የሴቶች ገፅ | የቅጣት ምቷ ስፔሻሊስት ሕይወት ደንጊሶ

በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ውስጥ ከሚጠቀሱ ጠንካራ ተጫዋቾች መካከል አንዷ ነች። ተክለ ሰውነቷ፣ ከረጅም ርቀት እና ከቅጣት ምት የምታስቆጥራቸው አስደናቂ ጎሎቿ መገለጫዎቿ ናቸው፡፡ በሴንትራል ዩኒቨርሲቲ የጀመረው የክለብ ህይወቷ ዛሬ ላይ ጎልታ ለታየችበት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አብቅቷታል፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ከ2002 ጀምሮ ያለማቋረጥ ዛሬም ድረስ እየተጫወተች የምትገኘው የተከላካይ አማካይ ሕይወት ደንጊሶ በዛሬው የሴቶች ገፅ መሰናዷችን ቃኝተናታል፤ ተከታተሉን፡፡

ከሚሊኒየሙ መግቢያ አንስቶ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በመሀል ሜዳው የተከላካይ አማካይ ስፍራ ላይ ጥንካሬን የፈጠረ የሴት ተጫዋች ማግኘት እጅጉን ከባድ ነው። እግር ኳስን በልጅነቷ ግብ ጠባቂ ሆና ብትጀምር ከጊዜያት በኃላ በተከላካይነት እንዲሁም በአሁኑ ሰአት ደግሞ በተከላካይ አማካይ ስፍራ ላይ ተፅኖ ፈጣሪ ከርቀት በሚመቱ እና ከቅጣት ምት በሚገኙ አጋጣሚዎች አስደናቂ ግቦችንም ጭምር ከመረብ በማዋሃድ መለያዎቿ የሆኑላት አልፎም የተዋጣላት ጠንካራዋ የመሀል ሜዳ ተጫዋች ህይወት ደንጊሶ፡፡
ተወልዳ ያ
ደገችው ሀዋሳ የብዙሀን የእግርኳስ ተጫዋቾች መነሻ በሆነው ኮረም ሰፈር ውስጥ ነው፡፡ እሷም በዚህ ሰፈር ውስጥ ተወልዳ ማደጓ እግር ኳስን እንድትወደው አልፎም ደግሞ ዛሬ ላይ እንጀራዬ ብላ እንድትይዘው ትልቁን አስተዋጽኦ እንዳበረከተላት መለስ ብላ አጫውታናለች፡ ሕይወት በልጅነቷ ከቤታቸው ቅርብ ወደ ሆነው ኮረም ሜዳ ብቅ እያለች ኳስን ለመመልከት ብላ በተደጋጋሚ ስትሄድ እነ አዳነ ግርማ እና ሙሉጌታ ምህረትን የመሳሰሉ ተጫዋቾች በሜዳው ላይ ልምምድ ሲያደርጉ ትመለከትና ‘እኔም መጫወት አለብኝ’ ወደ ሚል ሀሳብ ውስጥ ትገባለች። እግር ኳስን እጅግ ከመውደዷ የተነሳም ያለማምንታት መጫወትን ጀመረች። “ህፃን ሆኜ የምሰራው ሰርከስ ነበር። ነገር ግን አንዳንድ ተጫዋቾችን ስመለከት እኔም ለመጫወት ተነሳሳሁ። አንድ ጊዜ አሰልጣኝ መለሰ ከበደ ፕሮጀክት እንድገባ ተደረኩ። ከመግባቴ በፊት ግን ሴት ተጫዋቾች ክልል ተመርጠው ሲሄዱ እመለከት ነበር። በተለይ በእኛ አካባቢ ያሉ እነ ሊያ ሽብሩ፣ ተራማጅ ተስፋዬ እና ወይንሸት ጸጋዬ (ኦሎምቤ) እነሱን እመለከት ስለነበር ተነሳሽነት