የ”3ኛው ተጫዋች መርሕ” ትግበራ እና ፋይዳ

አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ከተለያዩ ድረ-ገጾች ያገኛቸውን የእግርኳስ ታክቲክ ንድፈ-ሐሳቦችን የተመለከቱ ጥልቅ ትንተናዎች፣ የሥልጠና መመሪያዎች እና መጻህፍትን ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ በመተርጎም ሌሎች አሰልጣኞችና አንባቢን ይጠቅም ዘንድ ጥቅም ላይ ለማዋል ይሞክራል፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው ፅሁፍም አንዱ አካል ነው፡፡

ታክቲካዊ ኅልዮት

ጸሃፊ
– ቶቢያስ ኻን

ተርጓሚ
– ደስታ ታደሰ

ታክ-ታክ-ታክ-….. እነዚህ ተደጋጋሚ ቃላት የአንድ ቡድን ተጫዋቾች እርስ በእርሳቸው በፍጥነት የኳስ ቅብብል ሲከውኑ የሚሰማ ድምፅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የድምጹ ፍሰት ቀለል ካለ የኳስ ቅብብልም የላቀ አንድምታ ይኖረዋል፡፡ የቡድን ተጫዋቾች በጋራ ሆነው እንደ አንድ ሲንቀሳቀሱ የሚያስመለክት ምናብ ይከስትልናል፡፡ እግርኳሳዊ ጥበብ እንድናስብ ያደርገናል፡፡

ለእግርኳስ ተመልካቾች በጨዋታ ወቅት የሚፈጠሩ እነዚህ መሰል ቅብብሎች ከስንት-አንዴ የሚፈጠሩ ብርቅዬ ቅጽበቶች በመሆናቸው በቀላሉ ከአዕምሮ አይወጡም፤ ይልቁንም ለረጅም ጊዜ የሚታወሱ ትዝታዎች ይሆናሉ፡፡ መለስ ብለን ታሪክን የኋሊት ብናወሳ የ1970ዎቹ የሆላንድ ብሄራዊ ቡድን እና አያክስ አምስተርዳም፣ የ1990 ዎቹ ኤሲ-ሚላን ወይም ከ2008-2012 በጓርዲዮላ የተመራው ባርሴሎና በፍጥነት ወደ ትውስታችን ጓዳ ይዘልቃሉ፡፡ እነዚህ ቡድኖች ስኬታማ ብቻ አልነበሩም-እግርኳስን ውብ በሆነ ሥልት እና “ትክክለኛ” በሚባል የአጨዋወት መንገድ ተግብረዋል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ሁሉም ቡድኖች የሚጋሩት መሰረታዊ ተመሳስሎ አላቸው፡፡ ይኸውም እነዚህ ቡድኖች በ1970ዎቹ በሪኑስ ሚሸልስ አማካኝነት ለዓለም እግርኳስ የተዋወቀው የ”Total Football” እሳቤ ተፅእኖ ያረፈባቸው መሆኑ ነው፡፡ ከሚሼልስ፣ ክራይፍ እና ጋርዲዮላ የጨዋታ አስተምህሮ በተለየ ሁኔታ ማውሪሲዮ ሳሪም ከብዙ ዓመታት በኋላ በጣሊያን የራሳቸውን የአጨዋወት ዘይቤ አምጥተዋል፡፡ በእርግጥ የፔፕ ጓርዲዮላ፣ አሪጎ ሳኪ ወይም አንቶኒዮ ኮንቴ ጉልህ ተፅእኖ ቢያርፍባቸውም ሳሪ ቀደም ሲል ከታዩት በተጻራሪ የራሳቸውን ሐሳብ ያስተጋቡበትና የተለየ ማንነት ያለው ቡድን ሰርተው አሳይተዋል፡፡

በተለይ በ2017-2018 የውድድር ዘመን በሴሪኤው 91 ነጥቦች መሰብሰብ የቻለው ናፓሊ የሊጉን ድል መቀዳጀት ባይችልም ማውሪዝዮ ሳሪ ቡድናቸው እንዲጫወት የሚፈልጉትን የአጨዋወት ዘይቤ ለዓለም ለማሳየት ችለዋል፡፡ በዚህ ቡድን ጎልቶ የሚታየው የእግርኳስ ጽንሰ-ሃሳብ የ”3ተኛው ተጫዋች” ኅልዮት እና የትግበራ ሒደት ነው፡፡

