የሴቶች ገፅ | ቆይታ ከመስከረም ካንኮ ጋር…

በደደቢት እና አዳማ ከተማ ድንቅ ጊዜን ያሳለፈችውን መስከረም ካንኮን በሴቶች ገፅ አምዳችን እንግዳ አድርገናታል።

በመዲናችን አዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ በሚባል ሰፈር ተወልዳ ያደገችው መስከረም ኳስን እጅግ ትወድ እንደነበር እና መጫወትን ታዘወትር እንደነበር ታወሳለች። በተለይ በሰፈሯ ሽሮ ሜዳ በሚገኙ የኳስ ሜዳዎች ላይ ውሎዋን ታደርግ እንደነበር አስታውሳ ትናገራለች። የቀለም ትምህርቷን እየገፋችም በየዓመቱ የሚደረግ የትምህርት ቤት ውድድሮች ላይ ተሳትፎ በማድረግ ገና ከ5ኛ ክፍል ሳትዘል የብዙዎችን ቀልብ መግዛት ጀመረች። ቁስቋም ጣይቱ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ወክላ ዓመታዊ ውድድሩ ላይ እየተሳተፈችም በሰፈሯ በምትገኝ አንድ እንስት ጠቋሚነት አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛውን አግኝታ የእግርኳስ ህይወቷን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር መጣር ቀጠለች። በጊዜውም አሰልጣኙ በተጫዋቿ ብቃት ተደምሞ በዋና ቡድን ከሚያሰለጥነው የየካ ክፍለ ከተማ ክለብ በታች የሚገኘውን የሁለተኛ ቡድንን (B) እንድትቀላቀል አደረገ። በዛም ክለብ ለጥቂት ጊዜያት እድገቶችን ካሳየች በኋላ አሰልጣኙን ተከትላ ወደ ሴንትራል የጤና ኮሌጅ ክለብ ጉዞዋን አደረገች። በተመሳሳይ በዚህም ክለብ በሁለተኛ ቡድን ውስጥ ታቅፋ ለጥቂት ወራት ከቆየች በኋላ ወደ ዋናው ቡድን አድጋ ግልጋሎትን መስጠት ጀመረች። ከዛም ወደ ፔፕሲ እና ደደቢት በማምራት ጥሩ ጊዜያትን ካሳለፈች በኋላ መዳረሻዋን አዳማ ከተማ አድርጋለች።

ለመጀመረያ ጊዜ በአሰልጣኝ አብርሃም ተክለሃይማኖት አማካኝነት ሃገሯን እንድታገለግል ጥሪ የቀረበላት ተጫዋቿ በመጀመሪያው ምርጫ የመጫወትን ዕድል ሳታገኝ ለልምድ ልውውጥ ብቻ ስብስቡን ተቀላቅላ ተመልሳለች። ከዛም አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የብሔራዊ ቡድን የአሰልጣኝነት መንበሩን ሲረከብ ተጫዋቿን ዳግም ወደ ስብስቡ ጠርቶ የመሰለፍ እድል ሰጥቷት ሃገሯን ማገልገል ጀመረቸ። ከዛም በቋሚነት የብሄራዊ ቡድኑ አባል ሆና በተለያዩ ጊዜያት ጨዋታዎችን አድርጋለች።

በሴንትራል፣ ፔፕሲ፣ ደደቢት እና አዳማ የእግርኳስ ህይወቷን ያሳለፈችው መስከረም ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገችውን አጭር ቆይታ እንደሚከተለው አዘጋጅተነዋል።

የእግርኳስ አርዓያሽ ማናት?

እንዳልኩህ ሽሮ ሜዳ አካባቢ ስለሆነ ተወልጄ ያደኩት በዚሁ አካባቢ የሚገኙ ተጫዋቾችን እንደ አርኣያ እመለከት ነበር። በተለይ ራሄል ደገፉ ለእኔ ጥሩ አርዓያዬ ነበረች። ረጋ ያለች ምርጥ ተከላካይ ስለነበረች በጣም አደንቃት ነበር።

ሽሮ ሜዳ አካባቢ ተወልደሽ እንዳደግሽ አጫውተሽናል። ቦታው ደግሞ በጥበብ ሥራ የታወቀ አካባቢ ነው። ከዚህ የጥበብ ሥራ ጋር እድገትሽ ግንኙነት ይኖረው ይሆን?

እንዳልከው ሽሮሜዳ አካባቢ የጥበብ ሥራ የታወቀ ነው። እኔም ይህንን እሠራ ነበር። ልጅ እያለሁ ሦስት ነገሮችን ጎን ለጎን አስኬድ ነበር። ትምህርት፣ የሸማ ሥራ እና እግርኳስ። እንዳለወከው የሸማ ሥራንም ለተወሰነ ጊዜ እሰራ ነበር። እንደውም ደደቢት ደሞዝ መክፈል ሲጀምር ነው ያቆምኩት እንጂ ከዛ በፊት እሰራ ነበር። በተለይ በሳምንት ሦስት ቀን ልምምድ በምንሰራበት ጊዜ በሌሎቹ ቀናት ከትምህርት መልስ ሥራዬ እሱ ነበር።

የእግርኳስ ውድድሮች በኮቪድ-19 ምክንያት ከተቋረጠ በኋላ መስከረም ጊዜዋን በምን እያሳለፈች ነው?

አሁን ላይ ካደኩበት ሰፈር ትንሽ ራቅ ብያለሁ። ግን ባለሁበት ቦታ ላይ ሁል ጊዜ እንቅስቃሴ አደርጋለሁ። በተለይ ጠዋት ጠዋት ሰፈር ካሉ ልጆች ጋር ስፖርት እንሰራለን። ከዛ በጥሩ ሁኔታ እረፍት አደርጋለሁ። ከዚህ ውጪ በግሌ የምሰራው ሌላ ስራ አለ። እና ትርፍ ጊዜ ሲኖረኝ እዚህ ስራ ላይ ራሴን በመጥመድ ጊዜዬን አሳልፋለሁ።

በግልሽ ጥሩ ጊዜ ያሳለፍሽበት ዓመት መቼ ነው?

በአንፃራዊነት ጥሩ ጊዜ አሳልፌያለሁ የምለው ደደቢት እያለው የነበረው ቆይታዬን ነው። ረጅም ዓመትም እዛ ስላሳለፍኩ ጥሩ ጊዜያት ነበሩኝ። እርግጥ በቆይታዬ ስኬታማም ሆነ አሳዛኝ ጊዜያት ነበሩ። በተለይ ባንክን በልጠን ዋንጫ ያነሳንባቸው ዓመታት ለእኔ ድንቅ ነበሩ።

መስከረም እግርኳስ ተጫዋች ባትሆን በምን ሙያ እናገኛት ነበር?

እግርኳስ ተጫዋች ባልሆን ነጋዴ የምሆን ይመስለኛል። በቀጣይ ራሱ እግርኳሱን ሳቆም ወደ ንግዱ ዓለም እንደምቀላቀል አስባለሁ። ደግሞም አይቀርም።

አብሬያት ተጣምሬ መጫወት እሻለው የምትያት ተጫዋች አለች?

ከብዙሀን እንዳለ ጋር ተጣምሬ ብጫወት እጅግ ደስ ይለኛል። በእኔ ቦታም ስለሆነ የምትጫወተው ብንጣመር ደስ ይለኛል። ከምንም በላይ እርጋታዋ እና ብስለቷ በጣም ድንቅ ነው።

በተቃራኒ ስትገጥሚያት የምትከብድሽ ተጫዋችስ ትኖር ይሆን?

ኧረ በጭራሽ። እስካሁን የሚከብደኝ ተጫዋች አላገኘሁም።

በዚህ ሰዓት ከሚገኙ የሃገራችን ተጫዋቾች ያንቺ ምርጥ ተጫዋች ማነች?

አሁን ላይ የእኔ ምርጧ ተጫዋች ብርቱካን ገብረክርስቶስ ነች። ቡርቴ ሜዳ ላይ በጣም ድንቅ ነች። እርግጥ ከሜዳም ውጪ ያላት ስብዕና በጣም ግሩም ነው። ከእነዚህ ሁለት ነገሮች መነሻነቴ ቡርቴን ምርጥ አድርጌ እመርጣለሁ።

ከአሰልጣኞችስ?