ፈጥሮልኛች። በዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ ባህርዳር ላይ ሄጄ የክልል ምርጥ ውስጥ መጫወት ጀመርኩ። በዚህ ጊዜ ግን እኔ በረኛ ነበርኩ። አሰልጣኝ መለሰ ሲያየኝ በጣም ልጅ ስለነበርኩና ከእኔ የሚበላልጡ እነ ተስፋነሽ የሚባሉ በረኞች ስለነበሩ ቢያንስ ልምድ ያላቸው ስለነበሩ ‘አንቺ ለበረኝነት አታዋጭም’ ብሎ ወደ ተከላካይነት ቀየረኝ።” ስትል የእግር ኳስ አጀማመሯን አውስታናለች፡፡

ሀዋሳ ውስጥ የሰርከስ ቡድንን ተቀላቅላ መስራት ብትጀምርም በአካባቢዋ ላይ ወንድም ሆነ ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች እጅጉን በርካቶች በመሆናቸው እሷም ልቧ ወደ ሸፈተው የእግር ኳሱ ዓለም ተቀላቅላ ጉዞዋን ቀጠለች፡፡ ሀዋሳ ውስጥ ከ1990ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ በሴቶች እግር ኳስ ላይ ትልቅ አሻራ በጣለው አሰልጣኝ መለሰ ከበደ ታቅፋ ስልጠናን የጀመረችው ሕይወት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበሰለች ስትመጣ ለሀዋሳ ከተማ እና ለደቡብ ክልል ምርጥ በተደጋጋሚ በመመረጥ መጫወት ቻለች። በአንድ ወቅትም ቢሾፍቱ ላይ በነበረ አንድ የክልል ምርጥ ውድድር ላይ አካባቢዋን ወክላ በመጫወት ላይ እያለች ነው ወደ ክለብ ሕይወት ለመግባት መንደርደር የጀመረችው። በወቅቱ ሌሎች ሰባት ተጫዋቾች ብቻ የተጠሩ የነበረ ቢሆንም አሰልጣኝ መለሰ ከበደ አቅሟን ያውቅ ነበረና ለቤተሰቧ ነግሮ አዲስ አበባ ድረስ ይዟት በመሄድ ከተጠሩት ሰባት ተጫዋቾች ጋር ስምንተኛ አድርጎ ወደ አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ቡድን ሴንትራል ይዟት አመራ።

“የክልል ምርጥ ባቱ (ዝዋይ) ላይ ነበር ከዝዋይ በኃላ ደግሞ ቢሾፍቱ (ደብረዘይት) ተካሄደ። ከዚህ ውድድር በኃላ ነው ተመርጬ ወደ አዲስ አበባ የሄድኩት ማለት ነው። በወቅቱ እኔ አልተፈለኩም ነበር፤ የተፈለጉት ሰባት ተጫዋቾች ነበሩ። በዚህ አጋጣሚ አሰልጣኝ መለሰ ከበደ ከሰባት ተጫዋች ስምንተኛ አድርጎኝ ቤተሰቤን አስፈቅዶልኝ ወደ አዲስ አበባ ይዞኝ ስለመጣ ሳላመሰግን አላልፍም። አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ጋር የደቡብ ልጆች ሰባት ብቻ ነበር የተፈለጉት እኔ ስምንተኛ ስለነበርኩ አሰልጣኝ መለሰ እሷንም ተመልከታት ብሎ ለአሰልጣኝ ብርሀኑ ነገረውና መጀመርያ አልጠራዋትም ብሎ ነበር። ግን ሲያየኝ አንደኛ ከተመረጡት መሀል እኔ አንዷ ሆኜ ተገኘሁ። ከዛ በኃላ ወደ ሴንትራል ኮሌጅ ገባሁ።” ስትል በፍጥነት ወደ ክለብ ሕይወት ያመራችበትን ወቅት ገልፃልናለች፡፡