ምንምእንኳ ሐሳቡን ወደ ተግባር የመቀየሩ ዘዴ ቀላል ቢመስልም ንድፈ-ሃሳቡን መረዳት እጅጉን ጠቃሚ ነው፡፡ በእርግጥ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ወስደው ለመጫወት የሚፈልጉ ቡድኖች ለሐሳቡ ትግበራ አናሳ ግምት ሲሰጡ ይታያል፡፡ ነገርግን እነዚህ ቡድኖች በመረጡት የጨዋታ አቀራረብ ውጤታማ ለመሆን ይህኛው ታክቲካዊ ዝግጅት ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ በመቀጠል የ”3ኛው ተጫዋች መርህ” መነሻ ሃሳብ ለምን አስፈላጊ ሆነ? የትኞቹ ዝርዝር ጉዳዮች ጽንሰ-ኃሳቡን ጠቃሚ አደረጉት? እኛስ ለምን ኃሳቡን በጥልቀት መመርመር ያሻናል? ለሚሉ መሰረታዊ ጥያቄዎች ይህ ጽሁፍ ምላሽ ለመስጠት ይሞክራል፡፡

የዚህን ጽንሰ-ሃሳብ ጥቃቅን ጉዳዮች ሳይቀር በዝርዝር ለመረዳት መቻሉ የአንድን ቡድን የአጨዋወት ጥራት ደረጃ ከፍ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ሐሳቡን በንዑሳን-ርዕሶች ከፋፍዬ ለመተንተን እሞክራለሁ፡፡

መሰረታዊ ገቢሮች

ለ”3ኛው ተጫዋች” ንድፈ-ሃሳብ እንግዳ ለሆነ አንባቢ ሐሳቡ በሦስት ተጫዋቾች መካከል የሚደረግ የተቀናጀ የኳስ ቅብብል ማለት ነው፡፡በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፦ ተጫዋች ለተጫዋች ኳስ ማቀበል ይፈልጋል እንበል፡፡ ነገር ግን ተጫዋች የማቀበያ መስመሩ በተጋጣሚ ቡድን ተጫዋች ተዘግቶበታል፡፡ስለዚህም ተጫዋች የቅብብሉን ሒደት ለማስቀጠል ሦስተኛ ተጫዋች መጠቀም ግድ ይለዋል፡፡ ተጫዋች በተዘዋዋሪ መንገድ ለተጫዋች ኳስ እንዲደርስ የሚያስችለውን ሌላ የቡድን አጋር ሦስተኛው-ተጫዋች ብለን እንጠራዋለን፡፡ ታዲያ ይህ ሶሥተኛው ተጫዋች ኳሱን ለመቀበልም ሆነ ለማቀበል ክፍት ቦታ ላይ የሚገኝና ከተጋጣሚ ቡድን የቅርብ ርቀት ጥብቅ ቁጥጥር ነጻ መሆን ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ ተጫዋች ኳሱን ለተጫዋች ያቀብላል፤ ተጫዋች ደግሞ በቀላሉ ለተጫዋች ያቀብላል፡፡ እናም የ”3ተኛውን ተጫዋች” ዘዴ በመጠቀም ተጫዋች በቀላሉ ለተጫዋች ኳስን ያቀብለዋል ማለት ነው፡፡

በምስሉ እንደሚታየው ሐሳቡ ወደ ተግባር ሲለወጥ ቀላል ቢሆንም ከጽንሰ-ሃሳቡ ፍቺ ጀርባ ብዙ ትግበራዎች ይኖራሉ፡፡ እኔም ትንተናዬ ይበልጡን ግልጽና ጥልቀት ያለው እንዲሆን በሚከተለው ጽሁፌ በሙሉ በማውሪዚዮ ሳሪ ሥር ሲሰለጥን የነበረውን የናፖሊ ቡድን አጨዋወት ለዝርዝር ጥናቴ በናሙናነት መጠቀሜን ለማሳወቅ እወዳለሁ፡፡

