የዳኞች ገጽ | ብዙ የሚያልመው ተስፈኛ ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት

በቅርቡ የኢንተርናሽናልነት ባጁን አግኝቷል። ወደ ፊት በብዙ ነገሮች ከሚጠበቁ ዳኞች መካከልም ይመደባል። የዛሬው የዳኞች ገፅ እንግዳችን ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት ይባላል።

ከአዲስ አበባ በስተ ምዕራብ በኦሮሚያ ክልል 100 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው አዲስ ዓለም ከተማ ነው የተወለደው። በቀድሞ ፈረንሳዊው ድንቅ ተጫዋች ቴሪ ሄነሪ አድናቆት የጀመረው የእግርኳስ ቁርኝት ወደ ዳኝነት አድጎ በፍጥነት ነበር ከመምርያ አንድ ጀምሮ ፌደራል ዳኛ እስከመሆን ያደረሰው። ያለፉትን ስምንት ዓመታት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በረዳት ዳኝነት በጥሩ ብቃት ሲያገለግል አይተነዋል። የኬምስትሪ ምሩቁ ፋሲካ የኋላሸት በ2012 ጥር ወር ላይ ከብዙ ጥረት እና ልፋት በኃላ የኢንተርናሽናል ረዳት ዳኝነት ባጅን አግኝቷል። ሆኖም መጋቢት ወር ላይ የኮሮና ቫይረስ መጥቶ እስካሁን ሀገሩን በመወከል በዓለም ዓቀፍ መድረክ ውድድሮችን አይምራ እንጂ ወደ ፊት በተለያዩ ውድድሮች ላይ ተሳትፎ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ፈጣን እና ንቁ ዳኛ ሁሌም በኢንስትራክተሮች ዘንድ በሚሰጡ የሀገር ውስጥም ሆነ የካፍ ስልጠናዎች ላይ የሚያነሳቸው ነጥቦች (ጥያቄዎች) ዕይታው ምን ያህል ከፍ ያለ እንደሆነ የሚጠቁሙ ናቸው። በዛሬው የዳኞች ገፅ አምዳችን ብዙ ተስፋ ከፊቱ ከሚጠብቀው ፋሲካ የኋላሸት ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ጊዜ!

ከመጀመርያው ጥያቄዬ ልጀምር ትውልድ እና እድገትህ የት ነው?

በምዕራብ ሸዋ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ አዲስ ዓለም ከተማ ነው ትውልድ እና እድገቴ። አሁንም በሥራ ምክንያት ካልሆነ በቀር ቤተሰብ መስርቼ ኑሮዬን እየኖርኩ የምገኘው በዚሁ በአዲስ ዓለም ከተማ ነው።

መቼም ወደ ዳኝነት ለመግባት የተለያዩ ምክንያቶች ይኖራሉ። ለአንተ ወደ ዳኝነት እንድትገባ ገፊ ምክንያትህ ምን ነበር ?

ከእንግሊዝ ፕሪምየር የአርሰናል ደጋፊ ነኝ። ይህም ብቻ ሳይሆን የፈረሳዊው አጥቂ የቴሪ ሄነሪ ጫፍ የነካ የልብ አድናቂ ነኝ። አርሰናል በነበረበት ወቅት ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከተከላካዮች መሐል ሾልኮ ሲወጣ ረዳት ዳኞች በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጭ ያልሆነ አቋቋምን እያነሱ ጎል የሚያስቆጥርበትን ዕድል ሲያጨናግፉበት ሳይ በጣም ያናድዱኝ ነበር። ይህ ከጨዋታ ውጭ አቋቋም (offside) እና ከጨዋታ ውጭ ያልሆነ አቋቋም (onside) ምንድነው? ማወቅ እና መማር አለብኝ በሚል ነው የዳኝነት ትምህርት በመውሰድ ዳኛ ሆኜ የቀረሁት።

በጣም አስገራሚና ብዙም ባልተለመደ ምክንያት ነው ወደ ዳኝነት ህይወት የገባኸው? ታዲያ በመቀጠል ምን አደረክ?