ከአስር ዓመታት በላይ በክለብ ህይወት ውስጥ የምትገኘው ሕይወት ደንጊሶ 2000 ላይ ሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ገብታ የአምስት ዓመት ቆይታዋን በሚገባ ካጠናቀቀች በኃላ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቡድን ውስጥ ከ2005 ጀምሮ በፕሪምየር ሊጉ ላይ በወጥነት እያገለገሉ ካሉት ተጠቃሽ ተጫዋቾች አንዷ መሆን ችላለች፡፡ አብዛኛዎቹ የእግር ተመልካቾች በሜዳ ላይ ጠንካራ እልህኛ እንዲሁም የቅጣት ምት አጠቃቀሟ የተዋጣላት እንደሆነ የሚናገሩላት ሲሆን ላለፉት አስራ ሁለት ዓመታት ከሴንትራል ዩኒቨርሲቲ እስከ አሁኑ ንግድ ባንክ ድረስ አልፎም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እያሰለጠናት የዘለቀው በእሷም አገላለፅ “አባቴ ነው” የምትለው አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ስለ ሕይወት ደንጊሶ እንዲህ ይላል። “ሕይወት ማለት ከእግር ኳሱ ውጪ ገራገር የሚባል ሰው ታውቃለህ? ከተወለደችበት ካደገችበት አካባቢ ይሁን አላውቅም ገራገር የምትባል ሰው ነች። ሁለተኛ በስልጠና የነገርካትን በመቀበል በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ያደርጋታል። ለምሳሌ አንዳንድ ተጫዋቾች የሆነ ቦታ ላይ ፈረምኩ ካሉ ወይም ወደ ሌላ ከጥቅም ጋር ወደ ሌላ ሊቀይሩ ይችላሉ። ይሄ እሷ ጋር የለም። ሕይወት እንደሚታወቀው ትውልዷም እድገቷም ሀዋሳ ነው፡፡ በልጅነቷ በረኛ ነበረች። ከእዛ ተነስታ ወደ እኔጋም ስትመጣ ተከላካይ ነበረች፡፡ ተከላካይ ሆና ግን ለተወሰነ ጊዜ ስኬታማ አልነበረችም። አጋጣሚ ሴንትራል ካምፕ በነበረ ጊዜ በግሏ እየወሰድኩ አሥራት ስለነበረ በአንድ ጊዜ ከኦቨርቤንች ወደ ቤንች፤ ከቤንች ወደ ቤስት እንደገና ብሔራዊ ቡድንም ተጠርታ ተመልሳ የመጣችበት አጋጣሚ ነበር። በዓመቱ ብሔራዊ ቡድኑን ተከላካይ ሆና አገልግላለች። አሁን ደግሞ ለረጅም ጊዜ የተከላካይ አማካይ ሆና ቦታውን ተቆጣጥራለች፡፡ ሕይወትን ለዚህ ደረጃ ካበቃት እና ካስቀመጣት ዋነኛ ነገሯ የምትሰጣትን ነገር ትቀበላለች። ሌላው እልኸኛ ናት። ከምልህ በላይ ነው እልህዋ። አብዛኛውን ጊዜ ከእኔ እድገት ጋር ተያይዞ ጥንካሬዎችን ለእኔ የምትሰጥ ናት። ብዙ ጓደኞቼ አማካሪዎች ቢኖሩኝ አንዷ እሷው ናት። አንዷ እሷው ናት ስልህ ለምሳሌ የሰጠሀትን ስትራቴጂ ትወጣለች። በአንድ ወቅት እንደውም ሁለት አጥቂዎች ተጎዱብኝ (ሽታዬ እና ረሂማ) ከዛ በእሷ በቅጣት ምት አንድ ለባዶ አሸነፍን። ቅጣት ምት ስለማለማምዳት ንግድ ባንክ 1-0 ካሸነፈና ወይ በቅጣት ምት ወይንም በግንባር አሸንፈን ከወጣን በሷ ጎል ነው፡፡ ለእኔ ሕይወትን ዝም ብለህ ግለፃት ካልከኝ በጣም በኢትዮጵያ ውስጥ ምርጥ ተጫዋች ከሚባሉት በጣም ገራገር ከሚባሉት ተጫዋቾች ግንባር ቀደሟ ናት። ሁለተኛ የሜዳ ላይ ጥንካሬዋ የሚጠቀስ ነው። ተክለ-ሰውነቷም ለመጉላቷ አስተዋፅኦ አድርጓል። አንዳንድ የአፍሪካ ሀገር ስንሄድ ቀድመው እሷን ነው የሚያዩዋት። ሌሎቹ ደቀቅ እንላለን ለእሷ ግን የሰጠ ነው። ይሄ ደግሞ እይታ ውስጥ በደንብ እንድትገባ አድርጓታል፡፡ ባላት ነገር ላይ ደግሞ ጠንካራ ሆና መስራቷ እና የሥራ ዲሲፕሊኗ አስገራሚ ነው። በስልጠና ከስልጠና ውጪ እኔ በማዘው በሙሉ ቀድማ ተግባራዊ የምታደርግ ስለሆነች እግርኳሱ ከሕይወት ተጠቅሟል ብዬ አስባለሁ። ከዚህ በኃላም በደንብ ይጠቀማል ብዬ እጠብቃለሁ” ሲል ረጅም ጊዜ አብሯት የዘለቀው አንጋፋው አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ዘርዘር አድርጎ መስክሮላታል፡፡

ለፕሮጀክት አሰልጣኟ መለሰ ከበደ እንዲሁም በንግግሮቿ መካከል አባቴ ብላ ለምትጠራው አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ትልቅ አክብሮት ያላት ሕይወት ደንጊሶ ከተከላካይነት ወደ አማካይ ተከላካይነት ቦታ ስለ ተሸጋገረችበት ጊዜ እንዲህ ስትል አጋጣሚውን ትናገራለች፡፡ “የሚገርምህ አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ነው። በአንድ ጨዋታ ቤስት ነበርኩ፤ በወቅቱ ህመም ይገጥመኛል። እንደ ታይፎይድ ነገር ሲያመኝ ልምምድ ቀርቼ ነበር። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ሦስት ነበርን በቦታው ላይ የምንጫወተው። እኔ ስለታመምኩ አንድ ልጅ በዛ ጨዋታ ላይ ገባችና ተጫወተች። በነጋታው ብሬ እኔን ስለሚፈልገኝ ብቻዬን ጃን ሜዳ ላይ ልምምድ አሰራኝ። ከዛ በኃላ ቤንች ላይ እንድቀመጥ ተደረኩ። ተጠባባቂ ላይ ቁጭ ብዬ ከነበሩት እኔን ጠርቶ ሳልጠብቀው ስኪመር ላይ አስገባኝ። ለእርሱም ቦታው ላይ ልምድ አላቸው ከሚባሉት በላይ ተሽዬ ተገኘሁ። የመጀመሪያዬ አይመስልም ነበር ስጫወት። በቃ ጎል እስከ ማግባት ደረጃ ሁሉ ደረስኩና በዛው ቀጠልኩ። እሱም ሲያየኝ ጥሩ ስሆንበት በተደጋጋሚ በጣም ቦታው ላይ እኔን ማሰራት ጀመረ። ብዙ ነገሮችንም አስተምሮኝ ይኸው ከ2005 ጀምሮ ስኪመር ቦታ ላይ እየተጫወትኩኝ እገኛለሁ።” በማለት የጨዋታ ቦታ ሽግግሯን በተለይ ደግሞ ለስኬት ስለበቃችበት የተከላካይ አማካኝነቷ አውግታናለች፡፡

