የምስራቅ እና መካከኛው አፍሪካ የእግርኳስ ማህበር (ሴካፋ) በየአመቱ የሚያዘጋጀው የካጋሜ ክለብ ዋንጫ በታንዛኒያ አዘጋጅነት ዳሬ ሰላም ላይ ይካሄዳል፡፡
ሴካፋ ይፋ እንዳደረገው ከሆነ የክለብ ውድድሩ ሐምሌ 9 ይጀምራል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ሊጎች በሚያሸንፉ ክለቦች መካከል የሚደረገው ውድድር እንደከዚህ ቀደሞቹ ሁሉ በሩዋንዳው ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ ስፖንሰር ተደርጓል፡፡
ታንዛኒያ በ2015 የተካሄደውን የካጋሜ ክለብ ዋንጫ ያሰናዳች ሲሆን የሃገሪቱ ክለብ የሆነው አዛም በፍፃሜው ጨዋታ የኬንያውን ጎር ማሂያን 2-0 በማሸነፍ ለመጀመሪያ ግዜ ዋንጫውን ማንሳት ችሏል፡፡
አምና ኢትዮጵያን በመወከል በ2014/15 ፕሪምየር ሊጉን በሶስተኛነት የጨረሰው አዳማ ከተማ ተሳትፎ አድርጓል፡፡ አዳማ አዛም፣ የዩጋንዳው ካምፓላ ሲቲ ካውንስል እና የደቡብ ሱዳኑ አል ማላኪያ ከሚገኙበት ምድብ በጊዜ ተሰናብቷል፡፡
አንድም የኢትዮጵያ ክለብ የሴካፋ ክለቦች ዋንጫን አሸንፎ የማያውቅ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2010 ፍፃሜ በመድረስ የመጀመሪያው ክለብ ነው፡፡ ፈረሰኞቹ በሩዋንዳው ኤፒአር 2-0 ተሸንፈው ዋንጫውን ማንሳት ሳይችሉ መቅረታቸው ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ የነሃስ ሜዳልያ በማጥለቅ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ክለብ ነው፡፡