አዎ! ዳኛ ለመሆን ያነሳሳኝ ምክንያት ብዙዎችን ስነግራቸው ይገርማቸዋል። ያው ከጨዋታ ውጭ በሆነ አቋቋም ብዙ ጊዜ ጎል የሆነ ኳስ ሲሻር ታያለህ፣ ደግሞ ጎል መሆን የማይገባው ኳስ ሲገባ ትመለከታለህ። እነዚህ ነገሮች ምንድ ናቸው። በአብዛኛው ወይ በስህተት አልያም ባለው ሳይንሳዊ አተገባበር ክፍተት ምክንያት በቀላሉ ጎሎች ይቆጠራሉ፣ ይሻራሉ። ስለዚህ ይህን ለማየት ስሞክር ነው ዳኛ ለመሆን የበቃሁት።

ታዲያ እንዴት ኮርሱን ለመውሰድ እድሉ ተመቻቸልህ?

በአጋጣሚ ሆኖ በ1998 ኢንስትራክተር መኮንን ለገሰ የሚባሉ በጣም ታዋቂ እና በዳኝነት ዘመናቸውም ጎበዝ የሆኑ ሰው ወደ ከተማችን መጥተው የመጀመርያውን መምሪያ ሁለት ኮርስ ይሰጣሉ። እውነት ነው የምልህ አሁን ላይ ካሉ ኢንስትራክተሮች ባልተናነሰ መልኩ በጣም ጎበዝ እና እግርኳስን ከነ ታሪኩ አብራርተው የሚያስተምሩ ጠንካራ መምህር ነበሩ። አሁን በህይወት የሉም። ነፍሳቸውን ይማር። በጊዜው ከነበሩት የስልጠናው ተሳታፊዎች ውስጥ አብዝቼ እጠይቃቸው ነበር። በእድሜ ገና ልጅ ነኝ። በዛ ላይ በጣም ቀጫጫ ነበርኩኝ። በፍላጎት ነበር የማነሳውን ነገር አብራርተው ያስተማሩኝ። እንዳውም አንተ ወደፊት ትልቅ ዳኛ ትሆናለህ። እንደነ ፅጌ፣ ሊዲያ፣ ኃይለመልአክ ብለወ በጣም ብዙ ዳኞችን ስም ጠሩልኝ። እኔ ደግሞ በጊዜው እነዚህን ዳኞች አላቃቸውም። ዳኝነትን እንድወደው በውስጤ ብዙ ነገር ጫሩብኝ የበለጠ ጉጉት እንዲኖርብኝ አድርገው አስተማሩኝ። ያው እኔም ከጨዋታ ውጪ የሚለውን ስለምወደው ረዳት ዳኛ በመሆን መማር ጀመርኩ።

ቀጣይ ኮርሶችንስ እንዴት ወሰድክ?

በቀጣይ መምርያ አንድ እና የፌደራል ኮርስ በተከታታይ ዓመት ወሰድኩ። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ፌደራል ዳኛ ሆኜ ሳልሰራበት የዩኒቨርስቲ ውጤት መጥቶ አምቦ ዩኒቨርስቲ ገባሁ። አራት ዓመት ውስጥ በትልቅ ውድድሮች ከሰፖርቱ ዓለም በዳኝነት በመግባት (ሳልጠቀም) ቀረው።

እድገትህ በጣም ፈጣን ነው። ብዙ ጊዜ መምርያ ኮርሶችን ወስደው ፌደራል ዳኛ ለመሆን ቢያንስ አምስት ዓመት የሚቆዩ አሉ። ያንተ እንዲህ በሁለት ዓመት ውስጥ ፈጥኖ ፌዴራል የሆንክበት ምክንያት ምንድነው?

አዎ በጣም አጭር ነው። የመጀመርያውን መምርያ ኮርሶችን ወስጄ እዛው ባለሁበት አካባቢ እስከ ዞን ድረስ በዋናም፣ በረዳትም እሰራ ነበር። 2000 ላይ ፌደራል ዳኝነት ኮርስ ወስጃለው። ያኔ ብዙም ጊዜ ሳይኖረው በፍጥነት ለመውሰድ ምክንያት የሆነኝ ከተማችን ላይ በስፋት የዳኝነት ኮርስ ይሰጥ ስለነበር ነው። በወቅቱ የከተማው ስፖርት ኮሚሽን ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ቱሉ የሚባል በጣም ጎበዝ ሰው ነበር። እና እርሱ ፌደራል እንድሆን በጣም ይፈልግ ነበር። ይልቁንም አንተ ኢንተርናሽናል የመሆን እድሉ አለህ በሚል ተከታታይ ስልጠናዎችን እንድወስድ አድርጎኝ ነበር። በሁለቱም የመምርያ ኮርሶች ላይ ከፍተኛ ነጥብ አግኝቼ ስለጨረስኩ ይህ ልጅ ካለው የመቀበል ችሎታው አንፃር እንዲሁም ወደ ዩኒቨርስቲ ሲሄድ ስልጠናውን ስለማያገኘው በሚል የፌደራል ዳኝነት ኮርሱን አስፈቅዶልኝ ነው የወሰድኩት። እውነት ነው በተለየ ሁኔታ ነው እኔ እንድማር የተደረገው። አሁን የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት መኮንን አስረስ ናቸው ግን የፌደራል ዳኝነት ኮርስን የሰጡኝ።

በዩኒቨርስቲ በቆየህበት አራት ዓመት ውስጥ የነበረህ የዳኝነት ህይወት እንዴት ነው?

ዩኒቨርስቲ ውስጥ የተለያዩ የውስጥ ውድድሮች ስለነበሩ እና ብዙውን ጊዜ የዳኝነት ኮርስ የወሰደ ደኛ ስላልነበረ እኔ በረዳትም በዋና ዳኝነት እሰራ ነበር። በዛን ጊዜ በምዕራብ ሸዋ አንቦ ላይ በጣም ጠንካራ የሆነ አጠቃላይ የዞን ውድድሮች ላይ በጣም እሳተፍ ነበር። በአጠቃላይ ዳኛ ለመሆን ካለኝ ከፍተኛ ፍላጎት እና ፍቅር አኳያ ነው ይህ የሆነው። በፍጥነት ወደዚህ ሙያ ገብቼ ውጤታማ ልሆን የቻልኩትም በዚህ ምክንያት ነው።

ከዩኒቨርስቲ በኋላ የነበረህ የዳኝነት ህይወት ምን ይመስላል?

በዩኒቨርስቲ ውድድር በነበረኝ የላቀ ተሳትፎ 2002 ላይ ተማሪ ሆኜ በአጋጣሚ የኦሮሚያ ሊግ የሚባል ሃያ ክለቦች የሚሳተፉበት በጣም ጠንካራ ውድድር ባሌ ከተማ ላይ ይካሄድ ነበር። እዛ ላይ የመሳተፉን እድል አገኘው። ይህ ውድድር ወደ ዳኝነቱ የበለጠ እንድገባ፣ ወደ ላይ እንዳድግ መነሻ የሆነኝ እንዲሁም የዳኝነት ህይወቴን ምዕራፍ የቀየረ፣ ትልቅ ልምድ ያገኘሁበት፣ በክልሉ ካሉ የዳኞች ኮሚቴ ጋር ያስተዋወቀኝ በጣም ወሳኝ ታሪኬ ነው። የፌደራል ኮርሱን ወሰድኩኝ እንጂ ባጁን አላገኘሁም ነበር። አጋጣሚ ሆኖ በመላው ኢትዮጵያ ኦሮሚያን የሚወክል ቡድን የሚታወቅበት ወሳኝ ጨዋታ ላይ በዋናነት ተመድቦ የነበረው ዳኛ ታሟል። ልምድ ያለው ሰው ያስፈልግ ነበር። ሲታጣ እኔ ገብቼ በዋና ዳኝነት እድሰራ ተወሰነ። ብዙ ልምዱ የለኝም። ጨዋታው ደግሞ ከፍተኛ ልምድ የሚጠይቅ ነው። ወደ ሜዳ ገባው የኦሮሚያ የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩት በወቅቱ አቶ ለማ ጉተማ ነበሩ። አሁንም በዚህ ቦታ ላይ በኃላፊነት ይገኛሉ። እንዴት ነው ይሄ ልጅ ጨዋታውን ይዞልን ይወጣ ይሆን? የሚል ፍራቻ ነበራቸው። እንደ እድል ሆኖ ሮቤ ወንጂን አሸነፈ። እኔም የተሰጠኝን እድል በጥሩ ሆኔታ ተጠቀምኩኝ። ከዚህ በኃላ ይህ ዳኛ ማነው? እድል እንስጠው አሉ። በዚሁ ዓመት ሻሸመኔ ላይ መላው ሃገር አቀፍ የፕሮጀክት ውድድር እንዳጫውት እድሉ ተሰጠኝ። በኋላም የአካል ብቃት ፈተና ወስጄ በ2003 በወቅቱ ብሔራዊ ሊግ የሚባለውን ውድድር እየተዟዟርኩ በረዳት ዳኝነት ማጫወት ጀመርኩ። የመጀመርያም ጨዋታዬም ወልድያ ላይ ወልድያ ከአማራ ፖሊስ ያደረጉት ነበር።

በዳኝነቱ ሙያ በብሔራዊ ሊግ ውድድር በማጫወት ምን ያህል ቆየህ?

አንድ አጋጣሚ ልንገርህ በ2003 በአበበ ቢቃላ ስታድየም ላይ ፌደራል ፖሊስ ከሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሃን እያጫወትኩኝ የጨዋታው ኮሚሽነር ማስተር (ኢንስትራክተር) ተሾመ ነበሩ። በአንድ አጋጣሚ ለዳኛው በማይታይ መልኩ ለኔ አቋቋም ቅርብ የሆነ ቦታ ላይ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ኳስ በእጅ ሲነካ በመሐል ዳኝነት የነበረው መኮንን ይፍሩ ይባላል። እርሱን ረድቼ ፍፁም ቅጣት ምት እንዲሰጥ አደረኩኝ። በጊዜው በጣም ተጮኸ። እኔ ደግሞ ህግና ህግን ነው የተገበርኩት። በጊዜው ደግሞ አልተለመደም ፔናልቲ መስጠት። እረፍት ላይ ወደ መልበሻ ክፍል ስንገባ ኮሚሽነር መጥተው ‘ማነህ? ከየት ነህ?’ ብለው ስልክ ቁጥሬን ጠየቁኝ። ከዛም በጣም አድንቀው ረዳት ዳኝነት ላይ ያለህ ነገር በጣም ጥሩ ነው። ‘አሁን አንተን በቀጥታ ፕሪምየር ሊግ አስመድብሀለው’ አሉኝ። ኧረ እኔ ለዚህ ገና አልደረስኩም ገና ብዙ መስራት ይጠበቅብኛል አልኳቸው። ከዛ በኃላ እኔን ለማየት የተለያዩ ክልሎች ይመጣሉ፣ ስልክ እየደወሉ ‘እንዴት ነህ እየሰራህ ነው። ታነባለህ በርታ።’ እያሉ ይመክሩኝ ነበር። በዳኝነት ህይወቴ በጣም ተፅዕኖ ከፈጠሩብኝ ሰዎች መካል አቶ ለማ ጉተማ እና ኢንስትራክተር ተሾመ ዋናዎቹ ናቸው። በእነርሱ ጥረት እና እገዛ ለአንድ ዓመት ብቻ ሳገለግል ቆየሁ።

ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዴት ማደግ ቻልክ ታዲያ ?

በ2003 መጨረሻ ላይ ድሬዳዋ ላይ የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር ይካሄድ ነበር። ለዚህ ውድድር ተመርጬ ሄድኩ። አሁን ላይ ኢንተርናሽናል የሆኑት ለሚ ንጉሴ፣ ቴዎድሮስ ምትኩ፣ በላይ ታደሰ፣ ተካልኝ ለማ፣ አሸብር ሰቦቃ እና ሌሎችም ዳኞች ወደ ፕሪምየር ሊግ የወጣንበት እና እኔ በግሌ ጥሩ ልምድ ያገኘሁበት ውድድር ነበር። የሚገርምህ በአንድ አጋጣሚ በጣም የምወደው እና የማከብረው ኃይለመላክ ተሰማ አንድ ጨዋታ አይቶ፣ ተደስቶ ሎውስ ኦፍ ዘ ጌም 2010/11 የሚል መፅሐፍ የእንግሊዘኛ እትም ሸልሞኛል። ይህች ሽልማት ለእኔ የበለጠ እንድሰራ ያነሳሳችኝ ነበረች። በዚህ አጋጣሚ ጋሽ ኃይለመላአክን አመሰግናለው። በዛኑ ዓመት ከቀናት በኃላ በድጋሚ ከ17 ዓመት በታች ሀዋሳ ላይ የፕሮጀክት ምዘና ውድድር ሰርቼ ከ2004 ጀምሮ ወደ ፕሪምየር ሊጉ አድጌ ማጫወት ጀመርኩ። የመጀመርያ ጨዋታዬም አዲስ አበባ ስታዲየም ንግድ ባንክ ከ መብራት ኃይል ያደረጉት እና የለሚ ንጉሴ ረዳት ሆኜ የመራሁት ነው። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ባለሁበት ጊዜ ድረስ በውጤታማነት እና በቋሚነት እየሰራው እገኛለው። ቅድም እንደነገርኩህ ከኮርስ አወሳሰዴ ጀምሮ ፕሪምየር ሊግ ማጫወት እስከ ጀመርኩበት ጊዜ ድረስ ያለው ጊዜ በጣም አጭር ነው። ብሔራዊ ሊግ አንድ ዓመት ብቻ ነው የሰራሁት። ረጅሙን የዳኝነት ህይወቴን እየመራው የምገኘው ፕሪምየር ሊግ በማጫወት ነው።