ከሴንትራል ዩኒቨርሲቲ አንስቶ የአዲስ አበባ የዲቪዚዮን ዋንጫን በመሳም የጀመረችው ሕይወት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ2005 ጀምሮ በፕሪምየር ሊጉ በግሏ ከማንፀባረቅ በዘለለ ክለቡ በተደጋጋሚ የዋንጫ አሸናፊ መሆን ሲችል የዚህ ቡድን አካል በመሆን ከሌሎች የቡድን ጓደኞቿ ጋር ባለ ክብር መሆንም ችላለች፡፡ “በሴንትራል ዩኒቨርሲቲ የማይረሱ ደስ የሚሉ ጊዜያቶችን አሳልፌ ነው ወደ ንግድ ባንክ የገባሁት። ሴንትራል ላይ የነበረን አቋም፣ የነበረን ብቃት የነበረን፣ ፍቅር ልነግርህ ከምችለው በላይ ደስ ይል ነበር። ከሀዋሳ እንደመጣሁ ሀዋሳም እያለሁ በልጅነቴ ሀዋሳን ወክለን ስንጫወት ዋንጫ እንበላ ነበር። ግን ሴንትራል ነው ለእኔ ውጤታማ እንድሆን ያደረገኝ። ምክንያቱም ዋንጫ ሳንበላ ያለፍንበት ወቅት የለም፤ ሦስቱንም ዋንጫ ነበር የምንበላው። ስለዚህ ሴንትራል ላይ ደስ የሚል የውጤታማነት ጊዜ ነው ያሳለፍኩት። ወደ ንግድ ባንክም ያሸጋገረን ያ ታሪካችን ይመስለኛል። ራሳችንን የቀየርንበት በዋንጫ ያሸበረቅንበት፤ ለዛሬውም ስኬት ያበቃን ሴንትራል ነው። ሴንትራል ዋንጫ ማንሳት ባንችል ኖሮ እርግጠኛ ነኝ ንግድ ባንክ አይገዛንም ነበር። ምክንያቱም ማንኛውም ቡድን ውጤታማ የሆነን ቡድን ነው የሚፈልገው። እስከ አሁን ከገለፅኩት የሴንትራል ቆይታዬ ባሻገር የንግድ ባንኩ ለእኔ ጣፋጭ ጊዜ ነበር። ለእኛ እዚህ የመድረሳችን ምስጢር ውጤታማ መሆናችን ነው፡፡ ውጤታማ ባትሆን አንድ ክለብ ለአንተ ያለው ቦታ ይቀንሳል፡፡ በዛን ጊዜ ለሴቶች ብዙም ነገር አይደረግም ነበር። ”

ሕይወት የእግርኳስ ጉዞዋ ላይ ትልቅ አስዋፅኦ ያበረከተው ብርሀኑ ግዛውን እንዲህ ስትል ትገልፀዋለች። “እኔ ስለ እርሱ ስናገር ዕንባዬ ይመጣል። ብርሀኑ የእኛ የሴቶች የህይወት መሠረት ነው ብዬ ነው የማስበው። ምክንያቱም እሱ ስለ እኔ አያውቅም ነበር። ማንም ሌላ አሰልጣኝ አሰርቶኝ አያውቅም፤ በፕሮጀክት አሰልጣኝ መለሰ ከበደ ብቻ ነው ሀዋሳ እያለሁ፡፡ እሱ ግን እምነት ጥሎብኛል። አሁን ብርሀኑ አሰልጣኜ ብቻ ሳይሆን አባቴም ነው፡፡ ለንግድ ባንክ እና የሴቶች እግርኳስ ማደግ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተው አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ነው፡፡ ስለ ብርሀኑ ማንም ይመሰክራል። እሱ ስላለ ነው ንግድ ባንክም ያለው፤ እኛም ያለነው። እኛም ስላለን ነው እሱም ያለው። አሰልጣኙ ጥሩ ነገር ባይኖረው ኖሮ እርስ በእርስ እየተናናቅን ውጤት አይመጣም ነበር። ከ2005 እስከ 2008 በዚሁ መንገድ በንግድ ባንክ ጣፋጭ ጊዜን አሳልፌያለሁ። ዋንጫ እያነሳን እየበላን ነው፤ አንድ ብቻ አይደለም ሦስቱንም ሁለቱንም ዋንጫ ነው፡፡ ለእኔ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቃ ቤቴ ነው። የምበላበት የምጠጣበት ቤቴ ነው።” ስትል ስለ ንግድ ባንክ አልፎም ስለ አሰልጣኟ በዝርዝር የገለፀችው፡፡

2002 በሴንትራል ክለብ ውስጥ እየተጫወተች በአሰልጣኝ መሠረት ማኔ እና ቴዎድሮስ ደስታ አማካኝነት ሀገሯን ለማገልገል በሉሲዎቹ ስብስብ የመጀመሪያው ጥሪ ተደርጎላት የነበረ ቢሆንም በወቅቱ ከመጠራት ያለፈ የመጫወት ዕድልን በቶሎ ማግኘት ግን አልቻለችም። ከ2005 ጀምሮ ግን ቁልፍ ተጫዋች ለመሆን በቅታ ዛሬም ድረስ እየተጫወተች ዘልቃለች፡፡ “ለብሔራዊ ቡድን ትልቅ ነገር አድርጊያለሁ ብዬ አስባለሁ። በመሠረት ማኒ ጊዜ 2002 ላይ ተጠርቼ ነበር፤ አውትኦፍ ነበርኩኝ። የዛን ጊዜ ሁለተኛው ብሔራዊ ቡድን ላይ ግን ብርሀኑ እና አሥራት በያዙበት ወቅት ጠሩኝ አስገቡኝ የመጀመሪያዬ ነው ለብሔራዊ ቡድን ስሰለፍ ለብሔራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ቢሆንም የገባሁት አልደነገጥኩም። ኮንጎ ላይ ነበረ ጨዋታው። ገብቼ ሲኒየሮች ነበሩ እነ ብዙሀን አሉ እነ ኦሎምቤ አሉ ከእኛ በፊት ብሔራዊ ቡድንን ያውቃሉ ከእነርሱ ጋር ተሰልፈህ መጫወት መቻልህ በራሱ ትልቅ ዕድለኝነት ነው። በራሱ ለእኔ በዛን ሰዐመት በተለይ ከብዙሀን እንዳለ አጠገብ መጫወት እድለኝነት ነበር። ምክንያቱም ብሔራዊ ቡድን ገብቼ መጫወት ምናምን አላውቅም ነበር። ገብቼ ስጫወት ምንም ውስጤ ድንጋጤ አልነበረም፤ ጥሩ ነገር ነበር አድርጌ የወጣሁት። ልጆች ሁሉ ጀግና ነሽ ነው ያሉኝ የመጀመሪያሽ በብሔራዊ ቡድን ሆኖሽ አለመደንገጥሽ ብለው አበረታቱኝ። ከዛን በኃላ የመልስ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ከመሀል ሜዳ ኮንጎ ላይ ከቅጣት ምት አገባሁኝ ለራሴ አላመንኩም። እኔ ነኝ ያገባሁት እስከምል ድረስ ተቃቅፈን እየጨፈርን አላመንኩም ነበር። ህዝቡ ሲጮህ የምትደነግጠው ነገር አለ አይደለ ካገባሁት ጎል በላይ ህዝቡ ሲጮህ እኔ ደነገጥኩ። ከዛ ጊዜ ጀምሮ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ እየተጫወኩኝ ቀጠልኩ። እነ አብርሃም ተክለሃይማኖት እና ብሬም በያዙበት ወቅት ለአፍሪካ ዋንጫ ቡድኑን ስኬታማ አድርጊያለሁ። ከዛን ጊዜ ጀምሮም በብሔራዊ ቡድን ተጠባባቂ ሆኜ አላውቅም ቤስት በሚባል አቋም ላይ ስሆን ለባንክም ሆነ ለሀገሬ ቤንች ሆኜ አላውቅም።” ያለችው ሕይወት በቀጣይም ሀገሯን በበለጠ ለማገልገል ውጥኗ እንደማይቋረጥ በድፍረት ገልፃለች፡፡