ከ”3ኛው ተጫዋች መርህ” ጀርባ ያለው መሰረታዊ ሃሳብ

የ”3ኛው ተጫዋች መርህ” ጥቅም ላይ የሚውለው በተጋጣሚ ቡድን ተከላካይ ለተሸፈነው የቡድን ተጫዋች ኳስ ለማቀበል መሆኑን ተረድተናል፡፡ ከዚህ ጀርባ ያለውን ሃሳብ ለመረዳት ደግሞ አንድ ቡድን በኳስ ቁጥጥር የበላይ ሲሆን ሊተገብር የሚያቅደውን ዋነኛ ዓላማ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ በግልፅ ከሚታወቀው ግብ የማስቆጠር ዓላማ በተለየ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት የሚወስድ ቡድን ሁልጊዜም ጠቃሚ የሆነ የሜዳው ክፍል ላይ የሚገኝን ነፃ ተጫዋች ለማሰስ ይጥራል፡፡ ስለዚህም የጨዋታ አቅጣጫን መቀየር ወይም የ”3ተኛው ተጫዋች መርህ”ን የመሳሰሉ ሃሳቦች ሜዳ ላይ በትክክለኛው መንገድ ሲተገበሩ ከተጋጣሚ ተጫዋቾች ጥብቅ ቁጥጥር ነፃ የሆነውን የቡድን አጋር (ተጫዋች) ለማግኘት ያስችላሉ፡፡

በ”3ኛው ተጫዋች መርህ” መሰረት በመጨረሻው የቅብብል ሒደት ኳሷ የምትደርሰው ተጫዋች ከላይ በቀረበው ምሳሌ እንደሚታየው ተጫዋች ነው፡፡ ይህ ተጫዋች የቅብብሉ መዳረሻ እንዲሆን ነጻ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ አሁን-አሁን ቡድኖች 1-ለ-1 ከመከላከል ይልቅ ክፍት ቦታዎችን በመሸፈን እና በእንቅስቃሴያቸው ኳስ ወደ ሚገኝበት ክልል በማዘንበላቸው በብልሃት ኳስን ይዞ የመንቀሳቀስ ሒደት ነፃ የሚሆነውን ተጫዋች ያስገኛል፡፡

ነፃውን ተጫዋች ለማግኘት የሚደረገው እንቅስቃሴ ከላይ በማሳያነት በቀረበው የናፓሊ ቡድን ተመልክቷል፡፡ በምሳሌው መሰረት የቡድኑ ተጫዋቾች ለማሬክ ሃምሺክ ኳስ በማቀበል እርሱ ላይ የተጋጣሚ ቡድን ጫና እንዲፈጠር ያደርጋሉ፡፡ ይህን የሚያደርጉት ለምንድን ነው? ምክንያቱም ተቃራኒ ቡድን ጫና ሲያደርግ ሃምሼክ ኳሷን እግሩ ሥር እንደያዘ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክልል ፊቱን ካዞረ በቀላሉ በመስመሮች መካከል ክፍተት አይቶ ኳስን ማቀበል ይችላል፤ ለዩዲኒዜ ተከላካዮችም አደገኛ ሁኔታን ይፈጥርባቸዋል፡፡

ስለዚህ የሚከተሉት ሁለት ዐበይት ምክንያቶች-ማለትም በተጋጣሚ ቡድን የጨዋታ ሥልት የመበለጥ ሥጋት እና ኳሱን በራስ ቡድን ቁጥጥር ሥር የማድረግ ፍላጎት ተጋጣሚ ቡድን በከፍተኛ ደረጃ ተጭኖ እንዲጫወት ይገፋፋዋል፡፡ ብዙውን ጊዜ በመከላከል ሒደት ላይ ካለው ቡድን በቁጥር ላቅ ያሉት ተጫዋቾች ትኩረታቸውን ተጋጣሚ ቡድን ተጭኖ የሚጫወትበት አካባቢ ያደርጋሉ፡፡ በኳሱ አቅራቢያ ያለውን ቦታ በተቻለ መጠን በማጥበብም የመቀባበያ አማራጭ መስመሮችን ለመዝጋት ይጥራሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ ሌሎች የሜዳው ክፍሎች አንጻራዊ ክፍተት ይፈጠርባቸዋል፡፡ ስለዚህም በቅብብል ሒደቱ ተሳታፊ የሚሆኑ ተጫዋቾች እነዚህን ክፍተቶች ለመጠቀም ይዘጋጃሉ፡፡ ተጫዋቾቹ በዚህ ቅጽበት ኳስ ከደረሳቸው ነጻ ቦታ እና በቂ ጊዜ ስለሚኖራቸው የጨዋታውን ቀጣይ አቅጣጫ መልክ ያስይዛሉ፡፡