ኢንተርናሽናል ከመሆንህ አስቀድሞ በመሐል የወሰድካቸው ኮርሶች አሉ?

ብዙ ስልጠናዎችን ወስጃለው። ለምሳሌ 2006 ፊፋ ኤሜ ኤሊት ኮርስ ወስጃለው። በዚህ ስልጠና ላይ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ጨርሻለው። በተመሳሳይ በ2008 ላይ በነበረው ኮርስ ከክፍል ውስጥ ከፍተኛ ነጥብ በማምጣት ኳስ ተሸልሚያለው። ከ32 የአፍሪካ ሀገራት ለመጡ ዳኞች የተሰጠ የፊፋ ኮርስ ቦትሱዋና ላይ ከቴዎድሮስ ምትኩ ጋር በመሄድ ተሳትፌለው። ከዛን ጊዜ ጀምሮ በሚሰጡ ስልጣናዎች እራሴን እያሳደኩኝ እዚህ ደረጃ ደርሻለው።

ኢንተርናሽናል ዳኛ መቼ ሆንክ?

በ2012 ጥር ላይ ነው። ጥር ይሄን ባጅ ከወሰድኩ በኃላ የኮቪድ ወረርሽኝ መጥቶ ውድድሮች ተቋርጠዋል። በዚህ ምክንያት ከሀገሬ ውጭ ወጥቼ የማጫወት እድሉን አላገኘሁም።

በዳኝነት ዘመኔ ምንድነው ጥንካሬዬ ትላለህ?

ረዳት ዳኝነት በጣም ደስ የሚል ሙያ ነው። ጠንካራ ስብዕና፣ ፍጥነትን እና ንፁህ ህሊናን የሚጠይቅ እንዲሁም ሁሌም በስነ ልቦናው እና በአይምሮህን መዘጋጀት የሚገባህ ሙያ ነው። በተጨማሪም በንድፈ ሀሰብ ሁሌ ማንበበ የሚጠይቅ የምወደው ሙያ ነው። በኦፍሳይድ ምክንያት(በኔ ስህተተት) ማንም የለፋ እና የደከመ ቡድን መሸነፍ የለበትም የሚል አቋም አለኝ። እንደነገርኩሁ ኦፍሳይድ የሆነ ኳስ ይገባል፣ ኦፍሳይድ ያልሆነ ኳስ ይሻራል። በአብዛኛው በዓለም ቫር ከመጣ በኃላ ብዙ የተሻባሉ ነገሮች አሉ። እኛ ሀገር ስትመጣ ግን ብዙ የሚፈጠሩ ስህተቶች አሉ። እነዚህም ስህተቶች እኔ እንዳይሰሩ ጠንክሬ እየሰራው ነው። በኦፍሳይድ ጀመርኩ ይህው በከፍተኛ ፍላጎት እስካሁን በረዳት ዳኝነት እየሰራው እገኛለው። የኔ ጥንካሬ ሁልጊዜ እራሴን ዝግጁ አድርጌ ስለምጠብቅ ይሆናል።

እስካሁን ያገኘሀቸው የኮከብነት ሽልማቶች አሉ ?

በማጠቃለያ ውድድሮች ላይ ለምሳሌ በ2003 ድሬደዋ ላይ የክልል ክለቦች ሻምፒዮን ላይ የመዝጊያ ጨዋታ፣ እንደዚሁ በዚሁ ዓመት ከ17 ዓመት በታች የፕሮጀክት ውድድር መዝጊያውን ጨዋታ፣ 2006 እና 2010 ላይ የፕሪሚየር ሊጉ መዝጊያ ጨዋታ ላይ በመሳተፍ ሜዳልያ ተሸላሚ ሆኛለው። 2006 ላይ በደደቢት እና ቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል የተደረገውን የጥሎ ማለፍ የፍፃሜ ጨዋታን ሠርቻለው። እንደ አጠቃላይ ግን ኮርሶች ላይ በተደጋጋሚ ጥሩ ተሳትፎ በማድረግ በተለይ በ2008 ከፊፋ በመጣው ስቲቭ በሚባል ኢኒስትራክተር የተበረከተልኝ የኳስ ሸልማት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

እስካሁን እኔ በግሌ ካየኋቸው ረዳት ዳኞች መካከል በየጊዜው ራስህን እያሻሻልክ ኢንተርናሽናል ዳኛ ለመሆን የበቃህ ነህ። ከዚህ በኃላ ሀገርህን በዓለም አቀፍ መድረክ ለመወከል ምን ታቅዳለህ ?

በዓለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያን ዳኞች ያለን ስም እና ክብር በጣም ከፍተኛ ነው። ለስልጠና ቦትስዋና በሄድኩበትም ይሄንን ማስተዋል ችያለው። ከፈጣሪ ጋር እንደነ በዓምላክ ተሰማ በጥሩ ሁኔታ የተለያዩ ጨዋታዎችን በማጫወት እና በተለያዩ ኮርሶች ላይ በመሳተፍ የላቀ ውጤት በማምጣት አሉ ከሚባሉ ኤሊት ዳኞች መካከል አንዱ መሆን እፈልጋለው። የመጀመርያው B ነው የሚባለው። ይሄን ኮርስ ለመውሰድ ፈጣሪ ረድቶኝ እዚህ ውስጥ መግባት እፈልጋለው። ሲቀጥለም A ኤሊት ኮርስ ውስጥ በመግባት የመጨረሻው ግቤ የዓለም ዋንጫን መምራት ነው። ለዚህም የሚያስችለኝን በየጊዜው ወቅታዊ የሆኑ ማኗሎችን በማየት የአካል ብቃት፣ ቴክኒካል የሆኑ ቪዲዮ ክሊፖችን እያየሁ ያለኝን እውቀት እንዲሁም የተሻሻሉ ህጎችን እያነበብኩ እራሴን ለማብቃት ጠንክሬ እየሰራው ነው። ፈጣሪ ረድቶን በኮሮና የተፈጠረው ክፍተት ተደፍኖ እንደ ከዚህ በፊት እንደነበሩት የሙያ አጋሮቼ እና የሙያ አባቶቼ ስኬታማ ለመሆን ነው እቅዴ።

እስካሁን ባለው የዳኝነት ዘመን የማትረሳው ገጠመኝ አለ ?

በ2005 ከብሔራዊ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ለመግባት በጣም ጠንካራ ጨዋታ ነበር። ውድድሩ ሰበታ እና አዲስ አበባ ነበር። አስታውሳለው መቂ ከ ወላይታ ጋር ሰበታ ላይ ነበር ጨዋታው ። እና ኃይለኛ ዝናብ እየዘነበ የጫማ ክሬ ይፈታብኛል። ጨማዬ ጠልፎ እንዳይጥለኝ በማለት ለማሰር ጎንበስ ብዬ ስነሳ በሚገርም ፍጥነት በወላይታ በኩል በመልሶ ማጥቃት ኳሱ ኦፍሳይድ ክልል ውስጥ ሆነ። አጥቂው ኳስ ተለቆ ሲሮጥ አየው። በጣም ተደናገጥኩኝ ያለኝ እድል መወስን ነው። አንድ የተፃፈ ህግ አለ ምን አልባት አሁን ላይ ይህ ህግ ተሻሽሏል ምን ይላል መሰለህ “ጥርጥር ውስጥ ካለህ ጨዋታውን ልቀቀው። አትያዘው ይላል” እናም በአጋጣሚ ሆኖ ኳሱን ለቅቄው ጎሉ ተቆጠረ። በጣም ወሳኝ ጨዋታ ነበር። በሆነው ነገር ከህሊናዬ ጋር በጣም ታገልኩኝ ኦፍ ሳይድ ነው አይደለም በማለት ከራሴ ጋር ተከራክሬ ባለሁበት ሰዓት እንዳጋጣሚ ጨዋታውን ይከታተሉ የነበሩ የዳኞች ኮሚቴ አባለት በወሰንኩት ውሳኔ አድንቀው። ‘ይህ ኮንፊደስህን የሚያሳይ ነው። እኛ ግን ትይዘዋለህ ብለን ነበር።’ በማለት በጥሩ ሁኔታ አበረታቱኝ። አስበው አንዳንዴ ዳኝነት ቅፅበታዊ ነው። ስህተት ብሰራ ኖሮ ምን አልባት አሁን የደረስኩበት ደረጃ ላልደርስ እችል ነበር። ለእኔ ይህ ልዮ አጋጣሚ ነው።

