ፌዴሬሽኑ የአሰልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌን ቅጥር ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከሳምንት በፊት አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌን በይፋ ማሰናበቱን ተከትሎ የመከላከያው አሰልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ በጊዜያዊ አሰልጣኝነት ቢሾሙም ፌዴሬሽኑ እስካሁን ይፋ ሳያደርገው ቆይቶ ከደቂቃዎች በፊት ይፋ አድርጓል፡፡

በአሰልጣኙ ቅጥር ዙርያ የፌዴሬሽኑ መግለጫ ይህንን ይመሰላል፡፡

በፌዴሬሽኑና በአሠልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ መካከል የሥራ ውል ስምምነት ተፈረመ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን ከሥራ ማሰናበቱን ተከትሎ ዛሬ ግንቦት 1 ቀን 2008 ዓ.ም
በፌዴሬሽኑና በአሠልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ መካከል የሥራ ውል ስምምነት ተፈርሟል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና በገብረመድን ኃይሌ መካከል የተፈረመው የሥራ ውል ከግንቦት 1 ቀን 2008 ዓ.ም እስከ መስከረም 30/2009 ዓ.ም ለአምስት ወራት የሚቆይ ነው፡፡
በተጠቀሱት ወራት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለአሠልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ በየወሩ ያልተጣራ ብር 80,000.00 /ሰማኒያ ሺህ ብር/ ይከፍላል፡፡ የቴሌፎን ፣ የኃላፊነትና የነዳጅ ጥቅማ ጥቅሞችንም ይጠብቃል፡፡
አሠልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ሁለት ቀሪ የማጣሪያ ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግብ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
በአሠልጣኝ ገብረመድን ኃይሌና በፌዴሬሽኑ ከፍተኛ የሥራ መሪዎች መካከል ውይይት በተደረገበት ወቅት አሰልጣኝ ገብረመድን እንደገለፀው ለብሔራዊ ቡድን በመጫወት ያገኘው ትልቅ ክብር ለእዚህ ከባድ ሃገራዊ ኃላፊነት ስምምነቱንና ፈቃደኝነቱን
በመግለፅ ብሔራዊ ግዴታውን ለመወጣት ያስገደደው ሆኗል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ከሲሼልስ የማጣሪያ ጨዋታ ጀምሮ ያስመዘገበውን ዝቅተኛ ውጤት ተከትሎ ፌዴሬሽኑ ፈጣን እርምጃ አለመውሰዱ ክፍተት እንደፈጠረ በመቁጠር የተቀበለው ሲሆን በቀጣይነት ውስጣዊ የአሠራር ሥርዓት ማስተካከያ ለማድረግ ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
በሂሳባዊ ስሌት የቡድናችን ለ2017 የአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ተስፋው ሙሉ በሙሉ ያልተሟጠጠ በመሆኑም ፌዴሬሽኑ በእግር ኳስ ቤተሰቦች ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታ የሚሰጠውን ገብረመድን ኃይሌን በጊዜያዊ አሠልጣኝነት እንዲሾም አድርጓል፡፡ አሠልጣኝ ገብረመድን የተረከበውን ከባድ ኃላፊነት በብቃት እንዲወጣና ቡድናችን የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግብ የእግር ኳስ ቤተሰቦች የተለመደ ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉም ፌዴሬሽኑ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *