ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የደረሱት ሉሲዎቹ የመልሱን ጨዋታ የሚያደርጉበት ሜዳ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በ2026 የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከታንዛንያ ጋር ለሚያደርጋቸው ወሳኝ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ለ23 ቀናት በሀገር ቤት ሲያደርጉ የቆዩትን ዝግጅት አጠናቆ ትናንት የመጀመርያውን ከሜዳ ውጭ ጨዋታውን ለማከናወን 21 ተጫዋቾችን በመያዝ ወደ ታንዛንያ ማቅናቱ ይታወሳል።
ዛሬ በዳሬ ሰላም አዛም ኮምፕሌክስ 11:00 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል። ሆኖም የመልሱ ጨዋታ አስቀድሞ በአበበ ቢቂላ ስታድየም ለማከናወን ታስቦ የነበረ ቢሆንም ካፍ የአበበ ቢቂላ ስታድየም ካታጎሪ ሁለት ጨዋታዎችን ለማድረግ አይመጥንም በማለቱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሌላ አማራጭ ሜዳዎችን ለማስመዝገብ በጠየቀው መሠረት ኬንያዊት ዕንስት የካፍ ክለብ ላይሰንሲግ ከምጋሚ ከሰሞኑን በመምጣት በሁለት ስታዲየሞች ላይ ግምገማ ተደርጓል።
በዚህ መነሻነት ካፍ ዛሬ ባሳወቀው መሠረት የሉሲዎቹ ወሳኝ የመልስ ጨዋታ ማክሰኞ ጥቅምት አስራ ስምንት በድሬደዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም እንደሚከናወን አውቀናል።