ሌላው በመጥፎ የማስታውሰው ገጠመኝ 2008 ጎንደር አፄፋሲል ስታዲየም ዳሽን ቢራ ከኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ለመዳኘት እኔ፣ ዘካርያስ ግርማ እና አስቻለው የሚባል ዳኞች ነበርን። ዳሽን ላለመውረድ የሚጫወትበት ወሳኝ ጨዋታ ነበር። በካታንጋ በኩል አስቻለው ትክክለኛ ውሳኔ ወስኖ ኦንሳይድ የሆነ ኳስ ይለቃል። በዚሁ አጋጣሚ በጣም ከማከብራቸው፣ ከማደንቃቸው ትልቅ ቦታ ከምሰጣቸው ረዳት ዳኞች መካከል አንዱ ነው። በተለቀቀው ኳስ ቡና ጎል ያገባል። በዚህ የተነሳ ለአስቻለው የተወረወረ ድንጋይ ዘካርያስ ጆሮ አካባቢ ተመቶ ጨዋታው ለተወሰነ ደቂቃ ተቋረጠ። በኋላ ጨዋታው ቀጥሎ ጨዋታውን ጨርሰን ስንወጣ የተፈጠረው ነገር በጣም አሳዛኝ ነው። በካታንጋ በኩል አጥር ጥሰው የገቡ የዳሽን ደጋፊዎች እላያችን ላይ ወጥተው ተረጋግጠን በሞት እና በህይወት መካከል የሆንበትነን አጋጣሚ ያሳዝናል። እግራችን ቢሰበር ሁሉ ዳኝነት ልናቆምእንዲሁም በህይወትም ላንኖር የምንችልበት የማረሳው ገጠመኝ ነው።

ከዳኝነት ውጭ በምን ሙያ ላይ ነው የምትገኘው?

የኬሚስትሪ ባለሙያ ነኝ። የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራሁ ነበር። በአጋጣሚ በዚህ በኬሚስትሪ ላብራቶሪ ምክንያት የሳይነስ (እስማቲክ) ነገር ስለጀመረኝ ይህን ሙያ አቁሜ በግሌ የንግድ ዓለም ውስጥ ገብቼ እየሰራሁ ነው። ከውጭ የተለያዮ አልባሳትን እና ጫማዎችን እያስመጣው የማከፋፈል ስራ እየሰራው እገኛለው።

የቤተሰብ ህይወትህስ ?

በኮቪድ ምክንያት ዘንድሮ ሠርግም ባይኖር የተወሰነ ፕሮግራም አድርጌ አግብቼ ቢታንያ ፋሲካ የምትባል የአንድ የሴት ልጅ አባት ሆኛለው።

በመጨረሻ

ዳኝነት ሙያን እጅግ በጣም የምወደው እና የማከብረው ሙያ ነው። ዳኝነት ትልቅ ስብዕና የሚጠይቅ፣ ፍፁም ንፁህ ህሊና የሚጠይቅ፣ ከፈጣሪ ጋር የሚያገናኝ የተከበረ ሙያ ነው። ሁሌም ሆኖ መገኘት የሚያስፈልገው ሙያ ነው። ከሰው ጋር በፍቅር መኖርን የሚጠይቅ ጠንካራ አዕምሮ የሚፈልግ ሙያ ውስጥ በመኖሬ በጣም ደስተኛ ነኝ። አመሰግናለው።



© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!