“ፀጉር የተነቀለበት ክስተት…” ትውስታ ዐቢይ ሃይማኖት

በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ከተከሰቱ አይረሴ ገጠመኞች መካከል በ1987 ሙሉጌታ ከበደ ፀጉር የተነቀለበትን አጋጣሚ ነው። በዛሬው የትውስታ አምዳችን ይህን ክስተት ልናስቃኛቹ ወደድን።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ቤተሰብ ዘንድ መቼም የ1987 የባንክ ቡድን አይረሳም። በታሪክ የመጀመርያው የኢትዮጵያ ሻምፒዮን ሆኖ ለማጠናቀቅ ንግድ ባንክ ሦስት ዕድሎች ነበሩት። ማሸነፍ፣ ነጥብ መጋራት እንዲሁም ከሁለት በላይ ጎል ሳይቆጠርበት መሸነፍ። በአንፃሩ ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋንጫውን ለማንሳት ከነበረበት ደካማ አጀማመር አንሰራርቶ የነበረበትን የነጥብ መራራቅ በተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሎ ከንግድ ባንክ በሁለት ነጥብ አንሶ ዋንጫውን ለማንሳት ከሁለት ጎሎች በላይ አስቆጥሮ ማሸነፍ ብቸኛው ዕድሉ ነበር።

በእለተ እሁድ ይህን አጓጊ የመጨረሻ ጨዋታ ለመከታተል በርካታ ተመልካች በአዲስ አበባ ስታዲየም ታድሟል። ኢንተርናሽናል የቀድሞ ዳኛ ኃይለመላክ ተሰማ ጨዋታውን ለመምራት ከረዳት ዳኞቹ ጋር በመሆን ሁለቱን ቡድኖቹን አስከትሎ ወደ ሜዳ ገብተዋል። ጨዋታው ተጀምሮ ሦስት ዕድሎችን ይዘው ወደ ሜዳ የገቡት ንግድ ባንኮች በመጀመርያው አጋማሽ ጎል አስቆጥረው ጨዋታውን የበለጠ በመቆጣጠር ዋንጫ የማንሳት ዕድላቸውን አስፍተው ነበር። በዚህች ድንገተኛ ጎል የተደናገጡት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በስታዲየም ውስጥ በዝምታ ተውጠዋል። ፈረሰኞቹ ተጫዋቾች ጎል ፍለጋ ያለ የሌለ ጉልበታቸውን ተጠቅመው ጫና ፈጥረው ይጫወታሉ። በአንፃሩ ንግድ ባንኮች በመከላከሉ ላይ ተጠምደዋል። የቅዱስ ጊዮርጊስ የምንጊዜው ምርጥ አጥቂ ሙሉጌታ ከበደ (ወሎዬው) አቻ የምታደርገውን ጎል አስቆጥሮ በዝምታ የተዋጠውን ደጋፊ አነቃቅቶታል፣ ቡድኑንም ወደ ጨዋታ ይመልሰዋል። አሸናፊ ሲሳይ ሁለተኛ ጎል አክሎ ጨዋታውን የበለጠ አግሎት የንግድ ባንክ ተጫዋቾችን ተረባብሸው ድንጋጤ ውስጥ ከቷቸዋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 87ኛው ደቂቃ ላይ ደርሷል።

ንግድ ባንክ በአስራ አራተኛው ሳምንት እስከ 87ኛው ደቂቃ ድረስ ውድድሩን እየመራ በታሪክ የመጀመርያውን የኢትዮጵያ ሻምፒሆን ሆኖ ለማጠናቀቅ ሦስት ደቂቃዎች ይቀሩታል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አንድ ጎል በቀሩት ጥቂት ደቂቃዎች በማስቆጠር ሻምፒዮን ለመሆን ግዴታ ውስጥ ገብተዋል። ከዚህ በኋላ ነው ድራማዊ የሆነው ክስተት የተፈጠረው። ቁመተ አጭሩ ሙሉጌታ ከበደ ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ ለማራቅ የንግድ ባንኩ ተከላካይ ዐቢይ ሃይማኖት ለመዝለል በሚያስብበት ወቅት ሙሉጌታ ከዳኛው ዕይታ ውጭ የዐብይ ፀጉሩን በመጎተት ኳሱ ላይ እንዳይደርስ በማድረግ ፋሲል አብርሀ በግንባሩ ባስቆጠራት ጎል ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው 3-1 በሆነ ውጤት ተጠናቆ ፈረሰኞቹ የዋንጫ ባለቤት ይሆናሉ። ባንኮች ዓመቱን ሙሉ የለፉበትን፣ ሦስት ዕድል ይዘው ወደ ሜዳ ገብተው ዋንጫ ያጡበት እና ሜዳ ውስጥ በሀዘን ያነቡበት ሁኔታ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች “ጉሮሸባይ” በማለት ወደር የሌለው ደስታቸውን የገለፁበት መንገድ መቼም የሚዘነጋ አይደለም።

በዚህ ቡድን ውስጥ ከነበሩ ተጫዋቾች መካከል እና ፀጉሩ የተነቀለበት ዐቢይ ሃይማኖት አንዱ ነበር። ይህን አስገራሚ ትይንት እና ፀጉሩን ሙሉጌታ ከበደ የነቀለበትን አጋጣሚ በትውስታ አምዳችን ሃያ አምስት ዓመታት ወደ ኃላ መለስ ብሎ እንዲህ ያስታውሰናል።

“ዋንጫ ለማንሳት የመጨረሻው ጫፍ ላይ ደርሰናል። ቀድመንም ጎል አስቆጥረን ጨዋታውን ከተቆጣጠርን በኋላ ምን እንደተፈጠረ አላውቅም። እስካሁን ድረስም ለምን እንደሆነ አይገባኝም። ዋንጫ ማንሳት ሲገባን ያው በተለይ የሙሉጌታ ከበደ ብልጠት ቡድኑን የበለጠ ጠቅሞት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋንጫን ሊያነሳ ችሏል። አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው ብዙ ስህተቶች ነበሩን እንዴት ጨዋታውን ተቆጣጥረን ውጤት ማስጠበቅ እንደነበረብን ያንን የመረዳት አቅም (ብስለት) ባለመኖሩ ውጤታችንን አሳልፈን ሰጥተናል። ያው በጣም የሚቆጨን አጋጣሚ ሆኖ አልፏል። አስታውሳለው ባዛን ጊዜ ሙሉጌታ ከበደ ከኋላዬ ሆኖ ፀጉሬ ረጅም በመሆኑ ይመች ስለነበር ይዞት ሲጎትተው አየህ ማልያም ይዞ ከሚጎትት ይመስለኛል ፀጉሬን ይዞ ወደ ኃላ ለማስቀረት ብልጠት ይመስለኛል (እየሳቀ)። ትዝ ይለኛል ፀጉሬን እንደነጨው፣ እንደነቀለው አስታውሳለው። ወቅቱ ለሙሉጌታ ከበደ ጥሩ ጊዜ ነበረ። በጣም ትልቅ አቅም ያለው ተጫዋች ነው። ልምዱን፣ በብስለቱ እና ብልጠቱን ተጠቅሞ ቡድኑ ውጤት ይዞ እንዲወጣ አድርጓል። ያው ለእኛ እጅግ የሚያስቆጭ ትልቅ ቁጭት የሚፈጥር ነው። እስካሁን ድረስ የሚሰማኝ ስሜት አለ ይህን ዋንጫ አለማንሳታችን። ”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: