በ28ኛ ሳምንት መጀመርያ ቀን ቀዳሚ የሆነው የአዳማ ከተማ እና የመቐለ 70 እንደርታ ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተገባዷል።
አዳማ ከተማ ነጥብ ተጋርተው ከወጡበት የባለፈው ሳምንት ጨዋታ አሰላለፍ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳያደርጉ ለጨዋታው ቀርበዋል። በተቃራኒው መቐለ 70 እንደርታ ከሽንፈት መልስ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም መድሃኔ ብርሀኔ፣ ዘረሰናይ ብርሃነ እና ንኩዋ ሐምፖን አሳርፈው ብሩክ ሙሉጌታ፣ ሰለሞን ሐብቴ እና ኢማኑኤል ሳባን ላሪዬ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ተጠባቂው ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በላይ ታደሰ ሲመሩት ሁለቱም ቡድኖች የሚሰሩ ስህተቶች በቀጣይ በሊጉ ለመቆየት በሚያደርጉት ጥረት ዋጋ የሚያስከፍላቸው እንዳይሆን በማሰብ የጥንቃቄ አጨዋወት በመምረጣቸው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራዎችን ለማድረግ ዘለግ ያሉ ደቂቃቆች ወስደዋል። ይሁን እንጂ የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ለመቆጣጠር የሚደረገው ፉክክር እና ፍትጊያ ጨዋታውን ሳቢ አድርጎት እንዲቀጥል ሆኗል።
ከውሃ ዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ በአንፃራዊነት ተሽለው የመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች በ30ኛው ደቂቃ ከሄኖክ አዱኛ ከቅጣት ምት መነሻውን ያደረገውን ኳስ በግራ መስመር ሰለሞን ሐብቴ ተቀብሎ ያሻገረውን ያሬድ ብርሃኑ በግንባሩ አመቻችቶ ያቀበለው እና ብሩክ ሙሉጌታ ከጎሉ ቅርበት በግንባር በመምታት ወደ ላይ የላከው ኳስ ለጥቂት ዒላማውን ስቶባቸዋል።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎችም መቐለ 70 እንደርታዎች የጨዋታውን የበላይነት በመውሰድ በተደጋጋሚ የአዳማን የግብ ክልል ቢጎበኙም የጠራ ጥቃት ለመሰንዘር ሲቸገሩ ተስተውሏል። ጫናዎች የበዛባቸው አዳማዎች አልፎ አልፎ ኳሱን ለመቆጣጠር ከማሰብ ባለፈ ለመከላከል ሲጥሩ ቆይተው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራም ሳያደርጉ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
የሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር አድናንን ወደ መሐል በማስገባት ሙሴ ኪሮስን በቢንያም አይተን በመቀየረ የማጥቃት ኃይላቸውን ለማጠናከር ያሰቡት አዳማ ከተማዎች በጨዋታው የመጀመርያ ሙከራቸውን አድርገዋል። በ54ኛው ደቂቃ ላይ ነቢል ኑሪ በጥሩ መንገድ በተከላካዮች መሐል ሰንጥቆ አሾልኮለት ኳስ ተቀይሮ የገባው ቢንያም አይተን ኳሱን በመግፋት የመታውን ፈጥኖ የወጣው ግብ ጠባቂው ሶፎንያስ እንደምንም ጎል እንዳይሆን ከልክሎታል።
ከዚህች ሙከራ በኋላ የጨዋታው እንቅስቃሴ ተመጣጣኝ መልክ ኖሮት ሲቀጥል በ65ኛው ደቂቃ ላይ መቐለዎች በኩል ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ቡሩክ ሙሉጌታ ለጎል ያልቀረበ ሙከራ ካደረገ ከሁለት ደቂቃ በኋላ አዳማ ከተማዎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ቢንያም አይተን ከግራ መስመር ተከላካይ በመቀነስ ወደ ውስጥ ያሻገረውን ስንታየሁ መንግስቱ ወደ ጎልነት ቢቀይረውም ከጨዋታ ውጭ ነው መባሉ ክርክር ያስነሳ ክስተት ሆኖ አልፏል።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የአዳማ የበላይነት የታየ ሲሆን በ84ኛው ደቂቃ ቢንያም አይተን ነፃ የጎል አጋጣሚ አግኝቶ ከውሳኔ ችግር ሲያመነታ የመቐለ ተከላካዮች ሲደርሱበት ከጀርባው ለመጣው ቻላቸው መንበሩ ሰጥቶት ወደ ላይ የሰደዳት አጋጣሚ ከተፈጠረ በኋላ ጨዋታው ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።