ሽረ ምድረ ገነት የሁለት ተጫዋቾች ዝውውር አጠናቀቀ

ሽረ ምድረ ገነት የሁለት ተጫዋቾች ዝውውር አጠናቀቀ

ሽረ ምድረ ገነቶች ቡድናቸውን ማጠናቀር ቀጥለውበታል።

በአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ የሚመራው ሽረ ምድረ ገነት ቀደም ብሎ በዝውውሩ መስኮቱ መክብብ ደገፉ፣ ተካልኝ ደጀኔ፣ በኃይሉ ግርማ፣ ቢንያም ላንቃሞ፣ ፀጋአብ ዮሐንስን እንዲሁም አጥቂው አቤል ማሙሽን ማስፈረሙ የሚታወቅ ሲሆን አሁን ደግሞ ሁለት ተጫዋቾች ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል።

ቀዳሚው ወደ ቡድኑ ያመራው ተጫዋች በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ከኢትዮጵያ መድን ጋር የሊጉን ዋንጫ ያነሳው የመሐል ተከላካዩ አዲስ ተስፋዬ ነው። ከዚህ ቀደም በወላይታ ድቻ፣ መቻል፣ ሰበታ ከተማ እና አዳማ ከተማ መጫወት የቻለው በፕሪምየር ሊጉ የረዥም ዓመታት ልምድ ያለው የመሀል ተከላካዩ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከቆየበት ኢትዮጵያ መድን የነበረውን ውል ማጠናቀቁን ተከትሎ ማረፍያው ሽረ ምድረ ገነት ሆኗል።

ሁለተኛው ወደ ቡድኑ ያመራው ተጫዋች ደግሞ አማካዩ ስንታየሁ ዋለጬ ነው። ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ታዳጊ ቡድን አድጎ ባለፉት ዓመታት በአሳዳጊ ክለቡ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዋናው ቡድን ጨምሮ በሀድያ ሆሳዕና እና በኢትዮጵያ ቡና ቆይታ የነበረው አማካዩ በ2016 የውድድር ዓመት አጋማሽ ላይ ከተቀላቀለበት ኢትዮጵያ ቡና የነበረውን ውል አጠናቆ ወደ ሽረ ምድረ ገነት ለማምራት ፌርማውን አኑሯል።