በቅርቡ ከቡናማዎቹ ጋር በስምምነት የተለያየው ተጫዋች ዐፄዎቹን ለመቀላቀል ከስምምነት ደርሷል።
በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመሩትና ቀደም ብለው ሞየስ ፖዎቲ፣ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ፣ ያሬድ ብርሃኑ እና አብዱልአዚዝ አማንን ያስፈረሙት ፋሲል ከነማዎች አሁን ደግሞ ባለፈው አንድ ዓመት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ቆይታ የነበረው ዩጋንዳዊው የመሀል ተከላካይ ዋሳዋ ጄኦፍሪ ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል።
በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በ26 ጨዋታዎች ተሳትፎ 1900′ ደቂቃዎች ቡናማዎቹን በማገልገል ቀሪ ውል እያለው በስምምነት የተለያየው ይህ ተጫዋች ከዚህ በፊት በሀገሩ ክለቦች ካምፓላ ሲቲ ፣ ቫይፐርስ እና በኤስ ሲ ቪላ ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን አሁን ደግሞ ዐፄዎቹን ለመቀላቀል ተስማምቷል።