የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና በተለያዮ ክለቦች ሲጫወት የምናቀው የቀደሞ ኮከብ ግብ ጠባቂ በአሰልጣኝነት ወደ ሊጉ ተመልሷል።
የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸው በመቀመጫ ከተማቸው የጀመሩት እና በቅርቡ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅታቸውን ያጠናቀቁት ሀይቆቹ ግዙፉን የቀድሞ ኮከብ ግብ ዘብ ሲሳይ ሲሳይ ባጫን የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኛቸው አድርገው መሾማቸውን አውቀናል።
በመላው የሲዳማ ውድደር ላይ ባሳየው ምርጥ ብቃት ከ2000-04 ሲዳማ ቡናን በመቀላቀቀል ሲዳማ ቡናን ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ያሳደገው እና የ2003 የሊጉ ኮከብ ግብ ጠባቂ ክብር ያገኘው ግዙፉ ግብ ጠባቂ ሲሳይ ባጫ በ2005 ከደደቢት ጋር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ማሳካት ችሏል።
በማስከተል ወልድያ ፣ አዳማ ከተማ፣ ጅማ አባቡና እና አርባምንጭ ከተማን በሊጉ ያገለገለ ሲሆን በመቀጠል በከፍተኛ ሊግ ሻሸመኔ ከተማ ተጫውቶ አሳልፏል። በ2013 ሮቤ ከተማን ከአንደኛ ሊግ ወደ ከፍተኛ ሊግ ያሳደገው የግብ ዘቡ ወደ ዱራሜ በማቅናትም በተመሳሳይ ቡድኑን ወደ ከፍተኛ ሊግ ማምጣቱ ይታወሳል። ያለፉትን አስራ ስድስት ዓመት ካገለለገለው ግብ ጠባቂነት ጓንቱን በመስቀል ባሳለፍነው ዓመት ወደ አሰልጣኝነት በመምጣት ደደቢትን ሲያገለግል ቆይቷል።
አሁን የሀዋሳ ከተማ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝነትን የተረከበው ሲሳይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተለያዩ ጊዜዎች በመመረጥ ሀገሩን ሲያገለግል የቆየ ሲሆን አይረሴውን ከ31 ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ አፍሪካ ዋንጫ ስትገባ የቡድኑ ባለ ታሪክ አባል እንደነበረ አይዘነጋም።