም በላይ ይህን ሪከርድ በመያዜ በጣም ደሰተኛ ነኝ። ይህ ክብር እና ዝና ያገኘሁት ጠንክሬ በመስራት በመሆኑ ሁሌም ወደ ኋላ ሳስበው ያስደስተኛል። ከምንም በላይ በዚያ ሁሉ የቡና ደጋፊ ፊት እየተዘመረልህ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆነህ ስምህ ተጠርቶ መሸለም ልዩ ስሜት ይፈጥርብሀል። የእኔን ፍላጎት እና አቋቋም አይተው በርከት ያሉ ጎሎች እንዳስቆጥር ረዥም አመት አብረውኝ የተጫወቱት ዕድሉ ደረጄ እና ቢንያም ኃይሌ (ዋሴ) ብዙ አስተዋፆኦ አድርገውልኛል። ኢትዮጵያ ቡና ውስጥ እንደዛ እንደመልፋቴ የ2003 ዋንጫን በቡድኑ ውስጥ ሆኜ አለማንሳቴ በጣም ብቆጭም ወንድሜ ተክሉ ተስፋዬ ይህን ዋንጫ ማግኘቱን ሳስብ እደሰታለው። ይሄን ዓመት ከሜዳ ርቄያለው። ፈጣሪ ሀገራችንን ይጠብቅልን እንጂ በቀጣይ ዓመት ወደ ሜዳ እመለሳለው። ”

ታፈሰ እንደሚታወቀው ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር በዘንድሮ ዓመት ክስ ላይ የሚገኝ ሲሆን ጉዳዩ ውሳኔ አግኝቶ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ይግባኝ በመጠየቅ በሒደት ባለበት የወቅቱ በሽታ ኮሮና መጥቶ ጉዳዩን አቁሞታል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