ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሦስት ተጫዋቾች አስፈርሟል

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሦስት ተጫዋቾች አስፈርሟል

ትናንት የሦስት ነባር ተጫዋቾችን ውል በማራዘም ወደ ዝውውሩ መስኮት የገቡት ንግድ ባንኮች ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርመዋል።

በአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ የሚመሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ዘግይተውም ቢሆን በትናትናው ዕለት የእንዳለ ዮሐንስን፣ ዮናስ ለገሰን እና ዳዊት ዮሐንስ ውል ያራዘሙ ሲሆን አሁን ደግሞ ሦስት ተጫዋቾችን ማስፈረማቸው ታውቋል።

የመጀመርያው ፈራሚ ግብ ጠባቂው ጆርጅ ደስታ ሲሆን በከፍተኛ ሊግ በተለያዩ ክለቦች ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን ዘንድሮ በደሴ ከተማ ጥሩ ጊዜን አሳልፏል። ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ መድን ጋር ከአሰልጣኝ በፀሎት ጋር አብሮ የሰራ ሲሆን በድጋሚ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሁለት ዓመት አብሮ ለመስታት ፊርማውን አኑሯል።

ሌላኛው ፈራሚ ደግሞ ከታዳጊ እስከ ዋና ቡደን በኢትዮጵያ መድን ቆይታ የነበረው እና መድኖች ወደ ሊጉ ሲያድጉም ዘንድሮም የሊጉን ዋንጫ ሲያነሱ አብሮ የነበረው አማካይ መስፍን ዋሼ ሲሆን አሁን ለንግድ ባንክ ለሁለት ዓመት ለመፈረም ተስማምቷል።

ሦስተኛው ፈራሚ አማካይ ብሩክ ብፁዓምላክ ነው። በቢሸፍቱ ከተማ የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው አማካዩ በነገሌ አርሲ እና በገላን ከተማ ተጫውቶ በማሳለፍ በ2015 ንግድ ባንኮች ወደ ሊጉ እንዲያድጉ ትልቁን አስተዋፆኦ ያደረገ ሲሆን በመቀጠል በ2016 የሊጉ ቻምፒዮን ሲሆኑ የቡድኑ አካል ነበር። ዘንድሮ ከደሴ ከተማ ጋር የአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ዳግም ለሁለት ዓመት ንግድ ባንክን መቀላቀሉ ታውቋል።