ሁለት አሰልጣኞችን ብመርጥ ደስ ይለኛል። አንደኛው እና ምንም ድርድር የሌለው ብርሃኑ ግዛው ነው። ሁለተኛ ደግሞ ሰላም ዘርዓይ ናት። እነዚህ ሁለት አሰልጣኞች በዚህ ሰዓት የሃገራችን ምርጦቹ አሰልጣኞች ናቸው።

በእግርኳስ በጣም የተደሰትሽበት አጋጣሚን እስኪ አስታውሺን?

ዓምና አዳማ እያለሁ ቡድናችን ዋንጫ ሲያነሳ በጣም ተደስቼ ነበር። ቡድኑም አዲስ ቡድን ነበር፤ ግን ከባድ ጊዜዎችን አሳልፈን ዋንጫ ስናነሳ በጣም ተደስቻለሁ።

በተቃራኒ የተከፋሽበትስ ጊዜ ይኖር ይሆን?

መከፋት እኮ ቀላል ነው። ያለቀስኩበት ጊዜ ሁሉ አለ። በተለይ ደደቢት እያለሁ አዳማ ላይ ከባንክ ጋር ስንጫወት ያለቀስኩትን ዕንባ ቤተሰብ ቢሞት እንኳን እንደዛ የማወጣው አይመስለኝም። በጨዋታው እስከ 90ኛው ደቂቃ 1-0 እየመራን 7 ተጨማሪ ደቂቃዎች ተጨመሩ። ከዛም በጭማሪ ደቂቃዎቹ አንድ ጎል ገብቶብን አቻ ተለያየን። በመለያ ምትም በባንክ ተሸነፍን። እና ይህ ጨዋታ መቼም ከአዕምሮዬ አይጠፋም።

ኳስ ተጫዋች ገጠመኝ አይጠፋውም መቼስ። እስኪ አንዱን አጫውቺኝ?

ልክ ነው ኳስ ተጫዋች ብዙ አይነት ገጠመኝ አለው። ግን በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ከሃገር ወጥተን የገጠመኝን ነገር ልንገርህ። ሲጀምር ከሃገር ስንወጣ ብዙ የሚያስቁ ነገሮች ይከሰታሉ። እና በጊዜውም አልጄሪያ ሄደን ስንጫወት ሜዳ ላይ ኳስ የእኛ ቡድን ተጫዋች ትይዛለች። ከዛ የዕለቷ ዳኛ ጥፋት ሰርተሻል ብላ ጨዋታውን ስታቆም ስሟን የማልነግርልክ የቡድን አጋራችን ‘ማርያምን አልነካኋትም። ማርያምን! ከፈለክሽ አራጋቢዋን ጠይቂያት። ማርያምን! ነይ ልማልልሽ’ እያለች ዳኛዋን በሩጫ ስትከተላት እኛ በሳቅ ወደቅን። እርግጥ ዳኛዋም እንግሊዝኛ አትችልም ነበር። ግን አሁን ላይ ስሟን የማልጠቅስልን ተጫዋች በአማርኛ እየማለች ውሳኔ ልታስቀይር የሞከረችው ነገር በጣም አስቆን ነበር።

በእግርኳሱ ውስጥ ከሚገኙ ግለሰቦች የቅርብ ጓደኛሽ ማነች/ው?

በእግርኳስ ውስጥ ካሉ ሰዎች እንደ እህት እና አማካሪ የማያት ብርቱካን ገብረክርስቶስ ነች። ቀድሜ እንዳልኩህ ቡርቴ ስብዕናዋም ጥሩ ስለሆነ እንደ ምርጥ ጓደኛዬ እና ሚስጥረኛዬ ነው የማያት።

እስኪ ስለ ግል ባህሪሽ አጫውቺኝ? ምን የተለየ የግል ባህሪ አለሽ?

የተለየ ባህሪ እንኳን የለኝም። ግን ቡድናችን ውስጥ ተጫዋች ነኝ። ዝምታ ብዙ አይመቸኝም። ቀልድ እና ጨዋታ አዘወትራለሁ።

የግል ህይወትሽ ምን ይመስላል?

ትዳር ውስጥ ልገባ መንገድ ላይ ነኝ። ሁሉ ነገር አልቋል። ሽማግሌም ተልኳል። ስለዚህ በአጭር ጊዜ እጠቃለላለሁ።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!