“የኢትዮጵያ ግብጠባቂዎች አብዮት በኛ ዘመን ይነሳል” ተስፈኛው ግብጠባቂ ዳዊት በኃይሉ

የኢትዮጵያ ወጣቶች አካዳሚ ፍሬ የሆነው እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ተስፋ ቡድን መልካም ነገሮችን እያሳየ የሚገኘው ግብጠባቂ ዳዊት በኃይሉ የዛሬው ተስፈኛ ገፅ ተረኛ እንግዳ ነው።

ተወልዶ ያደገው ካዛንቺስ ከፍተኛ ስድስት አካባቢ ነው። ወላጅ አባቱን አይመልከታቸው እንጂ ቀድሞ በተለያዩ ክለቦች በግብጠባቂነት ያገለግሉ እንደነበረ ከአባቱ ጓደኞች ሲሰማ እና በፎቶ ሲመለከት አድጓል። የአጋጣሚ ሆኖ በምን መንገድ መነሻ አድርጎ እንደሆነ ብዙ መላ ምት የሚያስፈልገው ቢሆንም የዛሬው የተስፈኞች አምዳችን ተረኛ እንግዳችን ግብጠባቂ ነው።

በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ያለፉትን አራት ዓመታት በስልጠና ቆይቷል። በነዚህ ሁሉ ዓመታት ከ17 –20 በታች የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መጫወት ችሏል። ልጅነቱ ጀምሮ ከቤተሰቡ በወረሰው ማሊያ የቅዱስ ጊዮርጊስ የልብ ደጋፊ ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ አበባ ጨዋታ አለው ከተባለ ይህን ብላቴና ስታዲየም ቢፈለግ አይታጣም። ከልጅነቱ ጀምሮ ሲመኘው የነበረውን ለማሳካት መንገድ ጀምሯል። አሁን ከደጋፊነት አልፎ ከ2012 ጀምሮ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተስፋ ቡድን እየተጫወተ ይገኛል። ሶከር ኢትዮጵያ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተስፋ ቡድን ዓምና ከኢትዮጵያ ቡና፣ ከመከላከያ፣ ከጥሩነሽ ዲባባ ጋት ያደረገውን ጨዋታዎች እንደተመለከትነው ከሆነ በየጨዋታዎቹ ከፍተኛ መሻሻል እያሳየ ጥሩ ቅርፅ ላይ እየመጣ ሳለ የኮሮና ቫይረስ በሀገራችን ስጋት ሆኖ ውድድሮች መቋረጣቸው እድገቱ ላይ ተፅእኖ ሳያሳድር አልቀረም። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከጥሪ ባለፈ የመጫወት እድል ባያገኝም ደፋር፣ ብስለት ያለው እና አንድ ለአንድ ጥሩ የማዳን ችሎታ እንዳለው የተመለከትነው ተስፈኛው ግብጠባቂ ዳዊት በኃይሉ አሁን ስላለበት እና ስለ ወደ ፊቱ እቅዱ እንዲህ ይናገራል።

“አባቴ አሁን በህይወት የለም። ነፍሱን ይማረው እና ሲጫወት ባላየውም ቀድሞ ግብጠባቂ እንደነበረ ጓደኞቹ ይነግሩኛል። ምን አልባት ግብጠባቂ እንድሆን ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። ካዛንቺስ አካባቢ ምንም አይነት ሜዳ ባለመኖሩ ወደ አቧሬ 28 ሜዳ እየሄድን ነበር ተጫውተን የምንመለሰው። በኃላም መብራት ኃይል ቡድን በታዳጊ እድሜዬ እጫወት ነበር። በአጋጣሚ የጓደኛዬ ቡድን አካዳሚ የነበረውን ጨዋታ ለመከታተል ሄጄ እኔም እዛው ተመዝግቤ ከ2008-11 ድረስ በአካዳሚ ስጫወት በቂ የግብጠባቂነት ስልጠናዎችን አግኝቼ ባሳየሁት ጥሩ ነገር አምና ቅዱስ ጊዮርጊስ ገብቻለው።

“እውነት ለመናገር ከልጅነቴ ጀምሮ ስደግፈው የቆየሁት የቤተሰቤ ክለብ የሆነውን ቅዱስ ጊዮርጊስ በመግባቴ እና የእርሱን ማልያ ለብሼ በመጫወቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። ዓምና እንደገባሁ የመጀመርያ ጨዋታ ተጠባባቂ ነበርኩ። ሆኖም ዋና ቡድን ላይ ማታሲ ሲጎዳ የተስፋ ቡድኑ የመጀመርያው ተሰላፊ አቡበከር ወደ ዋናው ቡድን ተጠርቶ በመሄዱ የእርሱን ቦታ ተክቼ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖልኝ መጫወት ጀምሬ ባሳየሁት ጥሩ ነገር በኮሮና ምክንያት ውድድሩ እስኪቋረጥ ድረስ ከቡና፣ መከላከያ፣ ጥሩነሽ ዲባባ እና ድሬደዋ ከተማ ጋር በቋሚነት ተጫውቻለው። በደጋፊውም በክለቡ አመራርም ፣ በአሰልጣኞችም እምነት ተጥሎብኝ ከዋናው ቡድን ጋር ልምምድ እድሰራ አሪፍ እድል ተመቻችቶልኝ ነበር። ወደ ፊትም መልካም ነገር እየታየኝ ባለሁበት ሁኔታ ውድድሩ በመቋረጡ በጣም አዝኛለው። ያው እስካሁን ልምምዴን እየሰራሁ ነው።

“ወደ ፊት የምወደውን ክለቤ ትልቁ ግቡ በአፍሪካ መድረክ የበላይ ሆኖ ማጠናቀቅ ነው። እኔም ይሄን ለማሳካት ረጅም ዓመት መጫወት እና በተሻለ ከፍ ባለ ሁኔታ ስሙን ለማስጠራት ህልም አለኝ። የኢትዮጵያ ግብጠባቂዎች አብዮት በኛ ዘመን ይነሳል፤ ይህን ተስፋ አደርጋለው። ከኢትዮጵያም ውጭ መጫወት አስባለው። አካዳሚ በነበረኝ ቆይታ አሰልጣኞቼ ቻላቸው ለሜቻ፣ ሐብታሙ፣ አብረውኝ የነበሩ ጓደኞቼን አመሰግናለው። ጋሽ ተመስገን ተሰማ አካዳሚ እያለው ይረዱኝ ነበር። ቤተሰቦቼ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ አመራሮች፣ የቡድን አጋሮቼ እና አሰልጣኞች እና የቅዱስ ጊዮርጊስ የግብጠባቂ አሰልጣኝ ጋንዳን በጣም አመሰግናለው”።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!