ከላይ በተመለከተው ምሳሌ-ዲያዋራ በተቃራኒ ቡድን አጥቂ እና አማካይ ተጫዋቾች ሳቢያ ክፍት ቦታ አጥቶ ይታያል፡፡ ይሁን እንጂ ሃምሺክ ኳስ እንደተቀበለ የተጋጣሚያቸው አጥቂ ኳስ ለማስጣል ሲንደረደር ስሎቫኪያዊው የናፖሊ አማካይ ደግሞ በጥቂት ሰከንዶች እንቅስቃሴ የዩዲኒዜውን የመሃል ተጫዋች እንዲሁ ቦታውን እንዲለቅ አድርጎታል፡፡ ይህም ዲያዋራን ኳስ ከተቀበለ በኋላ ብዙ ክፍት ቦታ እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡

ይህኛው ምሳሌ በመጀመሪያው ኳስ ለየት ባለ የማቀበል ሒደት ጫና መፍጠር ውጤታማ እንደሚያደርግ ያመለክታል፡፡ በምስሉ ላይ እንደሚታየው ሶስት የዩዲኔዜ ተጫዋቾች ተጋጣሚያቸውን ተጭኖ የመጫወት እድል አላቸው፡፡ በዚህም ናፓሊዎች የ”3ተኛ ተጫዋች መርህ”ን በመተግበር ሊጠቀሙበት የሚችሉት በሰማያዊ የተመለከተ ክፍት ቦታ ተፈጥሮላቸዋል፡፡

የ”ሦስተኛው ተጫዋች መርህ”ን የመጠቀም ዓላማ ነፃ ተጫዋች ከመፍጠር ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም፡፡ ቀደም ብለው የቀረቡት ሁለቱም ምሳሌዎች ሌላ በትኩረት ልናጤነው የሚገባ አስፈላጊ የታክቲክ መፍትሄ እንዳለ አሳይተዋል፡፡በቅብብል ሒደቱ መጨረሻ ላይ ኳስ የሚቀበለው ተጫዋች ፊቱን ወደ ተጋጣሚ ቡድን የግብ ክልል ሲያዞር የቡድን አጋሮቹ ወደ እርሱ ተጠግተው እንደሚንቀሳቀሱ ይገነዘባል፡፡

እዚህ ጋር መረዳት ያለብን መሰረታዊ ጉዳይ ለአንድ አጥቂም ሆነ ሌላ ተጫዋች ኳስ ይዞ የተቃራኒ ቡድን ጎል ፊት መድረስ በሜዳው ላይ የሚገኙ አብዛኞቹን ተጫዋቾች የማየት ዕድል ይሰጠዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የተጋጣሚ ቡድኑን የመከላከል አደረጃጀት የመመልከት አጋጣሚም ያገኛል፡፡ በእርግጥ አንድ ተጫዋች ኳስ ከቡድን አጋሮቹ እንደተቀበለ ሰውነቱን በቀላሉ በማዞር ወደ ፊት መገስገስ ይችላል፡፡ ያም ሆኖ በዘመናዊ እግርኳስ ይህን ማድረግ ከባድ ሆኗል፡፡ ቡድኖች በከፍተኛ ጥግግት በሚያደራጁት የመከላከል ሒደት እና ተጫዋቾች ካላቸው የላቀ ጨዋታ የመረዳት አቅም መጎልበት ጋር በተያያዘ በቀላሉ ኳስን ይዞ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክልል በዘፈቀደ መክነፍ ፡፡

በምስሉ ላይ ዲያዋራ በቂ ቦታ ሲያገኝ ይታያል፡፡ በዚህ ቅጽበት ኳስ እግሩ ሥር እንደያዘ በቀላሉ አቅጣጫውን መቀየር ይችላል፡፡


የጽሁፉ ተርጓሚ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል፡፡ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፂዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