የደጋፊዎች ገፅ | ቆይታ ከፋሲል ከነማ የደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ኃይለማርያም ፈረደ ጋር

በቅርብ ዓመታት በተለይም ፋሲል ከነማ ወደ ፕሪምየር ሊግ ከመጣ በኋላ ጥሩ አደረጃጀት ፈጥረዋል ከሚባሉ የደጋፊ ማኅበራት መካከል አንዱ ከሆነው የፋሲል ከነማ ደጋፊ ማኅበር ፕሬዝዳንት ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገናል ።


ማኅበሩ ራሱን ለማሻሻል ምን አይነት ሥራዎች እየሠራ ነው?

አዲስ  ስራ አስፈፃሚ ምርጫ ተደርጎ ወደ ሥራ ከተገባበት ህዳር 2012 ጀምሮ ከደጋፊዎች ይነሱ የነበሩ የፋይናንስ ብክነትና ግልፃነት የጎደላቸው አሰራሮችን የሚደፍኑ አሰራሮች በመዘርጋት አገልጋይነት ብቻ ተቀብለው በሚያገለግሉ ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማደራጀት ችግሮቹን የመቅረፍ፣ የገቢ ማስገኛ እቅድ አውጥቶ ከተራዘሙ እቅዶች ውጭ ያሉትን የአባላት ማፍራትና ሌሎች ሥራዎች እየሰራ ይገኛል።

ባለፈት ዓመታት ደጋፊ ማኅበሩ ምን አሳክቻለው ይላል?

ምስጋና ከመሠረቱ ደጋፊ ማህበሩን ላቋቋሙ፣ በተለያየ ጊዜ በአመራርነት ተመርጠው ማህበሩን ለማሻሻል አበርክቶ ላደረጉ ወንድሞቻችን ይግባና ማኅበሩ ግልፅ የሆነ መተዳደሪያ ደንብ ያለው፣ ከአስተዳደርና ፋይናንስ እስከ ሽያጭ ሰራተኛ ያለው ተቋም ለመሆን በቅቷል። ይህ ለማኅበሩ ስኬት ሲሆን ዛሬ ተረኛው እኛ ላይ ደርሶ ይህን ተቋም እንደመረከባችን ማኅበሩ ይበልጥ ለማጠናከር አሰራሮችን በመዘርጋት በቀጣይም ትልቅና ለሌሎች ደጋፊ ማኅበራትም በአርዓያነት ተጠቃሽ ሆኖ እንዲቀጥል እያሰራን እንገኛለን ።

ፋሲል በርካታ ደጋፊ ያለው ክለብ ነው። ነገር ግን አብዛኛው ደጋፊ የተመዘገበ ደጋፊ አይደለም። መታወቂያ በማስያዝ ረገድ ምን እየሰራችሁ ነው ?

ፋሲል ከነማ በሜዳው ላይ ያለውን ተመልካች ያክል እና ራሱን የክለቡ ደጋፊ ነኝ ብሎ ከሚያስበው ሰው ቁጥር አንፃር በወር ከ10 ብር እስከ 3,000 ብር የሚደርሱ የአባልነት ደረጃዎች ተመዝግቦ የደጋፊነት የደጋፊነት ግዴታውን እየተወጣ የሚገኘው ደጋፊ ቁጥር እጅግ በጣም አነስተኛ በመሆኑ ከፍተኛ ቁጭት የሚሰማን እንደመሆኑ ማኅበራችን በኮሮና ምክንያት በየተቋማት የአባልነት ምዝገባ ለማከናወን የተያዘው እቅድ የተራዘመ መሆኑ አንደተጠበቀ ሆኖ አሰራሩ ቀልጣፋ ለማድረግ ደጋፊዎች ባሉበት ሀገር በሚቀርባቸው የዳሽን እና የንግድ ባንኮች በሒሳብ ቁጥራችን የአባልነት መዋጮ ገቢ ማድረግ የ፣ ፎቶ በማህበራዊ ሚዲያ መልዕክት መቀባበያዎች ልከው አባል የሚሆኑበትን እንዲሁም በአካል በቢሮዎቻችን ቀርበው ፈጣን ምዝገባ ማድረግ የሚችሉበትን ሰርዓት አሻሽሎ ያቀረበ ሲሆን በቀጣይ ደግሞ ደጋፊ ነኝ ስንል በተግባር መደገፍ እንደሆነ የግንዛቤ ለውጥ በሚፈጠሩ ሥራዎች ላይ አትኩረን እንሰራለን።