ከቤተሰቦቿ መካከል ወላጅ እናቷ ቢሻሽ በቀለ እግር ኳስም ሆነ መረብ ኳስን ተጫውታ እንዳለፈች የገለፀች ሲሆን ታናሽ እህቷ ትህትና ደንጊሶም ሙገር ሲሚንቶ እስከፈረሰበት ጊዜ ድረስ የቡድኑ አባል እንደነበረች ይታወቃል፡፡ እህቷ ምንም እንኳ በጉዳት ከጨዋታ ዓለም ብትገለልም እርሷ ግን ዛሬ ድረስ በተሻለ አቅም ላይ እንደቀጠለች ትገኛለች፡፡ ታላላቅ እህቶቿ ወደ ትምህርቷ እንድታዘነብል ቢወተውቷትም ወላጅ እናቷ የእግር ኳስን ጣዕም ታውቀው ስለነበረ ከመቃረን ይልቅ ብርታት መስጠትን ከመከልከል ይልቅ አይዞሽ ማለትን ለህይወት ገና ከልጅነት ጊዜዋ ጀምሮ ብርታት እንደሆነቻት ስለ እናቷ ስትናገር “ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሮጀክት ተመርጪ ወደ ባህርዳር ስሄድ ለእኔ የሚያደርጉት ድጋፍ ከፍ አለ። እኔ በዚህ አጋጣሚ ከልብ አልቅሼ የምናገረው ስለ እናቴ ነው። እናቴ ለእኔ የታሪኬ መሠረት ናት እሬሷ ባትፈቅድልኝ እኔ እዚህ ጋር አልመጣም ነበር እዚህም ደረጃ አልደርስም ነበር፡፡ እህቶቼ ባህርዳር ላይ ሄጄ ተጫውቼ ባልመጣ ኖሮም አያበረታቱኝም ነበረ ለእኔ እናቴ ነበረች መለያ የምትገዛልኝ የነበረው። እናቴ ለእኔ የሕይወቴም ሆነ የእግር ኳስ መሠረቴ ናት። በነገራችን ላይ ከዚህ በፊት ተጫዋች ነበረች። እግር ኳስ ድሮ መረብ ኳስም ትሞክር ነበር፡፡ ያቤሎ አካባቢ ተወልዳ ባደገችበት አካባቢ ማለት ነው። ለዛ ለእኔ ትልቁን ነገር አድርጋልኛለች። እርሷ ባትፈልቅድልኝ ብርሀኑ ጋር አልመጣም ነበር። እርሷም ባትፈቅድልኝ አሰልጣኝ መለሰ ከበደም ይዞኝ አይመጣም ነበር፤ እዚህም ደረጃ አልደርስም ነበር። የህይወቴ መሠረት ናት። በአሁን ሰዓት በእኔ ቤተሰቦቼ አይደራደሩም። እናቴ እኔ የማላውቀውን ነገር ትነግረኛለች። አንዳንዴ የብሔራዊ ቡድን ምርጫ ሲኖር ሳልሰማ ሲያመልጠኝ ሲቀር ስለ ኳስ ሲነገር ቁጭ ብላ ስለምታይ ከእርሷ ነው የምሰማው። የሚገርምህ ስለ ንግድ ባንክም ሲወራ እናቴ አለች ማለት ነው፡፡በዚህ ሰዓት ከሚደግፉኝ ከሚያበረታቱኝ እናቴ አለች። እህቶቼ አሉ አራት ነን ሦስት እህቶች አሉኝ። እኔ አራተኛዋ እኔ ነኝ ታናሼ ትህትናም ትጫወት ነበር። እግሯን ትንሽ አሟት አሁን አቁማ ወደ ትምህርቷ አዘንብላለች፡፡ እህቶቼም እናቴም ጥሩ ነገር አላቸው። ለእኔ ባለቤቴንም ጨምሮ እንደ ስራ ኳስን ስለያዝኩ እነሱም ይረዱኛል። የሚገርምህ እናቴ አሁን እግሯን አሟት ቀረች እንጂ አሁንም ድረስ ሀዋሳ ለጨዋታ ስሄድ እህቶቼ ሜዳ ገብተው ይደግፉኛል፡፡ ትልቋ እህቴ ሜዳ ላይ ንግድ ባንክ ሲሰደብ ሁሉ ሲሜታዊ ሆነው ይናገራሉ ከእኔም አልፎ ይሄን ያህል ደርሷል እናቴ ቤት ሆና የሴት ጨዋታ ከተባለ በቴሌቪዥንም ታያለች ድሮ የሚከለክሉኝ አሁን ላይ ይቅናሽ እያሉ ያበረታቱኛል አሰልጣኜ ብርሀኑ ግዛውመም ከዚህ በላይ እንደድሆንለት ይፈልጋል”በማለት ስለ ቤተሰቧ በተለይ ስለ እናቷ ተናግራም አትጠግብም፡፡

ከርቀት በአመዛኙ ደግሞ ከቅጣት ምት ግቦችን የማስቆጠር መለያ ቢኖራትም በሌላኛው በኩል ደግሞ ተለዋዋጭ የሆነው የፀጉር ስታይሏም መገለጫዋ ነው። እኛም በተለየ መልኩ ትኩረት ስለሚስበው የፀጉር አቆራረጧ ከየት የተገኘ ወይንም ከየት የመጣ ነው ስንል ጠይቀናታል፡፡ “….እየሳቀች፤ ማለት እኔ በጣም ደስ ይለኛል፤ በአቆራረጤ እኮራለሁ። የዚህን ሀገር ስታይል አይቼ አይደለም ይሄን የማደርገው። በነገራችን ዳንስ እወዳለሁ። ድሮም ሰርከስ ስሰራ ዳንሰኛ ነበርኩ እና ሪሀናን አያለሁ። በቴሌቪዥን በብዛትም የርሷን ስታይል ነው የምወስደው። የፀጉር ቁርጤን እና የተለያዩ ነገሮችን እጠቀማለሁ። ዛሬ አሳደገች ሲባል ነገ ተቆርጪ የምታገኘኝ ማለት ነው በጣም ስታይል እወዳለሁ ወጣ ያለም ነገር ደስ ይለኛል፡፡ የሪሀናን ስታይል ከበፊት ጀምሮ መውሰድም ደስ ይለኛል ስለማያት ማለት ነው ከዛ የመጣ ነው ይሄ ነገር።

“ሜዳ ላይ በጨዋታ ሒደት አላስፈላጊ ስድቦች መኖራቸውን አላምንም መልሼም አልናገርም። በሥራ ለመመለስ እንጂ በስድብ መልስ መስጠትን አልወድም። ይሄንን አለማድረጌ የተለየ ባህሪ ነው።” የምትለዋ ህይወት ከሰዎች መሳቅ፣ መጫወት፣ መቀለድ እና መግባባት ጋርም እጅጉን ያስደስተኛል ብላለች፡፡ ከልምምድ በኃላ ከቤት ያለመውጣትም ልምድ እንዳላት የምትናገረው ተጫዋቿ በቀጣይ የጨዋታ ዘመኖቿ በንግድ ባንክ ዳግም የውጤታማነት ጊዜን ማጣጣም ህልሟ እንደሆነ እና በኮሮና ወረርሽኝ ያጣነውን የዋንጫ ጉዞ በዘንድሮው የውድድር ዓመት አሳካዋለሁም ስትል ገልፃለች፡፡ “ዕድሉን ካገኘሁ በውጪ የመጫወት ዕቅድ በውስጤ አለ” የምትለዋ ህይወት ደንጊሶ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ለአፍሪካ ዋንጫ አልፎ መታየትንም እንደምትመኝ በመጨረሻም ተናግራለች፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!