አዲስ አበባ ካለው የደጋፊ ማኅበር ጋር አለመናበብ አለመስማማት እንዳለ ይነገራል። ያንን ለማጥራት ምን አስባችኋል?

የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ማኅበር አንድ ህጋዊ መብት የተሰጠው ማኅበር ሲሆን በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት ቅርንጫፍ ደጋፊ ማኅበር ያቋቁማል፣ ይመራል፣ ይዘጋል። ይህን መሰረት በማድረግ በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት አዲስ አበባ እና አቅራቢያው የሚገኘውን ደጋፊዎች አስተባብሮ የሚመራ ንዑስ ስራ አስፈፃሚ አስመርጠን ቅርንጫፉ የሚመራበት ግልፅ እና ተጠያቂነት ያለው የፋይናንስ አሰራርን ዘርግተናል። ይሁንና ሥራ አስፈፃሚዉ ይህን አሰራር የሚጥስ አሰራርን የመከተል ዝንባሌ ስለመረጠ አዲስ አበባ የሚገኙ ደጋፊዎችን በስብሰባ ጠርተን የውስጥ ጉዳዮችን ተወያይተን የማስተካከያ እርምጃ እስክንወስድ ስራ አስፈፃሚ ብቻ ለጊዜው አግደናል። እስከዚያ ግን ተቋም እንደመሆኑ ቢሯችን በሽያጭ ፅህፈት ሰራተኛችን አማካኝነት ክፍት ሆኖ የሽያጭ እና የአባልነት ምዝገባ እየተከናወነ ይገኛል።

ክለቡ ላይ የትጥቅ ችግር ባይኖርም የማሊያ ጥራት በደጋፊዎች ላይ ይነሳል። በርካታ ደጋፊዎች ደረጃውን የጠበቀ ማልያ በተለያዩ ዲዛይኖች እንዲመጣላቸው ይጠይቃሉ። ያንን ለማድረግ ምን እየሰራችሁ ነው?

ማሊያ ከዚህ በኋላ የሚያስመጣውና የሚያስመርተው ክለቡ ነው። እኛ በአሁኑ ሰዓት ከ6,000 በላይ ማልያዎች ዳሽን ቢራ በስፖንሰርነት ከቻይና አስመጥቶ ለደጋፊው ያቀረባቸው ማልያዎች ያሉን ሲሆን ይህም በሽያጭ ላይ ይገኛል። የአዲስ ማልያ ዲዛይን በደጋፊው ብቻ ሳይሆን በስፖርት ክለቡም አብሮ የሚቀይረው በመሆኑ በቀጣይ በዲዛይን ለውጥ የሚሻሻልበት ሁኔታ ላይ ጥናት ተደርጎ እንዲሰራ እንሰራለን ።

በስታዲየም ፀጥታ ያሳኩት ስኬት ለማስቀጠል ምን አይነት ስራዎች ለመስራት አስባችኃል ?

ስታዲየም ፀጥታ ማስከበር እና የክለቡን ጥቅም ማስከበር ስራ በንዑስ ኮሚቴ በአዲስ አደራጅተናል፤ ጥሩ ውጤት የመጣውም ደጋፊዎችን ተባባሪነት በልጆቻችን የአገልጋይነት መንፈስ በመገንባት ነው። ይህንንም ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የስልጠናና ድጋፍ ሥራችንን እንቀጥላለን። ለዚህ በእጅጉ አከብራቸዋለሁ፤ ይህንን በሌሎች ንዑሳን ኮሚቴዎችም ማስቀጠል ይኖርብናል ።

ፋሲል ከነማ በሜዳው በሚያደርገው ጨዋታ ላይ በርካታ ደጋፊዎች ይመለሳሉ። በርካቶች ቆመው ነው የሚመለከቱት። ደጋፊ ከዚህ ጋር በተያያዘ የራሱን ድርሻ ለመወጣት ምን እየተሰራ ነው ?

ሜዳ በደጋፊ ማኅበሩ ወይም በክለቡ አቅም የሚገነባ አይደለም። ይህን የከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲያግዘን እኛም ክለቡም የራሱ ካምፕና መለማመጃ ሜዳ እንዲኖረው እቅድ ተይዞ እቅዱ ወደ መሬት የሚወርድበት ዓመት ከፊታችን እየጠበቅን ነው። ደረጃ በደረጃ ከተማው የታቀደው ስታዲየም እቅድ በተግባር እንዲተገበር እንጠይቃለን፤ እናግዛለን ።

ደጋፊ ማኅበሩ በክለቡ ቦርድ አንድ መቀመጫ አለው። ወደፊት ክለቡን የደጋፊዎች የማድረግ እቅድ ነው ያላችሁ ?

ደጋፊ ማኅበሩ በክለቡ ጉዳይ ላይ ንቁና ባለድርሻም እንደመሆኑ በቦርድ ያው ውክልና አንድ ወንበር በቂ ነው ብለን አናምንም። ስለዚህ በቅርቡ ሁለት መቀመጫ እንዲኖረን እየሰራን ነው ተግባራዊ ይሆናል ብለን እናምናለን ።

ክለቡ ላይ በደል ሲደርስ ከክለቡ በተጨማሪ ደጋፊ ማኅበሩም ደብዳቤ ይፅፋል። ይህ የክለቡ አሰራር ላይ ተፃዕኖ አይኖረውም ?

ደጋፊ ማኅበሩ ለፌደሬሽን ደብዳቤ ፅፎም አያውቅም። ለፌዴሬሽን የክለቡን ጥያቄ ለመጠየቅ የሚያስችል ችሎታ እና ውክልና እንደሌለውም ጠንቅቀን እናውቃለን። ደጋፊውን የሚመለከት ጉዳይ ከሆን ግን የማንጠይቅበት ምክኒያት አይኖርም ።

ክለቡ የከነማ ክለብ ከመሆኑ አንፃር የከተማው ታዳጊዎች ላይ እንዲሁም ዋናው ቡድን ላሉ የከተማዋ ተዋላጅ ተጫዋቾች ትኩረት ያለመስጠት ችግር አለ ይሰማል። ከዚህ አንፃር የበኩላችሁን አዎንታዊ ጫና ለመፍጠር ትጥራላችሁ?

በባለፈው የውድድር ዘመን በዋናው ቡድን ውስጥ ባልሳሳት 7 ወይም 8 የከተማችን ተጫዋቾች ተካተው አገልገለዋል። ለዋንጫ በሚጫወት ቡድን ውስጥ እንደመሆናችን በቦታቸው ከሌላ የሀገራችን አልያም ውጭ ሀገራት ተጫዋቾች ጋር ተፎካክረው በቋሚነት ተመራጭ የመሆኑትን መምረጡ የኮችንግ ስታፍ ሙያዊ ስልጣን ነው። በቋሚነት የተመረጡ እንዳሉ በተጠባባቂነት ያለፉትም ነበሩ። በቀጣይ በተለይ ታዳጊዎች ላይ እድል የሚያገኙበት ሁኔታ ለማመቻቸት በቦርድ እና በአሰልጣኙ መካከል ውይይት ተደርጎ በተለይም የውጭ ዜጎች ቁጥር በመቀነስ ለተስፈኛ ተጫዋቾች እንደ ብቃታቸው ጤነኛ ፉክክር ማድረግ የሚችሉበትን እድል የሚያሰፋ ሁኔታ እየተፈጠረ እንዳለ ይታየኛል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